የፈረሰው ድልድይ

ከ 1 ሰአት በፊት

በአሜሪካዋ ቦልቲሞር ከተማ የሚገኘው ፍራንሲስ ስኮት ኪይ የተባለው ታዋቂ ድልድይ በመርከብ ተገጭቶ መፍረሱን ተከትሎ ስድስት ሰዎች በመጥፋታቸው ሳይሞቱ እንዳለቀረ ተነገረ።

የሰዎቹን አስከሬን ለማውጣት ጥረት እየተደረገ መሆኑም ተገልጿል።

2.6 ኪሜ የሚረዝመው ድልድይ ምሰሶ በመርከብ ተገጭቶ የተወሰነው ክፍሉ ሲፈርስ በርካታ መኪኖች እያቋረጡ ነበር ተብሏል።

መርከቡ “ሞተሩ ችግር እንደገጠመው” እና ከግጭቱ በፊት ይህንን አሳውቆ ነበር ሲሉ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

የጠፉትን ሰዎች ለመፈለግ ጀልባዎች እና ሄሊኮፕተሮች ተሰማርተዋል። ሁለት ሰዎች ከውሃው የወጡ ሲሆን፣ አንደኛው ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል።

የአሜሪካ የባሕር ጠረፍ ጥበቃ ባልደረባ የሆኑት ሪር አድሚራል ሻነን ግልሪዝ ከውሃው ቅዝቃዜ እና ካለፉት ሰዓታት አንጻር ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተናግረዋል።

ሰዎቹ በድልድዩ ላይ የጥገና ሥራ የሚያከናውኑ ሠራተኞች መሆናቸውን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

አደጋውን ያደረሰው ዳሊ የተሰኘው መርከብ ባለቤትነቱ የሲንጋፖር ሲሆን 47 ዓመት ያስቆጠረውን ድልድይ ምሰሶ ገጭቶ እንዲፈረስ አድርጎታል።

መርከቡ ወደ ስሪላንካ መዲና ኮሎምቦ ለማምራት ከብሪዝ ወደብ ቢነሳም ከ45 ደቂቃ በኋላ ነበር አደጋውን ያደረሰው።

መርከቡ ከወደቡ ብዙም ሳይርቅ የሚያንቀሳቅሰውን ኃይል እንዳጣ የአሜሪካ ፌደራል ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

የመርከቡ ሠራተኞች ግጭት ሊኖር እንደሚችል ለሜሪላንድ የትራንስፖርት ባለሥልጣናት ማስጠንቀቃቸው ተዘግቧል።

የነፍስ አድን ሠራተኞች
የምስሉ መግለጫ,የነፍስ አድን ሠራተኞች

የሜሪላንድ አስተዳዳሪ ዌስ ሙር “ሠራተኞቹ የኃይል ችግር እንደገጠማቸው” ማሳወቃቸውን ገልጸው በኋላም የኃይል እጥረት ገጥሟቸው ከድልድዩ አንዱ ምሰሶ ጋር መጋጨቱን አክለዋል።

የድልድዩን መፍረስ ተከትሎም በርካታ መኪናዎች ውሃ ውስጥ መውደቃቸውን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

የባልቲሞር እሳት አደጋ፣ የአሜሪካ የባሕር ጠረፍ ጥበቃ እና ሌሎች የሜሪላንድ ተቋማት በአሰሳው ሥራ ተሳትፈዋል።

ውሃው ላይ የሚፈጠረው ማዕበል የነፍስ አድን ሥራው ላይ እንቅፋት መፍጠሩንም አክለዋል፤ ሌሎች ባለሥልጣናት ደግሞ ያለው ቀዝቀዛ አየር ሁኔታም መስናክል መሆኑን ጠቁመዋል።

የቦልቲሞር ከንቲባ ብራንዳን ስኮት ክስተቱን “ሊታሰብ የማይችል አደጋ” በማለት ትኩረት ሁሉ “በውሃ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን፣ ሕይወትን፣ ነፍስን. . . ወደ ማዳን መሸጋገሩን” አስታውቀዋል።

የሜሪላንድ ትራንስፖርት ኃላፊ ፖል ዋይፌልድ በበኩላቸው በድልድዩ ላይ የደረሰውን ጉዳት ለማጥናት መሐንዲሶች በቦታው መሠማራተቸውን ታነግረዋል።

ሲነርጂ ማሪን ግሩፕ የተሰኘው መርከብ ኩባንያ ለቢቢሲ እንዳስታወቀው በመርከቡ ላይ 22 ሠራተኞች ነበሩ። ሁሉም የመርከቡ ሠራተኞች ሕንዳውያን ሲሆኑ፣ እንደ ወደብ ፓይለት የሚያገለግሉ ሁለት የቦልቲሞር ነዋሪዎችም አብረዋቸው ነበሩ። ሠራተኞቹ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አለመድረሱም ተገልጿል።

መርከብ ላይ ፓይለት የሚባሉት የወደቡን አካባቢ የሚያውቁ እና መርከቡን ወደ ወደቡ የሚያስገቡ እና የሚያስወጡ ባለሙያዎች ናቸው።

የአደጋው ትክክለኛ ምክንያት እየተጣራ መሆኑን ኩባንያው ጠቅሶ ከፌደራል ባለሥልጣናት ጋር “በመተባበር ላይ መሆኑን” አክሏል።

ግዙፉ የመርከብ ኩባንያ ማርስክ መርከቧን በመከራየት የደንበኞቿን ንብረት እየጫነች ነበር ብሏል።

“በዖልቲሞር በተፈጠረው ነገር በጣምአዝነናል። ለተጎዱት በሙሉ ሐዘናችንን እንገልጻለን” ሲል መግለጫ አውጥቷል። በመርከቧ ላይ የማርስክ ቡድን ሠራተኞች አልነበሩም ተብሏል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በፍጥነት ወደ ቦልቲሞር እንደሚጓዙ እና የፍለጋ እንዲሁም የነፍስ ማዳን ሥራዎች ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።

“ወደቡን ለመክፈት እና በተቻለ ፍጥነት ድልድዩን እንደገና ለመገንባት ያለ ኃይል በሙሉ እንዲንቀሳቅስ መመሪያ አስተላልፌያለሁ” ብለዋል።

አደጋው በአጋጣሚ የተፈጠረ መሆኑን እና የፌደራል መንግሥት ለድልድዩ አጠቃላይ ወጪ እንደሚከፍል ተናግረዋል። ገንዘቡ በኮንግረስ አባላት መጽደቅ አለበትም ሲሉም አክለዋል።