ማኅበራዊ የሴቶችን የመረጃ ክፍተት የሚሞላው መድረክ

ምሕረት ሞገስ

ቀን: March 27, 2024

ኢትዮጵያውያን ሴቶች በተለይም በገጠር የሚኖሩት እየገጠማቸው ያለው የመረጃ ክፍተት ተጠቃሚ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ ችግሩን ለመፍታት የመረጃ ፍሰትን እስከታች ሊያወርዱ የሚችሉ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ዘመኑ የደረሰበት መፍትሔ ነው፡፡

በመሆኑም፣ የመረጃ ክፍተትን ለመሙላት ያግዛል የተባለውና በሴቶችና ሕፃናት ዙሪያ የሚሠሩ ድርጅቶች መረጃ የሚያደርሱበት ኢትዮውሜንስ የተባለ ድረገጽ ይፋ ሆኗል፡፡

ለድረገጹ አንድ ግብዓት ሆኖ ያገለግላል የተባለው የሴቶች መረጃ ማዕከል እየተሠራ መሆኑንም፣ የኢትዮጵያ ሴቶችና ሕፃናት ማኅበራት ኅብረት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ አዜብ ቀለመወርቅ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴት ተመራጭ ስብስብ (ኮከስ) ሰብሳቢ ኪሚያ ጁንዲ በበኩላቸው፣ ዓለም አንድ መንደር እየሆነች በመጣችበት ወቅት የሴት ድርጅቶች መረጃን በአንድ ትስስር ለማዳረስ መሥራታቸው መልካም ቢሆንም፣ ድረገጽ መከፈት በራሱ በቂ ስላልሆነ፣ በእያንዳንዱ ተቋም ውስጥ የሚሠሩ ሥራዎችን ይፋ ለማድረግ፣ ከተሠሩ በኋላ ለኅብረተሰቡ እንዲደርሱና ተቋማቱ ቀጣይነት እንዲራቸው ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል፡፡

አንድ ሥራ ለመሥራት መቀናጀትና በሲቪል ማኅበራት መመዝገብ ብቻ ለተቋሙም ለአገርም ጥቅም የለውም ያሉት ወ/ሮ ኪሚያ፣ ትልቁ ፋይዳ የሚሆነው ‹‹ያቺ የተናገርንላት ሴት ምን አግኝታለች፣ ምን ሠርታለች፣ ምንስ ውጤት መጥቷል የሚለውን በጋራ እየገመገምን ስንሄድ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

በተለይ ለመንግሥትና ለኅብረተሰቡ የሚጠቅሙ ጥናቶች በእናንተ ዘንድ አሉ ያሉት ወ/ሮ ኪሚያ፣ ጥናቶቹ የሴቶች ፖሊሲ፣ ፕሮግራምም ሆነ ዕቅድ ላይ ለሚደረጉ ውሳኔዎች ጠቀሜታ ስላላቸው  በድረገጹ እንዲጫኑ ማረደግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ይህም ‹‹እናንተም እኛም ለቆምንላትና ድምጽ እንሆናለን ላልናት ሴት ውጤት ያመጣል›› ብለዋል፡፡

ማንኛውም ሥራ ከአገር በላይ አይደለምና የሚሠሩ ሥራዎች የአገር ሉዓላዊነትን የሚነኩ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ወ/ሮ አዜብ እንዳሉት፣ ድረገጹ በዋናነት መነሻው ሴቶችና ሕፃናት በተለይ የገጠር ሴቶች እንዲሁም በሴቶችና ሕፃናት ዙሪያ የሚሠሩ ድርጅቶች ያለባቸውን መረጃ የማግኘት ችግር ለመቅረፍ ነው፡፡

ዓለም በዲጂታል ቴክኖሎጂ አንድ እየሆነች በመጣችበትና መረጃ በቀላሉ በሚተላለፍበት ዘመን፣ በኢትዮጵያ በተለይ የገጠሯ ሴት በዓለምና በአገር ውስጥ የሚስተዋሉ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና አየር ንብረታዊ መረጃዎችን የማግኘት ዕድል የላትም፡፡ ቴክኖሎጂውም አልደረሰም፡፡ ከአንድ ቋት ትክክለኛ መረጃ የማግኘት ዕድሉም ጠባብ ነው ብለዋል፡፡

ድረገጹ በመረጃ ክፍተት የሚመጡ ችግሮችን ከመቅረፍ ባሻገር፣ በሴቶችና ሕፃናት ዙሪያ የሚሠሩ ድርጅቶች የሚሠሯቸውን ሥራዎች በጋራ ወደ አንድ ለማምጣት፣ በጋራ ሆነው ለሴቶች ድምፅ እንዲሆኑ ለማስቻል፣ ለሴቶችና ሕፃናት አቅም ለመፍጠርና የሥርዓተ ፆታ እኩልነትን ለማስፈን እንደሚያግዝም ገልጸዋል፡፡

