
ከ 1 ሰአት በፊት
የኡጋንዳ መንግሥት ሁሉም የመንግሥት ሠራተኞች በሳምንት ለሁለት ሰዓታት ያህል አካላዊ እንቅስቃሴዎችን እንዲያደርጉ የሚያዝ መመሪያ አወጣ።
ይህ የመንግሥት መመሪያ የወጣው በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የመንግሥት ሠራተኞች የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በማድረግ ክብደታቸውን ተቆጣጥረው ጤናማ እንዲሆኑ ዕድል ለመፍጠር መሆኑ ተነግሯል።
መመሪያው ይፋ የሆነው የአገሪቱ የመንግሥት ሠራተኞች አስተዳደር መሥሪያ ቤት ኃላፊ በመሆኑት ሉሲ ናኪዮቤ ተፈርሞ ለሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በተሰራጨ ደብዳቤ አማካይነት ነው።
ኃላፊዋ በደብዳቤያቸው የመንግሥት ሠራተኞች በሳምንት ለሁለት ሰዓታት የሚያደርጉት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አማካይነት “በሽታዎችን በመከላከል የሠራተኞችን ሕይወት ለመታደግ ይረዳል” ብለዋል።
የኡጋንዳ መንግሥት በበኩሉ ይህንን መመሪያ በተመለከተ ኤክስ ላይ ባሰራጨው መልዕክት ሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች “በአኗኗር ዘይቤ ምክንያት እየጨመሩ ያሉ በሽታዎችን ለመቆጣጠር” የስፖርታዊ እንቅስቃሴ ፕሮግራሞች እንዲያወጡ መታዘዛቸውን ገልጿል።
በርካታ ኡጋንዳውያን ከአመጋገብ እና ከእንቅስቃሴ ጉድለት የተነሳ ከመጠን በላይ የመወፈር እና ለተለያዩ የጤና ችግሮች ተጋላጭ መሆናቸው መነጋገሪያ ሆኗል።
- በዓለም ዙሪያ ከ1 ቢሊዮን በላይ ሰዎች ከመጠን ላለፈ ውፍረት መጋለጣቸውን ጥናት ጠቆመ1 መጋቢት 2024
- ደም ግፊትን ዝቅ ማድረግን ጨምሮ ቀይ ሥር የሚሰጣቸው አምስት ጥቅሞች27 የካቲት 2024
- ለ45 ደቂቃ አርምሞ ማድረግ የደም ግፊትን ይቀንስ ይሆን?17 መስከረም 2023
ይህ የመንግሥት መመሪያ የወጣው የኡጋንዳ ብሔራዊ የጤና ቅኝት ሪፖርት በአገሪቱ ያለው ከልክ በላይ የወፈሩ ሰዎች አሃዝ ጭማሪ ማሳየቱን ካመለከተ ከሁለት ዓመት በኋላ ነው።
ጥናቱ እንዳለው ባለፉት 17 ዓመታት በኡጋንዳ ውስጥ ከልክ በላይ የመወፈር መጠን ከ17 በመቶ ወደ 26 በመቶ ከፍ ብሏል።
ይህም የክብደት ጭማሪ በሰዎች ጤና ላይ ተላላፊ ያልሆኑ አደገኛ የጤና ችግሮችን እንደሚያስከትል የጤና ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።
የኡጋንዳ መንግሥት ዜጎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ሲያበረታታ ይህ የመጀመሪያ ጊዜው አይደለም።
ከአምስት ዓመት በፊት አገር አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ቀን ሲል አውጆ፣ በመላዋ አገሪቱ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲካሄዱ አድርጓል።
በኡጋንዳ ጤና ሚኒስቴር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ኮሚሽነር የሆኑት ዶክተር ኦዩ አኪያ ለመገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት፣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው ሠራተኞች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግን ቀደም ብለው መጀመራቸውን አመልክተዋል።
አሁን የአገሪቱ መንግሥት በመላው ኡጋንዳ ያሉ የመንግሥት ተቋማት ሠራተኞች በሳምንት ለሁለት ሰዓታት አካላዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ መታዘዛቸው ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲስፋፉ ያደርጋል ተብሏል።