
March 27, 2024

ወ/ሮ ቅድስት ሽመልስ በግሎባል ስተዲስ ኤንድ ኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በፕሮጀክት ማኔጅመንት እንዲሁም በኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ ሠርተዋል፡፡ በኮርፖሬት ፋይናንስ ካናዳ ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ አድቫንስድ ዲፕሎማ አላቸው፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራ አስተናጋጅነት ለሦስት ዓመታት፣ በኋላም ኤድማርክ ለሚባል የማሌዥያ ኩባንያ ሴልስ ኤጀንት ሆነው ለአራት ዓመታት ሠርተዋል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ፕሮጀክት ሱፐርቫይዘር ሆነውም አገልግለዋል፡፡ አሁን ላይ የኢት ኸርባል ማምረቻ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሲሆኑ፣ ከዓመት በፊት ለተቋቋመው ኢትኬር ቁጠባና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ የኅብረት ሥራ ማኅበርም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡ በኅብረት ሥራ ማኅበሩና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡
ሪፖርተር፡- የብድርና ቁጠባ ማኅበራት አንዱ ዓላማ ሥራ ፈጣሪ ማኅበረሰብ መፍጠር ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ ምን እየሠራችሁ ነው?
ወ/ሮ ቅድስት፡- ኢትኬር ቁጠባና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ የኅብረት ሥራ ማኅበር በዋናነት የተቋቋመው በኢት ኸርባል ምርቶች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ውስጥ በሽያጭ ሥራ የተሠማሩ ባለሙያዎችን በፋይናንስ የበለፀገ ዕውቀት እንዲኖራቸው፣ ገንዘባቸውን ወደ ሀብት (አሴት) እንዲቀይሩ፣ እንዲቆጥቡ፣ ብድር እንዲያገኙና ሥራ ፈጥረው የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ ለማስቻል ነው፡፡ መነሻው በዋናነት ኢትኬር ላይ የሚሠሩ ሰዎችን ሕይወት ለመቀየር ቢሆንም፣ በቀጣይ ለሁሉም ማኅበረሰብ ክፍት ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- ሥራ ፈጣሪ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ሲታሰብ በቅድሚያ የዕውቀት ክፍተቶችን መሙላት ያስፈልጋል፡፡ ገንዘብ ለመበደር የሚፈልጉ አባላት የሥራ ሐሳብ ሲያመጡ የማማከር ሥራ ትሠራላችሁ?
ወ/ሮ ቅድስት፡- የመጀመሪያው አገልግሎታችን ቁጠባ፣ በኋላ ብድርና የሥልጠና አገልግሎት መስጠት ነው፡፡ በዘርፉ ክፍተቶችን ለይተናል፡፡ የፋይናንስ ግንዛቤ እጥረት በግለሰብ ደረጃ መኖሩን ዓይተናል፡፡ ገንዘብን አብቃቅቶ መጠቀም፣ በቁጠባና በተያያዥ ጉዳዮች ክፍተት መኖሩን በማየታችን፣ በወር አንዴ ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ በፋይናንስ ዘርፍ ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎችን ጋብዘን አጠቃላይ በፋይናንስ ዕውቀት፣ በኢንቨስትመንትና በሀብት አጠቃቀም ዙሪያ ሥልጠና እንሰጣለን፡፡
ሪፖርተር፡- ሥልጠናው በመሰጠቱ በተበዳሪዎች የገንዘብ አጠቃቀምና የሥራ ሒደት ላይ ለውጥ አይታችኋል?
ወ/ሮ ቅድስት፡- በተበዳሪዎች ላይ ለውጥ አለ፡፡ በእጃቸው ብዙ ገንዘብ ያላቸውና ገንዘቡን ምን እንደሚያደርጉ ግራ የገባቸው አሉ፡፡ ካለው የዋጋ ግሽበት አንፃር ገንዘባቸውን አስቀምጠው ዋጋ እያሳጡት ያሉም አሉ፡፡ ይህንንና ሌሎችንም አካተን ሥልጠና ስንሰጥ የተለያየ ዕይታ በማግኘታቸው፣ አክሲዮን የገዙ አሉ፡፡ የተለያዩ ሥራዎች ውስጥ እየገቡም ነው፡፡ ቢዝነስ ከተጀመረ በኋላም እናማክራቸዋለን፡፡ ብድር ከተበደሩ በኋላ ለታቀደው ሥራ ሲያውሉት እንዴት መሆን እንዳለበት ሥልጠና እንሰጣለን፣ እንከታተላለን፡፡
ሪፖርተር፡- ከተመሠረታችሁ አንድ ዓመት ሆኗችኋል፡፡ በዚህ ጊዜ የተበዳሪዎች ብድር አመላለስ ምን ይመስላል? ሥልጠናው ጠቅሟል?