በሴትና ሕፃናት ዙሪያ የሚሠሩ ድርጅቶች መረጃ የሚቀባበሉበት፣ ልምድ የሚለዋወጡበት፣ ሀብት የሚያሰባስቡበት፣ ለሴቷ በጋራ የሚሠሩበት መድረክ ሆኖ የሚያገለግል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የውሜን ቮይስ ሊደርሽፕ ፕሮጀክት አካል የሆኑ በአገር አቀፍ ደረጃ 98 በሴቶች ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች መኖራቸውን፣ ለእነዚህ በድረገጹ ዙሪያ ሥልጠና መሰጠቱን፣ እያንዳንዱ ድርጅትም ከራሱ ድረገጽ ጋር አዋህዶ (Link) አድርጎ መረጃዎችን እንዲያሠራጭ፣ የጋራ መድረኮች እንዲኖሩ የሚያስችል ሆኖ በኅብረቱ አስተባባሪነት የሚሠራ እንደሆነም አክለዋል፡፡

እንደ ወ/ሮ አዜብ፣ በኢትዮጵያ ያሉ ሴቶች፣ ሕፃናት፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ትክክለኛ ገጽታ ምን ይመስላል? ለሴቶች አቅም ለመፍጠርና የሥርዓተ ፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ የሚሠሩ ሥራዎች ምን ውጤት አመጡ? የኑሮ ሁኔታን ለማሻሻል፣ ከአካባቢ አየር ለውጥ ጋር ያሉ ችግሮችን ለመቀነስ፣ ግጭትን አስወግዶ ሰላምን ለማስፈን፣ በግጭትም ሆነ በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ቤት ንብረት ያጡና ችግር ለደረሰባቸው የሚሰጠው ሰብዓዊ ድጋፍ ምን ይመስላል? የሴት ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሚሠሯቸው ሥራዎች ምን ለውጥ አምጥተዋል? የሚሉትም በድረገጹ የሚለቀቁ ይሆናል፡፡

በክልልና በገጠር በሴቶችና ሕፃናት ዙሪያ የሚሠሩ ድርጅቶች ከድረገጹ ያገኙትን መረጃ ታች ላለችው ሴት የሚያደርሱበት አሠራር እንደሚኖር፣ እነሱ የሠሩትን ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ያገኙትን መረጃም እንደሚያካፍሉ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢኮኖሚ፣ በአካባቢ አየር ለውጥ፣ በሰብዓዊ ድጋፍ አሰጣጥና ማንኛውም በሴቶች፣ ሕፃናት አረጋውያን ላይ ትኩረት አድርገው የሚሠሩ ሥራዎች ሁሉ የሚታወቁበትን ዕድል ይፈጥራል፡፡

መንግሥታዊም ሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚያጠኗቸው ጥናቶች ውጤት ተግባራዊ እንዲሆን በድረገጹ የሚቀመጥ መሆኑን፣ ኅብረቱ እያሠራ የሚገኘው የሴቶች መረጃ ማዕከልም ለድረገጹ ግብዓት እንደሚሆን አክለዋል፡፡ በሴቶችና ሕፃናት ዙሪያ የወጡ ሕጎች፣ ፖሊሲዎች፣ መመርያዎችና ስትራቴጂዎች በድረገጹ የሚቀመጡ በመሆኑ ድርጅቶች መረጃ የሚያገኙበትም ይሆናል ብለዋል፡፡

ሴቷ መብትና ግዴታዋን እንድታውቅ፣ ዓለም አቀፍ ረጂ ድርጀቶችም የሴቶች ድርጅቶች ምን እየሠሩ እንደሆነ እንዲገነዘቡ፣ በኢትዮጵያ በሴቶች ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ዘርፍ ያላቸው አስተዋጽኦ ይህንንም ያህል ዕውቅና ስላላገኘ፣ ይህንን ለማሳወቅ እንደሚረዳም ተናግረዋል፡፡

ድርጅቶች እየሠሩ ያሉትን፣ ያመጡትን ለውጥ፣ ምን አስተዋጽኦ አድርገዋል የሚለውን መረጃ ለመልቀቅ ስለሚያስችልም  ከረጂ ድርጅቶች ድጋፍ ለማግኘትም እንደሚያስችልም ገልጸዋል፡፡

በፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ በኩል ከግሎባል አፌርስ ካናዳ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የበለፀገው ድረገጽ፣ በኢትዮጵያ የሴቶችና ሕፃናት ማኅበራት ኅብረት አስተባባሪነት ከኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር፣ ከሴቶች ማኅበራት ቅንጅትና ከኢትዮጵያን ሴንተር ፎር ዴቨሎፕመንት ጋር የተሠራ ነው፡፡