
ከ 5 ሰአት በፊት
የአሜሪካን ገመና ለዓለም ይፋ ያደረገው ዊክሊክስ የተሰኘው ድረ ገጽ መሥራች ጁሊያን አሳንጅ ከሰሞኑ የበርካታ መገናኛ ብዙኃን ዋነኛ ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጁሊያን አሳንጅ ለአሜሪካ ተላልፎ ይሰጥ አይሰጥ በሚለው ጉዳይ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጥበትን ቀን ወደ ግንቦት ወር ገፍቶታል።
ከአውሮፓውያኑ 2019 ጀምሮ በዩናይትድ ኪንግደም እስር ቤት የሚገኘው አሳንጅ ምሥጢራዊ ወታደራዊ መረጃዎችን ለዓለም ይፋ በማድረግ አሜሪካ በጥብቅ ትፈልገዋለች።
እነዚህን መረጃዎች ይፋ ያደረገው በአውሮፓውያኑ 2010 እና 2011 ነው።
ጁሊያን አሳንጅ ማን ነው? ዊክሊክስስ ምንድን ነው?
አሳንጄ ገና በታዳጊነቱ ነው በኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ በነበረው ጥልቅ ዕውቀት ታዋቂነትን ማትረፍ የቻለው።
በአውሮፓውያኑ 1995 ከመረጃ ጠለፋ ጋር በተያያዘ በትውልድ አገሩ አውስትራሊያ ፍርድ ቤት ቀርቦ ነበር።
ድጋሚ ይህንን ላለማድረግ ቃል በመግባቱም ከእስር ማምለጥ ቻለ።
በቀጣዩ ዓመት፣ በ2006 አሳንጅ የዊክሊከስን ድረ ገጽ መሠረተ።
ከጦርነት፣ ከስለላ እና ከሙስና ጋር የተያያዙ ምሥጢራዊ እንዲሁም መንግሥታዊ ሪፖርቶችን ጨምሮ ከአስር ሚሊዮን በላይ ሰነዶችን ለዓለም ይፋ አድርጓል።
የአሜሪካ ወታደራዊ ሄሊኮፕተር በኢራቅ መዲና ባግዳድ ሲቪሎችን ሲገድሉ የሚያሳይ ቪዲዮ ይፋ ያደረገው ከአስራ አራት ዓመት በፊት ነበር።
በተጨማሪም በቀድሞ የአሜሪካ ጦር የስለላ ተንታኝ ቼልሲ ማኒንግ የተሰጡትን በሺዎች የሚቆጠሩ ምሥጢራዊ ሰነዶችን አሳትሟል።
በእነዚህ ሰነዶችም መሠረት የአሜሪካ ሠራዊት በአፍጋኒስታን ጦርነት ወቅት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎችን እንደገደለ ይጠቁማሉ። እነዚህ ግድያዎችም ሪፖርት እንዳልተደረጉ ሰነዶቹ ይገልጻሉ።
- ጁሊያን አሳንጅ በድብቅ የወለዳቸው ሁለት ልጆች “ተገኙ”13 ሚያዚያ 2020
- የዊክሊክስ መስራች ጁሊያን አሳንጄ ለአሜሪካ ተላልፎ ሊሰጥ እንደሚችል ተገለጸ17 ሰኔ 2022

የአሜሪካ መንግሥት ለዊክሊክስ ምን ምላሽ ነበረው?
