ዜና የፍትሕ ሥርዓቱ ክፍተት ሴቶች ሕፃናት ተገቢውን ፍትሕ እንዳያገኙ ማድረጉን ኢሰመኮ አስታወቀ

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

ቀን: March 27, 2024

በፅዮን ታደሰ

በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች፣ በወንጀል ሥነ ሥርዓትና በማስረጃ ደንቦች ባለመካተታቸው፣ የጥቃት ተጎጂ ሴቶችና ሕፃናት ፍትሕ እንዳያገኙ ማድረጉን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (አሰመኮ) አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ የጥቃት ተጎጂ ሴቶችና ሕፃናት ሰብዓዊ መብቶች አያያዝን አስመልክቶ ያደረገውን የክትትል ሪፖርት ማክሰኞ መጋቢት 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በሲዳማ ክልሎች በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ክትትሉን አለማከናወኑን አስታውቋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የፍትሕ ተቋማት የሴቶችን ጥቃት ከወሲባዊ ጥቃቶች አንፃር ብቻ ስለሚያዩ፣ የክትትሉን ወሰን የወሲባዊ ጥቃት ተጎጂዎች የመብቶች አያያዝ ላይ ብቻ እንዳደረገው ኢሰመኮ በሪፖርቱ ገልጿል፡፡

የጥቃት ተጎጂ ሴቶችና ሕፃናት በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት በሚያልፉበት ወቅት ፍትሕ የማግኘት፣ ክብርና ሚስጥራዊነትን በጠበቀ የፍትሕ ሥርዓት የመስተናገድ፣ ከሁለተኛ ደረጃ ጥቃት የመጠበቅና የደኅንነት ጥበቃና ድጋፍ የማግኘት መብታቸው በተሟላ መንገድ ተግባራዊ እየተደረገ አለመሆኑን በክተትሉ ለመረዳት መቻሉን አስታውቋል፡፡

ከመደበኛው የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ ውጪ በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር፣ የጥቃት ተጎጂ ሴቶችና ሕፃናትን የመብቶች አያያዝን የሚደነግግ ወጥና አስገዳጅ የሆነ የሥነ ሥርዓት መመርያ ወይም ፕሮቶኮል አለመኖሩን፣ ኮሚሽኑ ይፋ ባደረገው የክትትል ሪፖርት ገልጿል፡፡

የሴቶችና ሕፃናት ችሎት አደረጃጀት በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ብቻ ያለ መሆኑ፣ ጉዳዩ በከፍተኛ ፍርድ ቤት በሚታይበት ጊዜ፣ በመደበኛ የወንጀል ፍትሕ ሒደት የሚያልፍ መሆኑ ለመብት ጥሰቱ በምክንያትነት ቀርቧል፡፡ 

በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል በሸገር ከተማ አስተዳደር፣ በቡራዩና በሰበታ ክፍላተ ከተሞች፣ በኦሮሚያ ክልል በጅማ ዞን፣ በጅማ ከተማና በሸቤ ሶምቦ አዋሳኝ ወረዳ፣ እንዲሁም በሐረሪ ክልል የሴቶችና ሕፃናትን ጥቃት ብቻ የሚመለከት መዋቅር አለመኖር፣ የሕክምና ማስረጃ በሚፈለገው ጊዜና ይዘት አለመቅረብ፣ እንዲሁም የተከሳሽና የምስክሮች አለመገኘት፣ ጉዳዮች በፍጥነት ውሳኔ እንዳያገኙ ምክንያት መሆናቸውን በክትትሉ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ዳኞች መግለጻቸውን ኮሚሽኑ አስታወቋል።

የጥቃት ተጎጂ ሴቶችና ሕፃናት በፍርድ ወቅት ያሏቸው የመብት አያያዝ  ከአቤቱታ አቀራረብ ሥርዓት ጀምሮ፣ በምርመራ ሒደት፣ በክስ አቀራረብና አሰማም፣ እንዲሁም በፍርድ ወቅት አገር አቀፍ፣ አኅጉራዊና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መሥፈርቶችን ያሟላ አለመሆኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

ኮሚሽኑ መንግሥት በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትሕ ፖሊሲ መሠረት የጥቃት ተጎጂ ሴቶችና ሕፃናትን የተለየ አያያዝ የሚመለከት ግልጽ የሕግ ማዕቀፍ እንዲያወጣ አሳስቧል፡፡