አሜሪካዊው ራፐር ሾን "ዲዲ" ኮምብስ

ከ 8 ሰአት በፊት

ሾን “ዲዲ” ኮምብስ የተሰኘው ጉምቱው ራፐር መኖሪያ ቤት ሰኞ ዕለት በአሜሪካ ፌዴራል ፖሊስ ፍተሻ እንደተደረገበት ተዘገበ።

ሆምላንድ ሴኪዩሪቲ የተሰኘው የሀገር ውስጥ ፀጥታ መሥሪያ ቤት እንደገለጠው “እያደረገው ባለው ምርመራ መሠረት” ኒው ዮርክ፣ ሎስ አንጀለስ እና ማያሚ ያሉ ንብረቶች ላይ ፍተሻ አድርጓል።

ሎስ አንጀለስ እና ማያሚ የሚገኙ የራፐሩ ሁለት መኖሪያ ቤቶች ፍተሻ ተደርጎባቸዋል።

ባለሥልጣናቱ ለምን ድንገተኛ ፍተሻ እንዳደረጉ አሊያም ጉዳዩ እንዴት ከዲዲ ጋር ሊያያዝ አንደቻለ እስካሁን ምንም አላሉም።

የሂፕ ሆፕ የሙዚቃ ዘውግ አቀንቃኝ የሆነው ራፐር ተወካዮች ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አልሰጡም።

ነገር ግን ራፐሩ በቅርብ ጊዜያት በርካታ የፆታዊ ጥቃት ክሶች ቀርበውበታል። ጠበቃዎቹ ግን የቀረቡበትን ክሶች በሙሉ ውድቅ ያደርጋሉ።

ሰኞ የሆምላንድ ሴኪዩሪቲ መርማሪዎች 2570 ሜትር ስኩዌር ላይ ያረፈውን የራፐሩን የተንጣለለ መኖሪያ ቤት ሲፈትሹ ታይተዋል።

ዲዲ ባለፈው መስከረም አዲስ አልበም እንደሚለቅ ይፋ ያደረገው ከዚህ ሰፊ ግቢ ሆኖ ነው።

ይህ መኖሪያ ቤት የራፐሩ ኩባንያ የሆነው ባድ ቦይስ ፊልምስ ፕሮዳክሽን ንብረት ነው።

በሎስ አንጀለስ የልጥጥ ሀብታሞች መኖሪያ ሥፍራ በሆነው ሆልምቢ ሂልስ የሚገኝ ሲሆን መንደሩ እጅግ ታዋቂ ሰዎች የሚኖሩበት ነው።

ሁለት የፓሊስ አባላት ለአሶሺየትድ ፕሬስ እንደተናገሩት ድንገተኛ ፍተሻው የሕገ-ወጥ ወሲብ ዝውውር ምርመራ አካል ነው።

ቢቢሲ ይህ ዘገባ እውነት ስለመሆኑ በራሱ አላረጋገጠም።

ባለፈው ዓመት የአር ኤንድ ቢ ዘውግ አቀንቃኟ ካሳንድራ ቬንቹራ [ኬሲ] ኒው ዮርክ በሚገኝ ፍርድ ቤት ራፐሩ የተለያዩ ጥቃቶች አድርሶብኛል ስትል ክስ አቅርባ ነበር። ኬሲ እና ዲዲ ከ2005 እስከ 2018 ባለው ጊዜ አብረው ይኖሩ ነበር።

ከፍርድ ቤት የተገኙ ወረቀቶች እንደሚያሳዩት ራፐሩ ለዓመታት ጥቃት ያደርስባት እንደነበር ነው። ነገር ግን በኋላ ክሱ ተቋርጦ በድርድር ሸንጎ ተፈትቷል። በወቅቱ ራፐሩ በርካታ ገንዘብ እንደከፈላት ተዘግቦ ነበር።

ከዚህ በኋላ ሁለት ሌሎች ሴቶች ራፐሩ ወሲባዊ ጥቃት አድርሶብናል ሲሉ ከሰውታል። አንድ ወንድ በተመሳሳይ ሾን ኮምብስ ወሲባዊ ትንኮሳ አድርሶብኛል ሲል ክስ አቅርቦበታል።

የካሳንድራ እና የአንዲት ሌላ ከሳሽ ጠበቃ የሆኑት ዳግላስ ዊግዶር ሰኞ ዕለት በሰጡት ቃል ደንበኞቼ ፖሊስ እያደረገ ያለውን ነገር ይደግፋሉ ብለዋል።

“ኮምብስ ላደረገው ነገር ተጠያቂ እንዲሆን ይህ በር ይከፍታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል ጠበቃው በመግለጫቸው።

ሾን “ዲዲ” ኮምብስ በሂፕ ሆፕ የሙዚቃ ዘውግ አሉ ከሚባሉ ‘ፕሮዲውሰሮች’ መካከል ሲሆን ለበርካታ ዓመታት በኢንዱስትሪው ቁንጮ ሆኖ ቆይቷል።

ባድ ቦይ ሬከርድስ የተሰኘው ኩባንያ መሥራች የሆነው ዲዲ ሶስት ጊዜ የግራሚ ሽልማት ያገኘ ሲሆን ከሌሎች አሉ ከሚባሉ እንደ አሸር እና ሜሪ ጄ ብላይጅ ያሉ አርቲስቶች ጋር ሠርቷል።