የአሜሪካ የፍትህ መሥሪያ ቤት ሾልከው የወጡትን እነዚህን መረጃዎች “በአሜሪካ ታሪክ ከተፈጸሙት ምሥጢራዊ መረጃዎችን አደጋ ላይ ከጣሉት መካከል አንዱ ነው” ሲል ነበር በአውሮፓውያኑ 2019 የገለጸው።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት ጠበቆች መረጃው መታተሙ በተለይም ስማቸው ይፋ የተደረጉ አፍጋኒስታናውያን እና ኢራቃውያንን “ከፍተኛ ጉዳት አደጋ ላይ የሚጥላቸው ሲሆን አልፎ ተርፎም ለሞት ሊዳረጉ” እንደሚችሉም ተናግረዋል።
አሳንጅ በበኩሉ ይፋ ያደረጋቸው ሰነዶች በአሜሪካ የጦር ኃይል የሚፈጽማቸውን የከፉ በደሎች እና ግፎች ያጋለጡ እንደሆነ እና በእርሱም ላይ የተመሠረተው ክስ ፖለቲካዊ ነው ሲል አጥብቆ ይከራከራል።
ምሥጢራዊ ሰነዶችን ለማግኘት በሚል ወታደራዊ የመረጃ ቋቶችን ለመስበር የማሴር ክስን ጨምሮ በ18 ወንጀሎች ተከሷል። አሜሪካ አሳንጅ ተላልፎ እንዲሰጣት የአሜሪካ ባለሥልጣናት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረጉ ይገኛሉ።
አሳንጅ በአሜሪካ የጥፋተኝነት ብይን ከተላለፈበት እስከ 175 ዓመት እስራት እንደሚጠብቀው ጠበቆቹ ይናገራሉ።
ሆኖም የአሜሪካ መንግሥት በበኩሉ ከአራት እስከ ስድስት ዓመት የሚደርስ እስር ሊሆን እንደሚችል አስታውቋል።
የአሳንጅ ተላልፎ የመስጠት ሂደት
አሜሪካ በአውሮፓውያኑ 2019 አሳንጅ ተላልፎ ይሰጠኝ በማለት ያቀረበችው ጥያቄ ከተከታታይ ችሎቶች በኋላ እንዲቀርብ ፍቃድ አግኝቷል።
ነገር ግን አሳንጅ ይህ ውሳኔ እንዲቀለበስ ለበርካታ ዓመታት ሲታገል ቆይቷል።
ከዚህ ጋር ባልተያያዘ አሳንጅ የዋስትና ሁኔታዎቹን በመጣሱ በለንደን ከፍተኛ ጥበቃ ወደሚደረግለት የቤልማርሽ እስር ቤት ተልኳል።
አሳንጅ ከዚህ ቀደም ካለው ከእስር የማምለጥ ታሪክ ጋር ተያይዞም ለአሜሪካ ተላልፎ የመስጠቱ ጉዳይ የሚታይበት የፍርድ ሂደት እስኪያልቅ ድረስም በዚሁ እስር ቤት እንዲቆይ ተደርጓል።
በአውሮፓውያኑ 2021 የዩናይትድ ኪንግደም ፍርድ ቤት ለአሜሪካ ተላልፎ እንዲሰጥ በይኗል። ፍርድ ቤቱ የአሳንጅ የአዕምሮ ጤንነት ከመድከሙ ጋር ተያይዞ ሕይወቱን በአሜሪካ እስር ቤት ሊያጠፋ ይችላል የሚለውን መቃወሚያ ውድቅ አድርጎታል።
በአውሮፓውያኑ 2022 የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይህንኑ ውሳኔ በማጽናት የዚያን ጊዜ የአገር ውስጥ ጉዳይ ኃላፊ ፕሪቲ ፓቴል ተላልፎ የመሰጠት ትዕዛዙን አረጋግጠዋል።
አሳንጅም የባለሥልጣኗ ውሳኔ እንደገና እንዲታይለት እና የመጀመሪያው የ2021 የፍርድ ቤቱ ተላልፎ ይሰጥ ውሳኔን ለመቃወም ወደ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ተመልሷል።
ደጋፊዎቹ ይህ የመጨረሻው የፍርድ ሂደት ሊሆን እንደሚችልም እየተናገሩት።
የአሳንጅ ጠበቆች የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት የደንበኛቸውን ጉዳይ እንዲመለከተው ጠይቀው የነበረ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ግን ጉዳዩን ሳይሰማ ውድቅ አድርጎታል።

አሳንጅ በኢኳዶር ኤምባሲ ለምን ኖረ?
