March 26, 2024 – Konjit Sitotaw
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምን አለ ?
” … አንድ ሰው ያወጣው ትልቁ ገንዘብ 324 ሺህ ብር ነው ፤ 567 ደንበኞች ጠፍተዋል፤ የጠፉት ደንበኞች 9.8 ሚሊዮን ብር ነው ያወጡት ” – የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ መግለጫ ሰጥተው ነበር። በዚህም መግለጫቸው ባንኩ አጋጥሞት ከነበረው ችግር ጋር በተያያዘ እስካሁን ስለደረሰበት ደረጃ አብራርተዋል።
ምን አሉ ?
– ችግሩ የት ጋር ነው ያጋጠመው ? የሚለው ላይ በባለሙያ ጥናት እየተደረገ ነው ገና አላለቀም።
– አርብ መጋቢት 6 በተፈጠረው የሲስተም ችግር ከ801 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ተወስዶበት እንደነበርና 622 ሚሊዮን ያህሉን ወደ ባንኩ ተመላሽ ተደርጓል።
– ቀሪ 567 ግለሰቦች የወሰዱትን 9.8 ሚሊዮን ብር ማግኘት አልተቻለም።
– መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ምሽት ላይ ከ 3 ሰዓት ጀምሮ እስከ 8: 45 ድረስ ባለዉ ጊዜ ነው 25 ሺህ 761 ደንበኞች ብር 801.4 ሚሊዮን ነው የወሰዱት።
– ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ በሂደቱ ዉስጥ የተሳተፉ 15 ሺህ ያህል የሂሳብ ቁጥሮች ተገኝተዋል።
– የሲስተም ችግር በነበረበት በወቅት 25 ሺህ 761 ደንበኞች ግብይት ፈጽመዋል። በዚሁ ሰዓት ችግር ያለበት 238 ሺ 293 ጊዜ ግብይት ተፈጽሟል። አንድ ደንበኛ በአማካይ ከ9 ጊዜ በላይ ግብይት ፈፅሟል።
– በእለቱ አንድ ወይም ሁለት ግብይት የፈጸሙ ደንበኞች ጥርጣሬ ውስጥ አልገቡም። ያለ አግባብ የተወሰደ ገንዘብ ከሂሳባቸው ተቀናሽ ተደርጎ እንደሚመለስ ተደርጓል። በአካውንታቸው ላይ በቂ ገንዘብ ከነበራቸው 10 ሺህ ደንበኞች ላይ 44 ሚሊየን ብር ተመላሽ ተደርጓል።
– ቀሪዶቹ 15 ሺህ 8 ደንበኞች 207 ሺህ ግብይት ፈጽመዋል። እያንዳንዱ በዚያ ሌሊት በአማካይ 14 ጊዜ ግብይት ፈፅሟል።
– ሂሳባቸው ላይ ካለው ብር ወስደው ከነበሩ 15 ሺህ 8 ደንበኞች መካከል እስከ ትናንት ማታ ድረስ 372 ሚሊየን ብር ድረስ ተመላሽ ተደርጓል። ከእነዚህ ውስጥ 9 ሺህ 281 ሰዎች ሙሉ በሙሉ ያለባቸውን መክፈላቸውን 5 ሸህ 160 በከፊል መልሰው ቀሪውን ለመክፈል ቃል ገብተዋል።
– እስካሁን በድምሩ ሊጠፋ ከነበረው 800 ሚሊየን ብር ውስጥ 623 ሚሊየን ብር ተሰብስቧል። ቀሪውን የማስመለስ እና የማፈላለግ ስራ እየተከናወነ ነው።
– በህገ ወጥ መንገድ ገንዘብ ከወሰዱት መካከል 567 ደንበኞች ጠፍተዋል። ሙሉ አድራሻውን አለን፤ እየፈለግናቸው ነው። እነዚህ የጠፉት ደንበኞች የወሰዱት አጠቃላይ ገንዘብ 9.8 ሚሊየን ብር ነው። ከዚህም ውስጥ አንድ ሰው ያወጣው ትልቁ ገንዘብ 324 ሺህ ብር ነው።
– ገንዘብ ያልመለሱ ደንበኞች በባንኩ ቅርንጫፎች በያሉበት ስም ዝርዝራቸው ይለጠፋል። በባንኩ የማበራዊ ትስስር ገጾች ስማቸውን ይወጣል። ከዚህ ባልፉ ስማቸው ከነፎቶዋቸው ጭምር ይወጣል። በዚህም መመለስ ካልቻሉ በህግ ይጠየቃሉ።
– ያለአግባብ የተወሰደ አንድ ብር እንኳ ሳይቀር እናስመልሳለን።