መረጃ በመመንተፍ የተጠረጠሩት ቻይናውያን
የምስሉ መግለጫ,መረጃ በመመንተፍ የተጠረጠሩት ቻይናውያን

ከ 8 ሰአት በፊት

በሚሊዮን የሚቆጠሩ አሜሪካውያን የኢንተርኔት ‘አካውንቶች’ የቻይና ዜግነት ባላቸው መረጃ መንታፊዎች በዘረጉት እና እጅግ አደገኛ በሆነ ወጥመድ መያዛቸውን የአሜሪካ ባለስልጣናት፣ የፍትህ ቢሮ እና ኤፍ ቢ አይ ገልጸዋል።

በዚህ መጠነ ሰፊ የመረጃ ምንተፋ ወይም ‘ሳይበር አታክ’ ዘመቻ ላይ እንደተሳተፉ የተጠረጠሩ 7 ቻይናውያን ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ተከሳሾቹ 14 ዓመታት አስቆጥሯል በተባለው የዚህ የመረጃ ምንተፋ ስራ ግንኙነት እንዳላቸው ተጠርጥሯል።

የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሰባቱን ተጠርጣሪዎች ለሚጠቁም እስከ 10 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሸልም አስታውቋል።

መረጃ መንታፊዎቹ አሜሪካን እና ቻይናን በመተቸት የሚታወቁ የውጪ የንግድ ተቋማት እና ፖለቲከኞችን ኢላማ ማድረጋቸውን የፍትህ ቢሮ አስታውቋል።

ሰባቱ ተጠርጣሪዎች በተለያዩ አህጉራት ለሚገኙ ሰዎች ከ 10 ሺህ በላይ ለጠለፋ የሚያጋልጥ ይዘት ያላቸውን ኢሜይሎችን መላካቸውን የገለጸው የአሜሪካ ፍትህ ቢሮ ዓለም አቀፍ የመረጃ ምንተፋ ዘመቻ ሲል ጠርቶታል።

ዘመቻው በቻይና መንግሥት የሚደገፍ ነው ሲልም ከሷል።

የኤፍ ቢ አይ ዳይሬክተር ክሪስቶፎር ሬይ “ዛሬ ይፋ ያደረግነው መረጃ ቻይና የሀገራችንን የሳይበር ደህንነት፣ አሜሪካውያንን እንዲሁም ፈጠራዎቻችንን ለመናድ የምታደርገውን ሙከራ ያጋለጠ ነው” ብለዋል።

ጨምረውም ቻይና በዚህ መንገዷ የምትቀጥል ከሆነ ኤፍ ቢ አይ ሀገራቸው በፍጹም እንዳማትታገስም ተናግረዋል።

ኤፍ ቢ አይ ይህንን ከማለቱ ጥቂት ቀደም ብሎ የዩናይትድ ኪንግድም መንግሥት በሀገሩ እየተከናወነ ላለው መረጃ ምንተፋ ዘመቻ ቻይናን ተጠያቂ አደርገዋል።

በለንደን የቻይና ኤምባሲ የሚገኙ ዲፕሎማቶችን ይህንን ክስ በጽኑ አቋም የተቹ ሲሆን “ሙሉ በሙሉ የፈጠራ ወሬ ነው” ብለዋል።

በተመሳሳይ የኒውዚላንድ መንግሥት የሀገሪቱ ፓርላማ ቻይና ባሰማራቻቸው የመረጃ መንታፊዎች ኢላማ መደረጉን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ሆኖም በዋሽንግተን የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ቃል አቀባይ ይህንን ክስ ውድቅ አድርገዋል።

“ያለምንም አስተማማኝ ማስረጃ ሀገራት ያልተገባ ደምዳሜ ላይ ደርሰዋል” ያሉ ሲሆን “መሰረት የሌለው ክስ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

በሰባቱ ቻይናውያን ላይ የቀረበው ክስ የሰዎችን የስራ ‘አካውንት’፣ የግለሰብ ኤሜይሎችን፣ የኢንተርኔት ማከማቻዎችን መጥለፍን እንዲሁም የስልክ ልውውጦችን መቅረጽን ይመለከታል።

መንታፊዎቹ የሚልኳቸው ኢሜይሎች ከታዋቂ የዜና ተቋማት ወይም ጋዜጠኞች የተላኩ በማስመሰል እና ሰዎችን ለማጥመድ እና ለመከታተል የሚያስችሉ ሊንኮችን ያካትታሉ።

ታዲያ የተላከላቸው ሰዎች ይህንን ሊንክ ሲከፍቱ ያሉበት ቦታ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ቁሶችን መለያ ቁጥር (IP addresses) ሰባቱ ቻይናውያን ወደሚቆጣጠሩት ሰርቨር (ቋት) እንደሚተላለፍ ተነግሯል።

በእነዚህ መረጃዎች አማካኝነት ደግሞ ሌሎች ውስብስብ የመጥለፍ ስራዎችን ለመከወን እንደሚጠቀሙበት አቃቤ ህግ ገልጿል።

መንታፊዎቹ በተጨማሪም በአሜሪካ ዋይት ሃውስ እና ውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት የሚሰሩ ሰዎችንም ኢላማ እንደሚያደርጉ ተነግሯል።

በሌካ በኩል የመከላከያ፣ የኢንፎርሚሽን ቴክኖሎጂ፣ ቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ የንግድ፣ የፋይናንስ፣ የህግ እንዲሁም የምርምር ተቋማት ላይም እንደሚያነጣጥሩ ተዘግቧል።