
ከ 4 ሰአት በፊት
የናይጄሪያ ፍርድ ቤት ፍቅረኛውን የገደለው ቻይናዊ ነጋዴ በሞት እንዲቀጣ ውሳኔ አስተላልፏል።
ቻይናዊው ኡሙ ኩልቱም ሳኒ የተሰኘች ናይጄሪያዊት ፍቅረኛውን በእአአ 2022 መግደሉን ተከትሎ ነው ፍርድ ቤት የሞት ፍርድ ያስተላለፈበት።
ፍራንክ ጌንግ ኩዋሮንግ ፍቅረኛውን በስለት በተደጋጋሚ በመውጋት ሕይወቷ እንዲያልፍ አድርጓል።
የ22 ዓመቷ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ መገደል በናይጄሪያ ትልቅ መነጋገሪያ መሆኑን ተከትሎ የፍርድ ውሎው ትኩረት አግኝቶ ነበር።
በናይጄሪያ የሞት ቅጣት እምብዛም ነው። ኩዋሮንግ ይግባኝ ለመጠየቀ የ90 ቀናት ዕድሜ ተሰጥቶታል።
ቤተሰቡን ወክሎ አስተያየት የሰጠው የሟች ወንድም ሳዲቅ ሳኒ፤ ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘው ቻይናዊ በስቅላት እንዲቀጣ መወሰኑ ፍትሐዊ ነው ብሏል።
ወንድሟ እንደሚለው ማንኛውም ነብስ ያጠፋ ሰው በሞት ቅጣት ሊቀጣ ይገባል።
“ይህንን ቀን ስላሳየን ፈጣሪነን እናመሰግነዋለን። የእህቴ ነብስ በሰላም ያርፍ ዘንድ እፀልያለሁ” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
የግብርና ትምህርት እያጠናች የነበረችው ወጣት ሩህሩህ እና ተጫዋች ነበረች ሲሉ ቤተሰቦቿ ያስታውሷታል።
- በሞስኮ ላይ ጥቃት ፈጽሞ በርካቶችን የገደለው አይኤስ-ኬ የተባለው ቡድን ማን ነው?ከ 5 ሰአት በፊት
- የአሜሪካን ገመና ለዓለም ይፋ ያደረገው ጁሊያን አሳንጅ ማን ነው?ከ 5 ሰአት በፊት
- በምሥራቅ እና ምዕራብ አርሲ ዞኖች ታጣቂዎች አገልግጋዮችን እና ምዕመናንን መግደላቸው ተነገረከ 5 ሰአት በፊት
የ49 ዓመቱ ኩዋሮንግ እና ሳኒ ከአውሮፓውያኑ 2020 ጀምሮ በፍቅር ግንኙነት አብረው ቆይተዋል።
ቻይናዊው ግለሰብ ናይጄሪያ ውስጥ በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ተሰማርቶ ነው የሚሠራው።
መስከረም 2022 ግድያው ከተፈፀመ በኋላ የሳኒ ቤተሰብ ወዳጅ የሆነው አሕመድ አብዱላሂ የነበረውን ክስተት ያስታውሳል።
ወደ ቤተሰቦቿ ቤት ሲመጣ “በርካታ ሰዎች ከቤቱ ውጭ ተሰባስበው ተመለከትኩ” ይላል።
“ያኔ ነው የሆነ መጥፎ ነገር እንደተከሰተ የጠረጠርኩት። ጌንግ ፍቅረኛዋ ነበር። ከዚያች ቀን በፊት ከቤተሰቦቿ ጋር መልካም ግንኙነት ነበረው” ይላል።
“ከግድያው በፊት በመሃላቸው አለመስማማት ነበር። እሷ በግንኙነቱ ደስተኛ አልነበረችም። እሱ ደግሞ ሊተዋት አልፈለገም።”
ጎረቤቶች እንደሚሉት በግድያው ቀን ኩዋሮንግ የሳኒ ቤተሰብ ግቢን በኃይለኛው ሲያንኳኳ ተሰምቷል።
የሳኒ እናት በሩን ስትከፍት እሷን ገፍቶ ወደ ውስጥ በመግባት የሳኒ ክፍል ዘልቆ ከውስጥ ዘጋው።
ከሳኒ ክፍል የሚወጣው ጩኸትና ለቅሶን ሰምተው ቤተሰቦቿ ክፍሉን ሰብረወ ቢገቡም በርካታ ጊዜ በስለት በመወጋቷ ሊያድኗት አልቻሉም።
ሳኒ ወደ ሆስፒታል ከተወሰደች በኋላ ነው ሕይወቷ ያለፈው።
ናይጄሪያ በአሁኑ ወቅት 3400 የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ወንጀለኞች አሏት። ለመጨረሻ ጊዜ የሞት ፍርድ የተፈፀመው ግን በአውሮፓውያኑ 2012 ነበር።