አሳንጅ ስዊድን በነበረበት ወቅት አንዲት ሴትን በመድፈር እና ሌላኛዋ ላይ ጥቃት አድርሷል በሚል ክስ በስዊድን ባለሥልጣናት በአውሮፓውያኑ 2010 የእስር ማዘዣ አውጥተውበት ነበር።
አሳንጅ የቀረቡበትን ክሶች “መሠረተ ቢስ” ናቸው ሲልም አጣጥሏቸዋል።
በወቅቱ በዩናይትድ ኪንግደም በቁጥጥር ስር ውሎ በዋስ ወጥቶ የነበረው አሳንጅ፣ ተላልፎ እንዲሰጣት ስዊድን ጠየቀች።
ከሁለት ዓመታት የፍርድ ሂደት በኋላም በአውሮፓውያኑ 2012 የዩኬ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አሳንጅ ለጥያቄ ለስዊድን ተላልፎ እንዲሰጥ ወሰነ።
ሆኖም የስዊድን የፍርድ ሂደት ወደ አሜሪካ ተላልፎ እንዲሰጥ ሊያደርገኝ ይችላል በማለትም አሳንጅ ሸሽቶ በዩኬ በሚገኘው የኢኳዶር ኤምባሲ የፖለቲካ ጥገኝነት ጠየቀ።
ጥያቄውም በወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት በነበሩት ራፋኤል ኩርያ ተቀባይነት አገኘ።
አሳንጅ በኤምባሲው ውስጥ ለሰባት ዓመታት የኖረ ሲሆን፣ ታዋቂዋ ዘፋኝ ሌዲ ጋጋን እና ተዋናይት ፓምላ አንደርሰንን ጨምሮ በርካታ ታዋቂ ሰዎች አዘውትረው ይጎበኙት ነበር።
ሆኖም በአውሮፓውያኑ 2019 የኢኳዶሩ አዲስ ፕሬዝዳንት ሌኒን ሞሪኖ አሳንጅ “ጨዋነት የጎደለው እንዲሁም የጠበኝነት ባህርይ” አለው በሚል ምክንያት ኤምባሲውን ለቆ እንዲወጣ ትዕዛዝ ሰጡ።
አሳንጄ በኤምባሲው ውስጥ በእንግሊዝ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ለስዊድን ተላልፎ እንዲሰጥ ለፍርድ ቤት እጁን ባለመስጠቱ የዋስ መብቱን ጥሷል በሚል ችሎት ቀረበ። በዚህም የ50 ሳምንታት እስር ተፈረደበት።
በኅዳር ወር 2019 የስዊድን ባለሥልጣናት ጁሊያን አሳንጅ የተጠረጠረበት ወንጀል ረጅም ጊዜ አልፎታል በሚልም ያቀረቡትን ክስ አቋረጡ።

የጁሊያን አሳንጅ ባለቤት ስቴላ አሳንጅ ማን ናት?
አሳንጅ የረዥም ጊዜ አጋሩን ጠበቃ ከሆነችው ስቴላ ሞሪስ ጋር የተጋባው በአውሮፓውያኑ 2022 በቤልማርሽ እስር ቤት ውስጥ ሳለ ነው።
ጥንዶቹ ግንኙነታቸውን የጀመሩት በአውሮፓውያኑ 2015 ሲሆን፣ ሁለት ልጆችን አፍርተዋል። ልጆቹ የተወለዱት በኢኳዶር ኤምባሲ ውስጥ በሚኖርበት ወቅት ነበር።
ስቴላ ለሰርጓ የለበሰችው ቬሎም አሳንጄ ተላልፎ እንዳይሰጥ በመቃወም ዘመቻ ሲያካሂድ በነበረው ዴም ቪቪን ዌስትውድ ዲዛይን የተደረገ ነበር።
በሰርግ ሥነ ሥርዓቱ ላይም ሁለቱ ልጆቻቸው፣ የአሳንጅ አባት እና ወንድሙ ታድመው ነበር።