ጥቃት የተፈጸመበት ሕንጻ
የምስሉ መግለጫ,ጥቃቱ የተፈጸመበት የሙዚቃ አዳራሽ በእሳት በተያያዘበት ጊዜ

ከ 5 ሰአት በፊት

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በሩሲያዋ ዋና ከተማ ሞስኮ ውስጥ በተፈጸመ የሽብር ጥቃት የአገሪቱ ባለሥልጣናት ጣታቸውን ዩክሬን ላይ ቢቀስሩም፤ አይኤስ-ኬ የተባለው ቡድን ግን ለጥቃቱ ኃላፊነቱን እንደሚውስድ ወዲያው ነበር ያሳወቀው።

አሜሪካም ጥቃቱን የእስላማዊ መንግሥት ቡድን ወይም አይኤስ ስለመፈጸሙ ምንም ጥርጣሬ የለኝም ብላለች።

ለዚህም የዚህ ቡድን አንድ ቅርንጫፍ የሆነው ኤይኤስ-ኬ በመባል የሚታወቀው ቡድን በሞስኮ የሙዚቃ አዳራሽ ውስጥ 140 ሰዎች ለተገደሉበት ጥቃት ተጠያቂ ሆኗል።

አይኤስ-ኬ ቡድን ማን ነው?

አይኤስ-ኬ ኢስላሚክ ስቴት-ኾራሳን የሚለውን የሚወክል ሲሆን፣ መላው ዓለም በሚገኙ መንግሥታት በአሸባሪነት የተፈጀው የኢስላሚክ ስቴት የአካባቢው አገራት ቅርንጫፍ ነው።

ይህ ቡድንም ትኩረቱ በአፍጋኒስታን፣ በኢራን፣ በፓኪስታን እና በመካከለኛው እሲያ ላይ ያደረገ ነው።

ኾራሳን የሚለውን መጠሪያውንም በቀጠናው ከነበረ እስላማዊ አስተዳደር የወሰደው ነው።

አይኤስ-ኬ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት በቀጠናው ሲንቀሳቀስ የቆየ ቢሆንም፣ ስሙ በስፋት መነሳት የጀመረው በቅርብ ወራት ውስጥ ነው። ቡድኑ እጅግ ጭካኔ በተሞላባቸው ጥቃቶች ሰሙ ገናና ሆኗል።

ቡድኑ ጥብቅ የሸሪዓ ሕግጋቶችን በመዘርጋት አህጉር አቀፍ አስተዳደር የመገንባት ሕልም አለው።

ቡድኑ ጥቃቶችን ፈጽሞ ያውቃል?

እአአ 2021 ላይ አሜሪካ ከአፍጋኒስታን ስትወጣ ትርምስ በተፈጠረበት ወቅት ቡድኑ በካቡል አየር ማረፊያ የቦምብ ጥቃት ፈጽሞ 170 የአፍጋኒስታን እና 13 የአሜሪካ ዜጎችን ገድሎ ነበር።

ከዚህ ጥቃት አንድ ዓመት በኋላ በካቡል የሚገኘውን የሩሲያ ኤምባሲ ዒላማ አድርጎ ስድስት ሰዎችን ገድሎ በርካቶችን አቁስሏል።

ከሁለት ወራት በፊት ደግሞ በኢራን አንድ የእምነት ቦታ ላይ ጥቃት ፈጽሞ ከ100 ያላነሱ ኢራናውያንን ገድሏል።

ቡድኑ ያለ አንዳች ርህራሄ የእናቶች እና ሕጻናት ሆስፒታል፣ አውቶብስ ማቆሚያዎች እና የፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት ይፈጽማል።

በሩሲያም ቢሆን ከአንድ ሳምንት በፊት ከፈጸመው ጥቃት ቀደም ብሎ ጥቂቶች ላይ ጉዳት ያደረሱ በርካታ አነስተኛ ጥቃቶችን ሲፈጽሟ ቆይቷል።

የሩሲያ ደኅንነት ቢሮ በዚህ የአውሮፓውያን ዓመት ቡድኑ ያሴራቸውን በርካታ ጥቃቶችን ማክሸፉን ሲገልጽ ቆይቷል።

ከካቡል ለመውጣት በተሰበሰቡ ሰዎች
የምስሉ መግለጫ,ቡድኑ የአሜሪካ ጦር አፍጋኒስታንን ሲለቅ ከካቡል ለመውጣት በተሰበሰቡ ሰዎች መካከል ጥቃት ፈጽሞ በርካቶችን ገድሏል

የሞስኮ ጥቃት ፈጻሚዎች እነማን ናቸው?

የሩሲያ መንግሥታዊ መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡት እንዳለው ከሆነ በሽብር ወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው አራቱም ግለሰቦች ከዚህ ቀደም የሶቪዬት ኅብረት አካል የነበረችው ታጃኪስታን ዜጎች ናቸው።

እነዚህ አራት ግለሰቦች ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት ምርመራ ሲደረግባቸው ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ከደረሰባቸው አካላዊ ጉዳት መረዳት ይቻላል።

ሩሲያ እነዚህን ተጠርጣሪዎች ለመመርመር እየተከተለች ባለው አካሄድ ላይ በርካቶች ጥያቄ እያነሱ ይገኛሉ።

መከራከሪያቸው ደግሞ ሰዎች ስቃያቸውን ለማስቆም ሲሉ የሚቀርቡባቸውን ክሶች በሙሉ ሊቀበሉ ስለሚችሉ የእምነት ክህደት ቃላቸው ትርጉም አልባ ሊሆን ይችላል የሚል ነው።

እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ጥቃቱን በማድረስ ተጠርጥረው ከተያዙት አንዱ ከሦስት ሳምንታት በፊት ጥቃት የተፈጸመበትን አካባቢን ሲቃኝ የሚያሳይ ምስል ወጥቷል።

ሌሎች ሪፖርቶች ደግሞ ከጥቃት አድራሾቹ መካከል ሁለቱ ሩሲያ የገቡት ከጥቂት ቀናት በፊት ነው።

ሩሲያን ለምን ዒላማ አደረጉ?

