የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ
የምስሉ መግለጫ,የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ

ከ 4 ሰአት በፊት

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በገንዘብ ዝውውር ሥርዓቱ ላይ አጋጥሞት በነበረው ችግር ምክንያት ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበት እንደበር አስታወቀ።

የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 17/2016 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት ችግሩ አጋጥሞ በነበረበት ጊዜ ደንበኞች በአካውንታቸው ካለው ገንዘብ በላይ ብር ወጪ በማድረግ ወይም በማዘዋወር ነው የተወሰደበት።

የአገሪቱ ትልቁ ባንክ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሳምንት በፊት መጋቢት 8 ምሽት ላይ በተፈጠረበት ችግር ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በደንበኞቹ እንደተወሰደበት ሲገለጽ ቆይቶ ነበር።

ባንኩ “ጤናማ ያልሆነ” ባለው መንገድ ደንበኞቹ የወሰዱበትን ገንዘብ እንዲመልሱ በተለያዩ መንገዶች ጥረት ሲያደርግ የነበረ ሲሆን፣ ለመመለስ ፈቃደኛ ያልሆኑትን ደግሞ ስማቸውን እና ፎቷቸውን ይፋ በማድግ በሕግ እንደሚጠይቅ ሲያሳስብ ቆይቷል።

ፕሬዝዳንቱ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ከተወሰደበት ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ውስጥ ሦስት አራተኛውን ማለትም ከ620 ሚሊዮን ብር በላይ መልሶ በእጁ ማስገባቱን ገልጿል።

አርብ መጋቢት 6/2016 ዓ.ም. ከምሽቱ ከሦስት ሰዓት ጀምሮ በባንኩ የገንዘብ ዝውውር ሥርዓት ላይ ባጋጠመው እና ለአምስት ሰዓታት በቆየው ክፍተት ምክንያት 801.4 ሚሊዮን ብር ከባንኩ ተወስዷል።

ባንኩ “ጤናማ ያልሆነ” ባለው ሂደት ውስጥ የራሳቸው ያልሆነ ገንዘብ በማንቀሳቀስ ተሳተፈዋል የተባሉ 15 ሺህ የሚሆኑ የሂሳብ ቁጥሮች መገኘታቸውን እና በዕለቱም 238,293 የገንዘብ ዝውውር መደረጉን የባንኩ ፕሬዝዳንት አሳውቀዋል።

ከዚህም ውስጥ ባለፉት አስር ቀናት አላግባብ ከባንኩ ከተወሰደው ብር 622.9 ሚሊዮን ብር የሚሆነውን ማስመለስ መቻሉን ባንኩ አስታውቋል።

ነገር ግን አሁንም 567 የሚሆኑ የባንኩ ደንበኞች ከ9.8 ሚሊዮን ብር በላይ ያልመለሱ ሲሆን፣ እነዚህንም ሰዎች ስማቸውን እና ፎቷቸውን ከዛሬ ጀምሮ ይፋ እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገልጿል።

ባንኩ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ላይ እንዳስታወቀው ተገቢ ባልሆነ መንገድ ገንዘብ ከባንኩ የወሰዱ ደንበኞች አስካለፈው ቅዳሜ ድረስ በፈቃደኝነት የሚመለስኡ ከሆነ በሕግ እንደማይጠይቃቸው አስታውቆ፤ ያልመለሱትን ግን ስማቸው እና ፎቷቸውን በመገናኛ ብዙኃን ይፋ በማድረግ በሕግ ተጠያቂ እንደሚያደርግ አስጠንቅቆ ነበር።

ከአስር ቀናት በፊት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያጋጠመውን ‘የሲስተም ችግር’ ተከትሎ የተወሰኑ አገልግሎቶቹ በጊዜያዊነት እንዲቆሙ ተደርገው ያጋጠመው ችግር እንዲስተካከል መደረጉ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ችግሩ ካጋጠመው በኋላ ምን ያህል ገንዘብ ወጪ እንደተደረገበት ከመግለጽ ተቆጥቦ ቢቆይም፣ የተለያዩ ምንጮች የገንዘቡን መጠን ከመቶ ሚሊዮኖች አስከ ቢሊዮኖች እንደሚደርስ ሲገልጹ ነበር።

በዚህ ክስተት ውስጥ ገንዘብ ከመክፈያ ማሽኖች በማውጣት እና ወደ ሌሎች ባንኮች በማዘዋወር ዋነኛ ተጠርጣሪዎች ሆነው ስማቸው ሲነሳ የነበሩት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ናቸው።

ከ80 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአገሪቱ ውስጥ በደንበኞች እና በቅርንጫፎች ብዛት እንዲሁም በገንዘብ አቅም ቀዳሚ የሆነ ግዙፍ መንግሥታዊ የፋይናንስ ተቋም ነው።

እንደ ስታቲስታ መረጃ ከሆነ በሃብት ብዛት በምሥራቅ አፍሪካ አገራት ውስጥ ከሚገኙ ባንኮች ቀዳሚ የሆነው ንግድ ባንክ እአአ 2022 አጠቃላይ ንብረቱ 23 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል።

አንድ ትሪሊዮን ብር ጠቅላላ ሃብት መሰብሰብ የቻለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአገሪቱ ዋነኛ ተቋማት ከሚባሉት ጥቂት ተቋማት መካከል አንዱ ነው።

በእአአ 2020/21 የበጀት ዓመት 20 ቢሊዮን ብር ትርፍ ያገኘው ባንኩ በዚሁ የበጀት ዓመት 735 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ማድረግ መቻሉን ይፋ አድርጎ ነበር።