
ከ 9 ሰአት በፊት
አርብ ምሽት መጋቢት 13/2016 ዓ.ም. በሩሲያዋ መዲና ሞስኮ በሚገኘው የሙዚቃ አዳራሽ ላይ ጥቃት በደረሰ በሰዓታት ጊዜ ውስጥ ኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) በቴሌግራም ገፁ ኃላፊነት የወሰደው።
ጽንፈኛው የሱኒ ቡድን አይኤስ እንደ ማረጋገጫ ጥቃቱ ሲደርስ የሚያሳይ ቪድዮ አብሮ የለቀቀ ሲሆን፣ ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ ትክክለኛ ነው የሚል ማረጋገጫ ሰጥታለች።
አሜሪካ ጥቃቱ ከመፈጸሙ ከቀናት በፊት በሩሲያ የሚገኙ ዜጎቿ ብዙ ሰዎች ወደሚሰበሰቡበት ሥፍራ እንዳይሄዱ ማስጠንቀቂያ ያወጣቸው “ጽንፈኞች” አደጋ ሊያደርሱ ይችላሉ በሚል ፍራቻ ነው።
ዋሺንግተን እንደምትለው ከሆነ ለሞስኮም ማስጠንቀቂያው ተሰጥቷል። ለጊዜው ስለዚህ ጉዳይ ከሩሲያ በኩል የተሰማ ነገር የለም።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በዩክሬን ውስጥ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት በሩሲያ እና በአሜሪካ መካከል ያለው ውጥረት እየከረረ ነው።
ሩሲያ ከ140 በላይ ሰዎች ለሞቱበት እና በርካቶች ለቆሰሉበት አደጋ ተጠያቂ ናቸው ያለቻቸውን ተጠርጣሪዎች “በሽብር” ጥቃት ከሳቸዋለች።
የዐይን እማኞች ለቢቢሲ ሲናገሩ ታጣቂዎቹ ቡናማ ልብስ ለብሰው ወደ ክሮከስ ከተማ አዳራሽ የገቡት አርብ ምሽት 2፡00 ሰዓት አካባቢ ነው። ታጣቂዎቹ ፒንክ የተባለውን ባንድ ሙዚቃ ሊታደሙ የመጠ ሰዎችን በጥይት እየመቱ፤ ተቀጣጣይ ፈሳሽ እየወረወሩ ነበር።
በጥቃቱ ምክንያቱ አዳራሹ በእሳት ሲያያዝ የሕንፃው ላይኛው አካል በከፊል የተደረመሰ ሲሆን፣ ሁለት ፎቆች ከጥቅም ውጪ ሆነዋል።
የሩሲያ መንግሥት ከጥቃቱ ጀርባ ማን ሊኖር ይችላል ስለሚለው ጉዳይ እስካሁን ያለው ነገር የለም። ነገር ግን የመንግሥት ፕሮፓጋንዳን የሚያራምዱ መገናኛ ብዙኃን አይኤስ ነው መባሉን አይቀበሉትም።
ባለሥልጣናት አራቱ ተጠርጣሪዎች የኢስላሚክ ስቴት አባላት ስለመሆናቸውም ሆነ ጥቃቱን ያደረሰው አካል ማን ነው የሚለውን ጉዳይ መልስ አልሰጡበትም።
በርካታ ተንታኞች ሩሲያ ለምን የአይኤስ ዒላማ ሆነች? ቡድኑ ከጥቃቱ ጀርባ አለ ወይ? የሚለውን ጉዳይ እንዲህ ያስረዳሉ።
- በሞስኮው ጥቃት ተሳታፊ ናቸው የተባሉት ላይ ክስ ተመሠረተ25 መጋቢት 2024
- ፑቲን ከምንጊዜውም በላይ ኃያል የሚሆኑባቸው ሦስት ምክንያቶች21 መጋቢት 2024
- ቭላድሚር ፑቲን፡ ከኬጂቢ ሰላይነት እስከ ረጅም የፕሬዝዳንትነት ዘመን20 መጋቢት 2024

የታሊባን ግንኙነት
ኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ሩሲያ ላይ ጥቃት ሲሰነዝር ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ቡድኑ 2015 (እአአ) ከግብፅ ተነስቶ 224 ሰዎችን አሳፍሮ ከግብፅ ተነስቶ ወደ ሩሲያ እያቀና ሳለ ለፈነዳው አውሮፕላን ጥቃት ኃላፊነት ወስዷል።
በ2022 ደግሞ ቡድኑ ካቡል በሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ላይ ጥቃት የፈጸመ ሲሆን፣ በዚህም ሁለት ሩሲያውያን ዲፕሎማቶች እና አራት አፍጋናዊያን ተገድለዋል።
