በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር አወርቪን ማሲንጋ
የምስሉ መግለጫ,በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር አወርቪን ማሲንጋ

26 መጋቢት 2024, 11:04 EAT

ተሻሽሏል ከ 5 ሰአት በፊት

አሜሪካ በአማራ ክልል ተጎራባች ዞኖች ውስጥ በሚፈጸሙ ጥቃቶች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት እንደሚያሳስባት ገለጸች።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር አወርቪን ማሲንጋ በአማራ ክልል ውስጥ ባለፉት ሳምንታት የተፈጸሙትን ጥቃቶች በተመለከተ የአገራቸውን ስጋት በኤምባሲያቸው የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ይፋ አድርገዋል።

በዚህም “በአማራ ክልል የኦሮሞ ልዩ ዞን እና በሰሜን ሸዋ ዞኖች ውስጥ የሚፈጸሙ. . . ጥቃቶችን በተመለከተ የሚወጡ ዘገባዎች ዩናይትድ ስቴትስን ያሳስቧታል” ብለዋል አምባሳደሩ።

ከአንድ ሳምንት በፊት በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙት በተጎራባቾቹ የኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን እና በሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ ታጣቂዎች ለበርካታ ቀናት የቆየ ጥቃት መፈጸማቸው ሲዘገብ ነበር።

በዚህም በሰዎች እና በንብረት ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፣ ነዋሪዎችም ጥቃቱን በመሸሽ ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው ተነግሯል።

ይህንንም መሠረት አድርገው ነው በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ ክስተቱ መንግሥታቸውን እንዳሳሰበው የገለጹት።

በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙት ሁለቱ ዞኖች ውስጥ በተፈጸሙ ጥቃቶች “በሰላማዊ ሰዎች ላይ ግድያ፣ ጉዳት እና መፈናቀል” መድረሱን የሚገልጹ ሪፖርቶች አሳሳቢ መሆናቸውን ያመለከቱት አምባሳደሩ “ማንም ጥቃት በመፈጸም ነዋሪዎችን ከቤታቸው ማፈናቀል የለበትም” ብለዋል።

ጨምረውም ለሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ እንዲደረግ እና ለአገሪቱ “ውስብስብ ፖለቲካዊ እና የደኅንነት ቀውስ መፍትሄ ለመፈለግ ቁርጠኛነት” አስፈላጊ ነው በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

የአጣዬ እና ከሚሴ ካርታዎች

በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙት ሁለቱ ዞኖች ውስጥ ለተራዘመ ቀናት በተፈጸሙ ጥቃቶች ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ሲናገሩ የቆዩ ሲሆን፣ በርካቶች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

የአማራ ክልልም ሆነ የፌደራል መንግሥቱ በዞኖቹ ውስጥ ስለተፈጸሙት ጥቃቶች አስካሁን ያለው ነገር የለም።

ጥቃቶቹ በተባባሱበት ወቅት በዞኖቹ ውስጥ የተነሱ ናቸው የተባሉ እና በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሲጋሩ የነበሩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በርካታ ቤቶች በእሳት ሲቃጠሉ አሳይተዋል። ነገር ግን ቢቢሲ የቪዲዮዎቹን ትክክለኛነት ከገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም።

በዞኖቹ ውስጥ ከሳምንት በላይ ግጭቶች ሲካሄዱ እና ጥቃቶች ሲፈጸሙ ከቆዩ በኋላ፣ ባለፈው ሳምንት የአገር መከላከያ ሠራዊት በአካባቢዎቹ ተሰማርቷል።

ይህንንም ተከትሎ በዞኖቹ ውስጥ ሰላም ቢሰፍንም በስጋት ውስጥ መሆናቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል። ጥቃት ሸሽተው ወደ ገጠር ቀበሌዎች የሄዱ ሰዎችም ባሉበት መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ውስጥ ላለፉት ስምንት ወራት የዘለቀውን አለመረጋጋት ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተጣለ ሲሆን፣ ሁለቱ ዞኖች ውስጥ የሚገኘው ዋነኛው አውና ጎዳናም ለደኅንነት ሲባል በአካባቢው ኮማንድ ፖስት እንዲዘጋ ከተደረገ አንድ ወር አልፎታል።

በሁለቱ የአማራ ክልል ዞኖች ውስጥ ግጭቶች እና ጥቃቶች በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ሲሆን፣ ማኅበረሰቦቹ ለሚፈጸሙ ጥቃቶች አንዳቸው ሌላኛቸውን ተጠያቂ ሲያደርጉ ቆይተዋል።