የአዋቂዎች ዳይፐር
የምስሉ መግለጫ,የአዋቂዎች ዳይፐር

27 መጋቢት 2024, 12:08 EAT

የውልደት መጠን በቀነሰባት ጃፓን የሚገኙ ዳይፐር አምራች ኩባንያዎች የሕጻናት ዳይፐር ምርት አቁመው ትኩረታቸውን የአዋቂ ዳይፐር ላይ እያደረጉ ነው።

በቅርቡም ኦጂ ሆልዲንግስ የተባለው ኩባንያ የሕጻናት ዳይፐር (ሽንት ጨርቅ) ምርትን በማቆም ከአሁን በኋላ የማምርተው የአዋቂ ዳይፐር ብቻ ይሆናል ብሏል።

ባለፉት አስርት ዓመታት በጃፓን ከሕጻናት ይልቅ የአዋቂ ዳይፐር ሽያጭ ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።

እአአ በ2023 በጃፓን የተወለዱት ሕጻናት ቁጥር 758 ሺህ 631 ሲሆን፣ ከቀደመው 2022 ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ5.1 በመቶ ቀንሷል።

በ2023 የተወለዱት ሕጻናት ቁጥር ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በዓመት ውስጥ ከተወለዱት አነስተኛው ቁጥር መሆኑ ተነግሯል።

እአአ በ1970ዎቹ በጃፓን በየዓመቱ የሚወለዱ ሕጻናት ቁጥር ከሁለት ሚሊዮን በላይ ነበር።

ኦጂ ሆልዲንግስ ባወጣው መግለጫ በየዓመቱ 400 ሚሊዮን የሕጻናት ዳይፐር ያመርት ነበር። ይሁን እንጂ ከ2001 ጀምሮ የሕጻናት ዳይፐር ምርቱን ሲቀንስ ቆይቷል።

የጃፓን ትልቁ የዳይፐር አምራች የሆነው ዩኒቻርም እአአ በ2011 የአዋቂዎች ዳይፐር ሽያጩ ከሕጻናቱ መብለጡን አስታውቋል።

የአዋቂዎች ዳይፐር ገበያ እየደራ በመሄድ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል። ለዚህም ምክንያቱ ጃፓን በዓለማችን በዕድሜ የገፉ በርካታ ሰዎች ካሉባቸው አገራት አንዷ በመሆኗ ነው።

30 በመቶ የሚሆኑት ዜጎቿ ከ65 ዓመት በላይ ናቸው። ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ዕድሜያቸው ከ80 በላይ የሆኑት ዜጎች ቁጥር ለመጀመሪያ ጊዜ ከአጠቃላይ ሕዝቡ ከ10 በመቶ በላይ ሆኗል።

ኦጂ ሆልዲንግስ የሕጻናት የዳይፐር ገበያው ይመነደጋል ብሎ በሚያስብባቸው ማሌዢያ እና ኢንዶኔዢያ ውስጥ ማምረቱን እንደሚቀጥል አስታውቋል።

በዓለም አራተኛዋ ባለትልቅ ኢኮኖሚ የሆነችው ጃፓን በወሊድ ምጣኔ መቀነስ እና በዕድሜ የገፉ ሰዎች መጨመር ምክንያት የሕዝብ ቁጥሯ እያሽቆለቆለ ይገኛል።

ይህንን አሳሳቢ ሁኔታ ለማስተካከል ጥረት ያደረገው የአገሪቱ መንግሥትም አስካሁን ይህ ነው የሚባል ውጤት አላገኘም።

ጃፓን ሕጻናት ነክ በሆኑ ፕሮግራሞች ላይ እና ወጣት ጥንዶች እንዲሁም ባለትዳሮች ላይ በርከት ያለ ገንዘብ ብታፈስም የወሊድ ምጣኔን ማሳደግ አልቻለችም።

ባለሙያዎች ግን ለዚህ ምክንያት የሚሏቸው በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን አንስተዋል። ወደ ትዳር የሚገቡ ጥንዶች መቀነስ፣ ሴቶች ወደ ሥራ መሠማራታቸው እና ለሕጻናት የሚወጣው ወጪ መጨር ጥቂቶቹ ናቸው።

በውልደት ምጣኔ መቀነስ ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ ባለፈው ዓመት ጃፓን እንደ ማኅበረሰብ መቀጠል የማትችልበት ደረጃ ላይ ልትደርስ እንደምትችል አስጠንቅቀው ነበር።

ለዚህ ችግር የተጋለጠችው ግን ጃፓን ብቻ አይደለችም። በሆንግ ኮንግ፣ ሲንጋፖር፣ ታይዋን እና ደቡብ ኮሪያ የወሊድ ምጣኔ እየቀነሰ ነው። ደቡብ ኮሪያ ዝቅተኛ የወሊድ መጠን በመያዝ ቀዳሚ ናት።

ቻይናም እአአ በ2023 የሕዝቧ ቁጥር ለተከታታይ ሁለተኛ ዓመት ቀንሷል።

ልክ እንደ ጃፓን ሁሉ ቻይናም የወሊድ ምጣኔን ለመጨመር የተለያዩ ማበረታቻዎችን ይፋ አድርጋለች። እርጅና የተጫነው የሕዝብ ቁጥር እና እንዲነሳ የተደረገው የአንድ ልጅ ፖሊሲ ተጽዕኖ በቻይናም ችግሮች እየፈጠሩ ነው።