ይህ የአይኤስ ቡድን ቅርንጫፍ ከቀናት በፊት የሞስኮ የሙዚቃ አዳራሽን ለምን ዒላማ እንዳደረገ የበርካቶች ጥያቄ ነው።

ለዚህም የተለያዩ ወገኖች የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉ ይገልጻሉ።

አይኤስ-ኬ አብዛኛውን ዓለም ጠላት አድርጎ ነው የሚወስደው።

ሩሲያ ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ፣ ከእስራኤል፣ ከአይሁዶች፣ ከክርስቲያኖች፣ ከሺዓ ሙስሊሞች እና ከታሊባን ጋር ቀንደኛ ጥላት ተብላ ተዘርዝራለች።

በቅርቡ ሩሲያ በሶሪያው የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ መሆኗ በቡድኑ ጥርስ እንዲነከስባት ያደረገ ሌላው ምክንያት ሆኗል።

ሞስኮ ሕዝባዊ አመጽ የተነሳባቸውን ፕሬዝዳንት ባሻር አል አሳድን ደግፋ ባካሄደቻቸው በርካታ የአየር ጥቃቶች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የኢስላሚክ ስቴት እና አል-ቃይዳ ተዋጊዎችን ገድላለች።

በአፍጋኒስታንም አይኤስ-ኬ ሩሲያን የታሊባን አጋር አድርጎ ይወስዳታል። ለዚህም ነበር እአአ 2022 ላይ አይኤስ-ኬ ካቡል በሚገኘው ኤምባሲዋ ላይ ጥቃት የፈጸመው።

አይኤስ-ኬ ሩሲያ የክርስቲያን አገር ነች ብሎም ያምናል።

የታጃኪስታን እና የሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ዜጎች የሆኑ ስደተኞች በሩሲያ መገፋት ይደርስባቸዋል መባሉም ሩሲያ እንደጠላት እንድትታይ የሚያደርገው ምክንያት ነው።

በመጨረሻም ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ጦርነት ውስጥ መግባቷን አይኤስ-ኬ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ጥቃት ሊያደርስ ይችላል።

የሩሲያ ፖሊስ

ስለሞስኮ ጥቃት እስካሁን የሚታወቀው. . . ?

137 ሰዎች ሞት ስለገደው እና ከ140 ሰዎች በላይ ለጉዳት ስለዳረገው ጥቃት ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉ።

ለምሳሌ ጥቃት አድራሾቹ ለአንድ ሰዓት ያክል ምንም ዓይነት መቻኮል ሳይታይባቸው እና የሩሲያ ፖሊስ እርምጃ ሳይወስድ ያን ያህል ጉዳት እያደረሱ እንዴት ሊቆዩ ቻሉ? የሚለው ቀዳሚው ነው።

ፖሊስ እና የደኅንነት አባላት በየትኛውም ሰዓት በፍጥነት ምላሽ የሚሰጡባት አገር በምትባለው ሩሲያ፣ ጥቃት አድራሾቹ ጥቃቱን ሲፈጽሙ ፖሊስ በፍጥነት ሊመጣባቸው እንደማይችል የተረዱ ይመስላሉ።

ሌላ መመለስ ያለበት ጥቃት ፈጻሚዎቹ የታጠቁት መሳሪያ ነው። የጦር መሳሪያቸው ዘመናዊ አውቶማቲክ ሲሆን፣ እነዚህን መሳሪያዎች ከየት አመጡት? እንዴትስ አድርገው የሙዚቃ ድግሱ ወደሚካሄድበት አዳራሽ አስገቡ?

ሌላ መታየት ያለበት ጉዳይ ተጠርጣሪዎች የተያዙበት ፍጥነት ነው። ከ20 ዓመታት ወዲህ በሩሲያ ታሪክ የከፋ የተባለውን ጥቃት ቀድሞ ማስቆም ያልቻለው ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን እንዴት በፍጥነት በሕይወት ሊይዛቸው ቻለ? የሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ የሚሹ ናቸው።

በዩክሬን ላይ በከፈተችው ወረራ ለሁለት ዓመታት በዘለቀ ጦርነት ውስጥ የምትገኘው ሩሲያ፣ በአይኤስ-ኬ አባላት በተፈጸመባት ጥቃት ውስጥ የዩክሬን እጅ አለበት በሚል ከሳለች።

ይህም በዩክሬን ላይ በቀጣይ ለምታካሂደው መጠነ ሰፊ ጥቃት ሰበብ ሊሆናት ይችላል የሚሉ አሉ።

በተጨማሪም ከአገሪቱ የደኅንነት ምክር ቤት አባላት ጋር የመከሩት ፕሬዝዳንት ፑቲን በቡድኑ ላይ ከባድ ጉዳትን የሚያስከትል የበቀል ጥቃትን እያቀዱለት ሳይሆን እንደማይቀር ይታመናል።