ጋዛ

ከ 2 ሰአት በፊት

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያ እስራኤል ጋዛ ላይ “የዘር ማጥፋት ወንጀል” እንደፈጸመች አምናለሁ ሲሉ ተናገሩ።

በእስራኤል ቁጥጥር ውስጥ በሚገኘው የፍልስጤም ግዛት ውስጥ የድርጅቱ የሰብአዊ መብቶች ባለሙያ የሆኑት ፍራንቼስካ አልባኒዚ ትላንት ማክሰኞ በጄኔቭ ተግኝተው ሪፖርት አቅርበዋል።

ፍራንቼስካ በሪፖርታቸው እስራኤል በጋዛ በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽማለች ማለት የሚያስችል ማሳያዎች አሉ ብለዋል።

ይህ ሪፖርተር ለተባበሩት መንግሥታት አባል አገራት የቀረበው እስራኤል ጦርንቱን እንድታቆም አሊያም ለሲቪል ሰዎች ጥበቃ እንድታደርግ ዓለም አቀፍ ጫናዎች በበረታበት ወቅት ነው።

እስራኤል ይህን ሪፖርት ውድቅ አድርጋዋለች።

እስራኤል ፍራንቼስካ ሪፖርታቸውን ለማቅረብ ወደ አዳራሽ ከመግባታቸው አስቀድሞ ነበር የሪፖርቱን ግኝት ውድቅ ያደረገችው።

ፍራንቼስካ ሐማስ ባለፈው መስከረም በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ድንገተኛ ጥቃት አውግዘው በጥቃቱ ወቅት በሐማስ የታገቱ ሰዎች ነጻ እንዲወጡ ሲጠይቁ ቆይተዋል።

በትናንቱ ሪፖርታቸውም “ባለፈው መስከረም ሐማስ እና ሌሎች የፍልስጤም ታጣቂዎች የፈጸሙትን ወንጀል አጥብቄ አወግዛለሁ” ብለዋል።

የዘር ማጥፋትን ሕጋዊ ትርጉም ያቀረቡት የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዋ፤ እስራኤል የዘር ማጥፋት ፈጽማለች ለማለት የሚያስችል ሁኔታዎች አሉ ብለዋል።

እስራኤል ፍልስጤማውያንን እንደ ቡድን በሙሉ ወይም በከፊል የማጥፋት ፍላጎት አሳይታለች ካሉ በኋላ ይህ የዘር ማጥፋት ትርጉሜ ስምምነትን ያሟላል ሲሉ ገልጸዋል።

ከስምምነቱም ሦስት ነገሮችን በማንሳት እስራኤል ፍልስጤም ላይ የዘር ማጥፋት ፈጽማለች ለማለት ይችላል ብለዋል።

እነሱም የማህበረሰቡን አባላት መግደል፣ የማህብረሰቡ አባላት ላይ ከባድ የአእምሮ እና የአካል ጉዳት ማድረስ እንዲሁም በተጠና ሁኔታ ሆን ብሎ የቡድንን በሕይወት የመኖር ሁኔታ በከፊል ወይም በሙሉ ለማወክ መሞከር ናቸው።

እንደ ጋዛ የጤና ሚኒስቴር መረጃ ከሆነ በእስራኤል ጥቃት የተገደሉ ሰዎች ቁጠር ከ32 ሺህ በላይ ደርሷል። በእስራኤል የአየር እና የምድር ጥቃት መሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት ከመድረሱም በላይ በሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ላይ ገደብ ተጥሏል።

የፍልስጤም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ማዕከል ሪፖርቱን ደግፎታል።

በታቃራኒው የእስራኤል ዲፕሎማቶች በሪፖርቱ ክፉኛ ተቆጥተዋል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ የመንግሥታቱ ድርጀት የጸጥታው ምክር ቤት በጋዛ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ድምጽ ሰጥተዋል። ይህ ደግሞ አባል አገራት እስራኤል ተኩስ እንድታቆም የሚያደረጉት ጫና እንደበረታ ማሳያ ሆኗል።

በርካታ የመንግሥታቱ ድርጅት መስሪያ ቤቶች በጋዛ ያለው ሁኔታ እጀግ አሳሳቢ ወደ ሆነ ሁታ አየተሸጋገረ እንደሆነ ተናግረዋል።