እስላማዊ ቡድኖች ሩሲያን አምርረው ከሚጠሉባቸው ምክንያቶች መካከል የአፍጋኒስታን እና የቼቺኒያ ጦርነቶች ይጠቀሳሉ። ኢስላሚክ ስቴት አክሎም ሩሲያ በሶሪያ እና በምዕራብ አፍሪካ ያሉ አባሎቼ ላይ ጥቃት እያደረሰች ነው ይላል።
“ሩሲያ በአይኤስ እና አጋሮቹ ላይ በሚደረጉ ‘ኦፕሬሽኖች’ መሳተፏ፤ አልፎም ከታሊባን ጋር ያላት ግንኙነት ቁልፍ ጠላት እንድትሆን አድርጓታል” ይላሉ ተባባሪ ፕሮፌሰር አሚራ ጃዱን።
በአሜሪካው ክሌምሰን ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩት አሚራ “አይኤስ በአፍጋኒስታን እና ፓኪስታን” የተሰኘ መጽሐፍ በትብብር ፅፈዋል።
በሩሲያው የሙዚቃ አዳራሽ የተፈጸመውን ጥቃት ያቀናጀው የአይኤስ የአፍጋን ክንፍ እንደሆነ ይታመናል። ቡድኑ በ2015 ከምሥራቅ አፍጋኒስታን ኾራሳን የተነሳ ሲሆን፣ ይህ ቦታ አንድ ሰሞን ኦሳማ ቢን ላደን ተደብቆበት ነበር።
መጀመሪያ ዒላማ ያደርግ የነበረው የአፍጋኒስታን የሺዓ እስልምና አማኞችን እና ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር በነረበው የሰላም ድርድር ተሳትፏል ያለውን ታሊባንን ነበር።
“ታሊባን ማለት የአይኤስ ጠላት ማለት ናቸው። ቡድኑ ታሊባን የሩሲያ ወዳጅ ነው ብሎ ያምናል” የሚሉት የዊልሰን ማዕከል የደቡብ እስያ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ማይክል ኩጌልማን ናቸው።
የአይኤስ የአፍጋን ክንፍ በቅርቡ ነው ግዛቱን ለማስፋፋት የወሰነው። ይህ ማለት ክፉኛ ሽንፈት ያስተናገደባቸውን ሶሪያን እና ኢራቅን ሙሉ በሙሉ ለቆ ሊወጣ ነው ማለት ነው ይላሉ ተንታኞች።
“በቅርቡ የምዕራቡ ዓለም የደኅንነት መሥሪያ ቤቶች ጥቃት ሊደርስ ይችላል ብለው ማወጃቸውን ተከትሎ በሩሲያ ጥቃት መድረሱ የአይኤስ ተግባር ሊሆን አንደሚችልም ጠቋሚ ነው” መሆኑን የወታደራዊ ጥናት ባለሙያው ሉካስ ዌበር ይናገራሉ።

የሙስሊም ጠላቶች
አይኤስ በቅርቡ የሚለቃቸው ፕሮፖጋንዳዎች የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን የሙስሊም ጠላት አድርጎ የሚስል እና በሩሲያም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ላይ ጥቃት እንዲሰነዘርባት የሚገፋፉ ናቸው።
“አሜሪካ እና ዴሞክራቱ ዓለም ከአምባገነን አገራት [ሩሲያ፣ ቻይና እና ኢራን] ጋር የሚያደርጉት ትግል ተካሯል። በዩክሬን እና በጋዛ ጦርነቶች አሉ። ነገር ግን ለኢስላሚክ ስቴት ሁሉም የሙስሊም ጠላት ናቸው፤ ሊጠፉም ግድ ነው” ሲሉ ሁለት የኢስላሚክ ስቴት አጥኚዎች ዎል ስትሪት ጆርናል የተሰኘው ጋዜጣ ላይ ጽፈዋል።
“የአይኤስ ስትራቴጂ አልፎ አልፎ ማጥቃት ብቻ ሳይሆን ውጤታማ ጥቃት መፈፀም ነው” የሚሉት ኢስላማባድ የሚገኙት ሪካርዶ ቫሌ ናቸው። “ዓላማው ጠንካራ ቡድን ሆኖ በመገኘት ተከታዮችን ማፍራት ነው።”
አክለውም “አይኤስ በትክክለኛው ሰዓት ጥቃት ለማድረስ ለመጠበቅ ዝግጁ ነው” ይላሉ።
“ዛሬስ ሞስኮ ናቸው። በቅርቡ ኢራን ነበሩ። ተጨማሪ ጥቃቶች ማድረሳቸው አይቀርም። በተለያዩ ዋና ከተሞች ጥቃት ሊኖር ይችላል” ይላሉ የቀድሞው የቱርክ ጦር ኮሎኔል ሙራት አስላን ለአል-ጄዚራ ሲናገሩ።
