የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህንጻ

ከ 9 ሰአት በፊት

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማይቱ የሚገኙ ዕድሮች እና የዕድር ምክር ቤቶች ተመዝግበው “ሕጋዊ እውቅና” እንዲያገኙ የሚያስገድድ መመሪያ አወጣ።

የከተማዋ የሴቶች፣ የህጻናት እና የማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ያወጣው ይህ መመሪያ የጸደቀው ባለፈው የካቲት ወር ሲሆን፣ መመሪያው ከዚህ በፊት የነበረውን የሰርኩላር የፈቃድ አሰጣጥ እንደሚሻር መግቢያው ላይ ሰፍሯል።

ከመመሪያው ዓላማዎች መካከል በከተማይቱ የሚገኙ ዕድሮች እና የዕድር ምክር ቤቶች ከወረዳ እስከ ከተማ በሁሉም ተዋረድ እንዲመዘግቡ እና ሕጋዊ እውቅና እንዲኖራቸው ማድረግ አንዱ ነው።

በቢሮው የማኅበራዊ ጥበቃ ማስተባባሪያ፣ መከታተያ ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ከማል በከተማዋ የሚገኙ ዕድሮች በዚህ መመሪያ መሠረት ተመዝግበው ሕጋዊ ዕውቅና ማግኘት እንዳለባቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አቶ መሐመድ “ማንኛውም አደረጃጃት ሕጋዊ መሠረት ይዞ ነው መሄድ ያለበት፤ ካልተመዘገበ ግን ህቡዕ አደረጃጀት ነው የሚሆነው” በማለት መመዝገብ ግዴታ መሆኑን አስረድተዋል።

አቶ መሐመድ አክለውም “እኛም ዕድሮችን [ካልተመዘገቡ] በልማት ለማሳተፍ እና ሌሎች ሥራዎችን እንዲሠሩ [ለማድረግም] አይታወቁም። ስለዚህ ተመዝገበው ሕጋዊ አሠራሩን ተከትለው መሄድ አለባቸው” ብለዋል።

“ሕጋዊ ሳይሆኑ እንዴት ሕዝብን ያሳትፋሉ?” የሚሉት አቶ መሐመድ፤ “አንደኛ በሕግ አሠራር ሕዝብ ቢሰበስብ ሕገ ወጥ ተብሎ ሊታሰሩም ይችላሉ። ሁለተኛ ሕጋዊ ካልሆነ ሕጋዊ [መሆን] ካልፈለገ እኛም ደግሞ እንዲበተኑ ነው የምንፈልገው” ሲሉ ያክላሉ።

የዕድሮች ምዝገባ ሂደትን በተመለከተ መመሪያው “ማንኛውም ዕድር የሕግ ሰውነትን ለማግኘት በሥራ አስፈፃሚ አባላቱ ወይም በሕጋዊ ወኪሎቹ አማካይነት በቢሮው የቀረበውን ቅጽ በመሙላት በዚህ መመሪያ መሠረት የተመለከቱትን ሰነዶች ለወረዳው ጽ/ቤት ያቀርባል” ሲል ያትታል።

ዕድሮች ከሚያቀርቧቸው ሰነዶች መካከል የዕድሩ አባላት ስም እና መኖሪያ፣ የዕድሩ ንብረት፣ የዕድሩ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ዝርዝር፣ የዕድሩ አድራሻ እንዲሁም የዕድሩ መተዳደሪያ ደንብ ናቸው።

ቀደም ሲል በራሳቸው ደንብ እና መመሪያ የተቋቋሙ ዕድሮች ወይም በየደረጃው የሚቋቋሙ የዕድር ምክር ቤቶች በመመሪያው መሠረት የሚመዘገቡበት ቋሚ ኦፊሴላዊ መዝገብ በቢሮው መቋቋሙን መመሪያው ላይ ሰፍሯል።

መመሪያው ያሰፈረው ሌላው ነገር ዕድሮች እንደ አስፈላጊነቱ በተዋረድ በወረዳ፣ በክፍለ ከተማ ወይም በከተማ ደረጃ ሊደራጁ እንደሚችሉ ነው። መመሪያው የዕድር ምክር ቤቶችም በተመሳሳይ “በወረዳ፣ በክፍለ ከተማ እና በከተማ ደረጃ ሊዋቀሩ ይችላሉ” ይላል።

ነገር ግን መመሪያው አክሎም “ወረዳ፣ ክፍለ ከተማ ወይም ከተማ ከአንድ በላይ የዕድር ምክር ቤት መኖር የለበትም” ሲል ያትታል።

ዕድሮችን ሕጋዊ ዕውቅና ከመስጠት ባለፈ መመሪያው ሌላም ዓላማ አለው።

“ዕድሮች ከቀብር እርዳታ ባለፈ አባሎቻቸው በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ከሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ እንዲያገኙ የሚያስችል አሠራር መዘርጋት” ሌላኛው የመመሪያው ዓላማ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም ዕድሮችን የማስተዳደር ኃላፊነት በአዋጅ ለቢሮው መሰጠቱን የሚያወሱት አቶ መሐመድ፤ ዕድሮችን ለማስተዳደር “በመመሪያ ማሰር አስፈላጊ ስለሆነ” መመሪያው መውጣቱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ መሐመድ የሚጠቅሱት አዋጅ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአስፈጻሚ አካላትን ለማቋቋም ከሁለት ዓመት በፊት የወጣ ነው።

አዋጁ፤ “በከተማው ውስጥ ያሉ መሠረታዊ ዕድር እና በየደረጃው የሚገኙት የዕድር ምክር ቤቶችን ይመዘግባል፣ ፈቃድ ይሰጣል፣ ባህላዊ እና ታሪካዊ ዕሴታቸውን ጠብቀው እንዲሄዱ ድጋፍ ያደርጋል፤ በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት ላይ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያጠናክሩ ያበረታታል” ሲል ይደነግጋል።

ከዚህ በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት መሥሪያ ቤት የአገልግሎት ክፍያ ደንብ ለመመሪያው መውጣት ሌላኛው ምክንያት ነው።

በዚህ ደንብ መሠረት ዕድሮች እና የዕድሮች ምክር ቤት ለምዝገባ አገልግሎት ክፍያዎችን ይፈጽማሉ። አዲስ የማኅበረሰብ እና የመሥሪያ ቤት ዕድሮች ምዝገባ ሲፈጸሙ ዕድሮች 350 ብር መክፈል ይኖርባቸዋል። ምዝገባ ለማሳደስ ደግሞ የክፍያ መጠኑ 300 ብር ነው።

መመሪያው ሕጋዊ እውቅና ያገኘ እና የተመዘገበ ማንኛውም ዕድር እንዲሁም የዕድር ምክር ቤት በየዓመቱ ምዝገባውን ማደስ እንዳለበት ደንግጓል። የምዝገባ ሰርተፊኬት ዕድሳት ከሐምሌ እስከ መስከረም መጨረሻ ባሉት ሦስት ወራት እንደሚካሄድም መመሪያው ላይ ሰፍሯል።

በአዲስ ከተማ በአካባቢ፣ በሥራ ቦታ እና በሌሎች ሁኔታዎች ተቋቋሙ ከሰባት ሺህ በላይ የሚሆኑ ዕድሮች የሚገኙ ሲሆን፣ በመመሪያው መሠረት ሁሉም ተመዝግበው ሕጋዊ ዕውቅና ማግኘት ይጠበቅባቸዋል።