በጋዜጣዉ ሪፓርተር

March 27, 2024

በፅዮን ታደሰ

ኢት ስዊች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ምሽት የሲስተም ችግር ሲገጥመው በሞባይል ባንክ አማካይት ወደ ሌላ ባንክ ሲደረጉ የነበሩ የገንዘብ ዝውውሮች መረጃዎችን፣ ለኢትዮጵያ በብሔራዊ ባንክና ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማስተላለፉን አስታወቀ፡፡

የኢትስዊች ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ይለበስ አዲስ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በሞባይል ባንኪንግ ከአንድ ወደ ሌላ ባንክ የሚደረግ የገንዘብ ዝውውር መረጃ በድርጅታቸው ይመዘገባል፡፡ ንግድ ባንክ የሲስተም ችግር ሲያጋጥመው የተደረጉ የገንዘብ ዝውውሮችን በተመለከተ እንደ ሌሎቹ ቀናት ሁሉ ኢትስዊች መረጃ አለው ብለዋል፡፡

ከንግድ ባንክ ወደ ሌላ ባንክ በሞባይል ባንኪንግ የተደረጉ የገንዘብ ዝውውር መረጃዎችን በየቀኑ ለብሔራዊ ባንክና ለባንኮች እንደሚላክ የገለጹት አቶ ይለበስ፣ ከንግድ ባንክ የገንዘብ ዝውውሮች በተካሄዱበት ምሽት ደግሞ ሁሉም የዝውውር መረጃዎች ለባንኩና ለብሔራዊ ባንክ መላካቸውን ጠቁመዋል፡፡

በሁሉም ባንኮች ባለቤትነት የሚተዳደረውና በ2003 ዓ.ም. የተመሠረተው ኢትስዊች፣ ብሔራዊ የክፍያ አገልግሎት ማዘመን ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ተቋም ነው፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ንግድ ባንክ ማክሰኞ መጋቢት 17 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ 567 ግለሰቦች የወሰዱትን 9.8 ሚሊዮን ብር እስካሁን ማስመለስ አለመቻሉን አስታውቋል፡፡ በዕለቱ 25,761 የባንኩ ደንበኞች 801.4 ሚሊዮን ብር መውሰዳቸውን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ገልጸው፣ እስከ ሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ከተወሰደው ገንዘብ 78 በመቶ ተመላሽ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

ገንዘቡን ተመላሽ ያላደረጉ ግለሰቦች ስማቸውንና ማንነታቸውን የሚገልጽ ምሥል ይፋ እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡

ንግድ ባንክ ያጋጠመው ዓይነት የሲስተም ችግር ‹‹በየትኛውም ባንክ ቢሆን ሊያጋጥመው የሚችል ነው፤›› ያሉት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የባንክ ባለሙያ፣ የሲስተም ችግሩን በመጠቀም የራሳቸው ያልሆነን ገንዘብ የወሰዱ ግለሰቦች ጊዜ ሊወስድ ይችል ይሆናል እንጂ ተለይተው መታወቃቸው እንደማይቀርና ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡

‹‹ባንኩ የደንበኞቹን ገንዘብ የመጠበቅ፣ እሴት የመጨመርና በፈለጉ ጊዜ የመስጠት ግዴታ እንዳለበት ሁሉ፣ የባንኩ ደንበኞችም አገልግሎቱን በታማኝነት የመጠቀም ግዴታ እንዳለባቸው በባንኩና በደንበኞች መካከል ስምምነት አለ፤›› ብለዋል፡፡ ለረዥም ዓመታት የዘለቀው የባንኩ ሲስተም ግንባታ በአንዴ ተሠርቶ አለመጠናቀቁን፣ በዚህ ሒደት ውስጥ የባለሙያዎች መለዋወጥ ለእንዲህ ዓይነት ችግር ተጋላጭ አድርጎት ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

የኢንፎርሜሽንና መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢንሳ) በባንኩ ላይ የተፈጠረው ችግር በሞባይል ባንኪንግ ሲስተሙ ላይ ባደረገው የማሻሻያ ሥራ ሳቢያ መሆኑን አስታውቆ፣ ባለሙያው ከሰጡት አስተያየት ጋር ተመሳሳይ የሆነ መረጃ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ኢንሳ በባንኩ ላይ ከአገር ውስጥም ሆነ ‹‹ከውጭ የተሰነዘረ የሳይበር ጥቃት የለም›› ማለቱ አይዘነጋም፡፡