ሩሲያ ከማዕከላዊ እስያ ለሥራ ወደ አገሯ የሚመጡ ዜጎችን አላስገባም ብላለች መባሏ ሌላኛው ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።
ምንም እንኳ ከሌላ አገር የሚመጡ ዜጎቸ የሩሲያ የሰው ኃይል ወደ ዩክሬን ለጦርነት መሄዱን ተከትሎ ሥራ ለመሥራት ቢሄዱም፣ ሩሲያኛ ባለማወቃቸው ከፖሊስ ጭምር ጥቃት ይደርስባቸዋል።
በአሜሪካ የቀድሞው የኪርጊስታን አምባሳደር የሆኑት ካዲር ቶክቶጉሎቭ በዚህ ሐሳብ እንደሚስማሙ ለዎል ስትሪት ጆርናል ይናገራሉ።

አዲስ መመሪያ
የሞስኮው ጥቃት በተፈጸመ በማግስቱ አይኤስ ባወጣው መግለጫ በሙዚቃ አዳራሹ ለደረሰው ጥቃት ኃላፊነቱን ወስዷል።
ከአይኤስ ጋር ግንኙነት አለው የሚባለው አማክ የዜና ወኪል ጥቃቱን አድርሰዋል የተባሉ አራት ግለሰቦችን ፎቶ አሰራጭቷል። ነገር ግን ፊታቸው ግማሹ በጭንብል ተሸፍኗል።
የቢቢሲው ጽንፈኛ ቡድኖችን በተመለከተ ባለሙያ የሆነው ሚና አል-ላሚ ግን የቡድኑ መግለጫ የትኛው የአይኤስ ክንፍ ጥቃቱን እንደፈጸም አይገልጥም ይላሉ።
አይኤስ ጥቃቱ በየትኛው ክፍን እንደደረሰ አለመናገሩ የተለመደ ነው የሚሉት አል-ላሚ፣ ምናልባትም ሩሲያ ያለው ክንፉን ለመጠበቅ ያደረገው ሙከራ አሊያም ደግሞ የሩሲያው ክንፍ ባለመሳተፉ የሆነ ነው ሲሉ ይተነትናሉ።
የመንግሥት ደጋፊ የሆኑ የሩሲያ መገናኛ ብዙኃንም አይኤስ የትኛው ክንፉ ጥቃቱን እንዳደረሰ አልተናገረም ይላሉ። ስለዚህ የቡድኑ መግለጫ ውድቅ ነው በማለት ዩክሬንን ተጠያቂ ለማድረግ ይሞክራሉ። ኪዬቭ ግን ይህን ታስተባብላለች።
በተመሳሳይ አይኤስ ባለፈው ጥር በኢራኗ ከርማን ከተማ ለደረሰው ጥቃት ኃላፊነቱን ሲወስድ የትኛው የቡድኑ ክንፍ ጥቃት እንዳደረሰ አልጠቀሰም።
አል-ላሚ በሞስኮ የተፈጸመው እና የኢራኑ ጥቃት ተመሳሳይነት አላቸው ባይ ናቸው። በሁለቱም ጥቃቶች የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ከ100 በላይ ነው። ቀጥሎ ደግሞ ቡድኑ በሁለቱም አገራት ይህ ነው የሚባል እንቅሰቃሴ የለውም።

ተጠርጣሪዎች
በሞስኮው የሙዚቃ አዳራሽ ጥቃት አድርሰዋል የተባሉት አራት ተጠርጣሪዎች ማንነትን የሩሲያ ባልሥልጣናት ይፋ አድርገዋል።
ተጠርጣሪዎቹ ዳሌርድዦን ሚርዞየቭ፣ ሳይድክራሚ ራቻባሊዞዳ፣ ሻምሲዲን ፋሪዱኒ እና ሙሐማድሶቢር ፋይዞቭ ናቸው።
እሑድ ዕለት ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ፊታቸው አባብጦ እና በልዞ የታዩ ሲሆን፣ አንደኛው ተጠርጣሪ ደግሞ ‘ባንዴጅ’ ተደርጎለታል። ባለሥልጣናት ይህ የሆነው በታሠሩበት ወቅት ነው ይላሉ።
አራተኛው ተጠርጣሪ አንድ ዐይኑ የጠፋ ይመስላል ይላል የሮይተርስ ዘገባ። ይህ ተጠርጣሪ መራመድ ባለመቻሉ በተሽከርካሪ ወንብር (ዊልቼር) ነው ወደ ችሎት የገባው።
ተንታኞች እንደሚያምኑት አይኤስ በሩሲያ እና በኢራን ላይ የፈጸመውን ጥቃት እንደ ድል ነው የሚቆጥረው። አልፎም ይህን ጥቃት እንደ ፕሮፖጋንዳ ተጠቅሞ አሁንም ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆኑን በማሳየት አዳዲስ አባላት ሊመለምልበት ይችላል።
ነገር ግን ይህም ሆኖ ይህ ዓመት ለአይኤስ አጅግ ከባድ ነው፤ ብዙ ሽንፈት ያስተናገደበት ነው ይላሉ አል-ላሚ።
