
ከ 1 ሰአት በፊት
ትልቅ ቦታ ላይ ይደርሳል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች አለልኝ አዘነ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።
ቢቢሲ ከተጫዋቹ የቅርብ ጓደኞች ማረጋገጥ እንደቻለው ተጫዋቹ ማክሰኞ መጋቢት 17/2016 ዓ.ም. ነው ከዚህ ዓለም በሞት የተለየወ።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በፌስቡክ ገፁ ባወጣው መግለጫ በተጫዋቹ ደንገተኛ ሕልፈት የተሰማውን ሐዘን ገልጧል።
አርባ ምንጭ ከተማ በተለምዶ ልማት ሰፈር የሚባለው ሰፈር ተወልዶ ያደገው አለልኝ አዘነ፣ በብሔራዊ ቡድኑ በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ እጀግ ተስፋ ከተጣለባቸው ተጫዋቾች መካከል ነበር።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተጫዋቹ በምን ምክንያት በድንገት እንዳረፈ ያለው ነገር የለም።
“አለልኝ አዘነ በተደጋጋሚ ለብሔራዊ ቡድናችን ተመርጦ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ እና በአሁኑ ወቅት በእግር ኳሳችን ላይ ምርጥ አቋማቸውን እያሳዩ ከሚገኙ ተጫዋቾች መካከል የሚጠቀስ ተጫዋች ነበር” ይላል የፌዴሬሽኑ መግለጫ።
የባሕር ዳር ከተማ እግር ኳስ ክለብ እንደገለጠው አለለኝ አዘነ በጉዳት ምክንያት ከቡድኑ ተነጥሎ ለእረፍት ነበር ወደ አርባምንጭ ያቀናው።
የባሕር ዳር ከተማ ቡድን መሪ ሄኖክ ሀብቴ የክለቡ አመራሮች እና ተጫዋቾች በአለልኝ ድንገተኛ ሞት ማዘናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
- የቻይና እግር ኳስ ማኅበር ፕሬዝዳንት በሙስና ወንጀል በዕድሜ ልክ እስራት ተቀጡ26 መጋቢት 2024
- ለጀርመን ብሔራዊ ቡድን የአሜሪካ ኩባንያ ትጥቅ እንዲያቀርብ መወሰኑን ፖለቲከኞች ተቃወሙ23 መጋቢት 2024
“በጉዳት ምክንያት እረፍት ስለሚያስፈልገው ነው ወደ አርባ ምንጭ የሄደው። ሰኞ [መጋቢት 16/2016] አዲስ አበባ መጥቶ ሕክምና አድርጎ ነው የተመለሰው። ከዚያ በኋላ ነው ሌሊት ተደውሎልን ሞቱን የተረዳነው” ይላሉ።
የቡደን መሪው አክለው የባሕር ዳር ተጫዋቾች እና አመራሮች በተጫዋቹ ሕልፈት ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ መሆናቸውን ለቢቢሲ ገልጠዋል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚዬረ ሊግ አክሲዮን ማኅበር፣ የአርባ ምንጭ ከነማ እግር ኳስ ክለብ፣ የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር እና ሌሎችም በተጫዋቹ ሞት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።
የአለልኝን ብቃት የሚያደንቁት በርካታ የእግር ኳስ አፍቃሪዎችም በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ የተጫዋቹ ሞት ለአገሪቱ እግር ኳስ ሊያበረክት የሚችለውን አስተዋጽኦ ያሳጣ ነው በማለት ሐዘናቸውን እየገለጹ ነው።
አለልኝ ማን ነበር?
አርባ ምንጭ ተወልዶ ያደገው አለልኝ አዘነ ላለፉት ሁለት ዓመታት ለባሕር ዳር ከተማ ተጫውቷል።
የተከላካይ አማካዩ አለልኝ ከባሕር ዳር ከተማ በፊት ለሐዋሳ ከተማ እና ለመቀለ 70 እንደርታ ተጫውቷል።
በቅርቡ በኦርቶዶክሰ እምነት መሠረት ትዳር የፈፀመው አለልኝ ከኢትዮጵያ ወጥቶ እግር ኳሰ መጫወት እንደሚሻ ይናገር ነበር።
የተጫዋቹ የቅርብ ጓደኛ የሆነ ሰው አለልኝ ለቤተሰቡ “ከሚገባው በላይ የሚያዝን፤ ይህን አደረግኩ ብሎ የማይረካ ሰው ነበር” ሲል ለቢቢሲ ይናገራል።
“በጣም ትልቅ ሕልም ነበረው። ከአንድ ሳምንት በፊት [ትዳር በመመሥረቱ] እንኳን ደስ አለህ ልለው ደውዬለት ነበር። ከጉዳቱ አገግሞ ድሬ ዳዋ እንደምንገናኝ ተነጋግረን ነበር። ሁሉም የቡደን አጋሮቹ የሚወዱት ሰው ነበር።”
የባሕር ዳር ከተማ ቡድን መሪ ሄኖክም እንዲሁ “አለልኝ እጅግ መልካም ባሕሪ ያለው፤ የቤተ-ክርስትያን ልጅ ነው” ይላሉ።
ሄኖክ አክለው አለልኝ ለክለብም ሆነ ለአገር ትልቅ ተስፋ የተጣለበት እግር ኳስ ተጫዋች እንደነበር ያወሳሉ።
የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ኮሜንታተር በመሆን ያገለገለው ጊልበርት ሴሌብዋል በተጫዋቹ ድንገተኛ ሞት የተሰማውን ሀዘን ለቢቢሲ ይገልጣል።
“እኔ ኮሜንታተር እያለሁ ያገባቸውን ሦስት ጎሎች አልረሳም። ከፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውጭ አክርሮ የመታቸው ተመሳሳይነት ያላቸው ጎሎች ነበሩ። በጣም የሚገርም ተሰጥዖ የነበረው፤ አውሮፓ ሁሉ ሄዶ መጫወት የሚያስችል አቋም እና ቁመና የነበረው ተጫዋች ነው። በጣም ደንግጫለሁ” ብሏል ጊልበርት።
የአለልኝ አዘነ ሥርዓተ-ቀብር ዛሬ ረቡዕ መጋቢት 18/2016 ኣ.ም. በአርባ ምንጭ ከተማ እንደሚፈፀም ይጠበቃል።