ዜና በአልሸባብ ክንፍነት የተጠረጠረ ታጣቂ ቡድን በባሌ የፀጥታ ሥጋት መሆኑ ተገለጸ

ዮናስ አማረ

ቀን: March 24, 2024

በኦሮሚያ ክልል በባሌ ዞን የአልሸባብ ክንፍ በመሆን የሚጠረጠር የታጠቀ ቡድን መደራጀቱንና እንቅስቃሴ መጀመሩን በፀጥታ ሥጋትነት የክልሉ ባለሥልጣናት ማስቀመጣቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰማኮ) ዓርብ መጋቢት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ሪፖርት አስታወቀ፡፡

በኬንያ፣ በኡጋንዳና በሶማሊያ ኃይሎች ጭምር ይደገፋል የሚባለው ይህ ሸማቂ ኃይል፣ በፖሊሶችና በመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ጥቃት መክፈቱ ችግሩን እንዳወሳሰበ ባለሥልጣናቱ ስለመናገራቸው ኢሰመኮ በሪፖርቱ አብራርቷል፡፡

የሶማሌ ክልልን ጨምሮ በአራቱ ሰፋፊ ክልሎች በማሰርና በእስር አያያዝ ሒደት ባለፉት አምስት ዓመታት የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን በሰፊው የሚዘረዝረው የኢሰማኮ ሪፖርት፣ ከባድ የመብት አያያዝ ጉድለቶችን ማግኘቱን አብራርቷል፡፡ ኢሰብዓዊ አያያዝን ጨምሮ ጭካኔ የተሞላበት ማሰቃየት፣ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃት መብታቸው በተገደበ ሰዎች ላይ ስለመፈጸሙ የኢሰመኮ ሪፖርት አሳሳቢ ጉዳይ ነው ሲል አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ነፃነታቸውን በተነፈጉ (በታሰሩ) ሰዎች ላይ የመብት ጥሰቶች እንደሚፈጸና ከ2010 እስከ 2015 ዓ.ም. ባሉት አምስት ዓመታት በአራት ክልሎች የታሰሩ ሰዎችን የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ በገመገመበት ሪፖርት ላይ አብራርቷል፡፡

ኢሰመኮ ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ ሥልታዊና የዘፈቀደ እስራት እንደሚፈጸም አስታውቆ፣ በእስር አያያዝ ሒደትም የመብት ጥሰቶች ይፈጸማሉ ብሏል፡፡

በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሌና በቀድሞው አጠራሩ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በታሰሩ ሰዎች ላይ ስለሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶች የሚዘረዝረው ሪፖርቱ፣ 86 ተጎጂዎችንና ምስክሮቻቸውን ማነጋገሩን ያስረዳል፡፡ በአራቱም ክልሎች አቤቱታ መቀበያ መድረኮችን በማዘጋጀትም የሕግ አካላትንና የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 365 ሰዎችን ያሳተፈ ውይይት ማድረጉንም ያክላል፡፡

በዚህ የምርመራ ሒደትም የዘፈቀደ እስርን ጨምሮ ማሰቃየትና ኢሰብዓዊ አያያዝ፣ ከሕግ አማካሪ ጋር መገናኘትን መከልከል፣ የቤተሰብ ጉብኝት ክልከላ፣ የመተዳደሪያ ገቢ ማጣት፣ ስለሰብዓዊ መብቶች በቂ ግንዛቤ አለመኖር፣ እንዲሁም ለጥሰቶቹ መፍትሔና ማካካሻ አለመኖርን የመሳሰሉ የመብት ጥሰቶች በታሳሪዎች ላይ እንደሚፈጸም ሪፖርቱ ማረጋገጡን ይገልጻል፡፡

መብታቸው እንዲገደብ የሚደረጉ ሰዎች የመብት ጥሰት በቁጥጥር ሥር ከመዋል ጀምሮ ባለው ሒደት እንደሚያጋጥም በሪፖርቱ ተካቷል፡፡ በፖሊሶች እየተፈጸመ ያለው ‹‹የምትክ እስራት›› ወይም ተጠርጣሪው እስከሚገኝ የቤተሰብ አባልን የማሰር ዕርምጃ፣ ከእነዚህ የመብት ጥሰቶች አንዱ አሳሳቢ ድርጊት እንደሆነ ሪፖርቱ በጉልህ ያወሳል፡፡

የእያንዳንዱን ክልል የታሰሩ ሰዎችን የመብት አያያዝ በተናጠል የሚዘረዝረው በሰባት ምዕራፎች የቀረበው ባለ 113 ገጽ የኢሰመኮ ሪፖርት፣ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት የታሰሩ ሰዎችን መብት አያያዝ ለማሻሻል ቁርጠኛ ሊሆኑ እንደሚገባ ይጠይቃል፡፡

በፈረሰው ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ለዘፈቀደ እስራትና ለተያያዥ የመብት ጥሰቶች ሲዳረጉ የቆዩ ችግሮች ከአስተዳደርና ከወሰን ጋር የተያያዙ ፖለቲካዊ ችግሮች መሆናቸውን ይገልጻል፡፡ በደራሼ ልዩ ወረዳ፣ በቁጫ፣ በመስቃንና ማረቆ አካባቢዎች ያጋጠሙ ችግሮች ከዚሁ ጋር የተያያዙ ስለመሆናቸው ያብራራል፡፡

በአማራ ክልል ለዘፈቀደ እስራትና ለተያያዥ የመብት ጥሰቶች ዜጎች የተጋለጡበትን ዋና ምክንያት ከፖለቲካዊ ጥያቄ ጋር የተገናኘ ስለመሆኑ ሪፖርቱ ያወሳል፡፡ በርካታ ሰለባዎች ሐሳባችንን በነፃነት እንግለጽ በማለታቸው፣ ተደራጅተው ለመንቀሳቀስ በመሞከራቸው ወይም ፖለቲካዊ ተሳትፎ በማድረጋቸው መታሰራቸውን እንደተናገሩ በኢሰመኮ ሪፖርት ተመልክቷል፡፡

በሌላ በኩል በኦሮሚያ ክልል ለዘፈቀደ እስራት ወይም በእስር ወቅት ለሚገጥሙ የመብት ጥሰቶች መነሻ ከሆኑ ችግሮች ዋናው፣ በታጠቁ ቡድኖች የሚጸመው ጥቃት አንዱ መሆኑን ይገልጻል፡፡ በተለይ በወለጋ አካባቢ የሚፈጸመው የታጠቁ ኃይሎች ጥቃት ችግሩን ካወሳሰቡት ጉዳዮች አንዱ መሆኑን ያስረዳል፡፡