ወ/ሮ ቅድስት፡- አዎ፡፡ ከሰጠነው 35 ሚሊዮን ብር ውስጥ ሁሉም ተበዳሪ በተሰጠው ጊዜ ማለትም ከሁለት እስከ አምስት ዓመታት ባለው ውስጥ መመለስ ስላለበት መመለስ ጀምረዋል፡፡ ከተበደረ አንድ ዓመት የሞላው ባይኖርም፣ ስድስት ወራት የሞላቸው ስላሉ፣ በእነሱ ላይ ያለው የብድር አመላለስ ጥሩ መሆኑን ዓይተናል፡፡
ሪፖርተር፡- የብድር አመላለሱ ላይ ችግር ቢኖር፣ ይህንን ለመታደግ የኢንሹራንስ ትግበራችሁ ምን ይመስላል?
ወ/ሮ ቅድስት፡- ከትንንሽ ብድር ጀምሮ እስከ ከፍተኛው የቤት ብድር ድረስ በመመርያችን መሠረት የ1.5 በመቶ ኢንሹራንስ አለ፡፡ ይህ አንድ ተበዳሪ ከተበደረ በኋላ በተለያየ አጋጣሚ በድንገትም ሊሆን ይችላል ሕይወቱ ቢያልፍ ዕዳው ወደ ቤተሰቦቹ እንዳይሄድ ያደርጋል፡፡ ይህ ተቀማጭ ገንዘብ እንዲኖር፣ በሌላ በኩል ዕዳ ለቤተሰብ እንዳይተላለፍ መጠበቂያችን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- አሠራርን ዘመናዊ ማድረግ ለፋይናንስ ተቋማት ወሳኝ ነው፡፡ ምን ያህል አሠራራችሁ ዘምኗል?
ወ/ሮ ቅድስት፡- አብዛኛዎቹ የቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበራት የአባላት ቁጥራቸው ሲጨምርና ይህንን በፒችትሪ (የሒሳብ አያያዝ) ማስተዳደር ሲያቅት ወደ ሌላ የአሠራር ሥርዓት ይገባሉ፡፡ እኛም በአሁኑ ሰዓት ባንኮች የሚቀመጡበትን ፔመኖስ (T24) የኮር ባንኪንግ ሲስተም ለመጠቀም ዩኤስአይ ከሚባል ድርጅት ጋር ስምምነት ፈጽመን ሥልጠና እየወሰድን ነው፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሥርዓቱን መተግበር እንጀምራለን፡፡
ሪፖርተር፡- ሴቶችን ታበረታታላችሁ? ምን የተለየ አገልግሎት አላችሁ?
ወ/ሮ ቅድስት፡- ከሴቶች አንፃር የሴቶች ቁጠባ አለን፡፡ ከፍ ያለ ወለድም አለው፡፡ ብድርም ስናበድር ለሴቶች ወለዱ ዝቅተኛ ነው፡፡ 14 በመቶ ነው፡፡ የሴቶች ማበረታቻ ሥልጠናዎች አሉ፡፡ ግንዛቤ የማስጨበጥና የፋይናንስ ዕገዛም አለን፡፡ ክትትልም ይደረግላቸዋል፡፡ ከሌሎች ሴቶች ተሞክሮ እንዲወስዱ ሁኔታዎችን እናመቻቻለን፡፡
ሪፖርተር፡- ሴት ተበዳሪዎችን እንዴት ይገልጿቸዋል?
ወ/ሮ ቅድስት፡- ሴቶች ከወንዶች በተሻለ ኃላፊነት ይወስዳሉ፡፡ ብድር በወቅቱ የመመለስ ነገር እናያለን፡፡ ቁጠባ ላይም የሴቶች ቁጥር ይበልጣል፡፡ ብድር ወስደው ችግር ውስጥ መግባት ስለማይፈልጉም ወዲያው ይከፍላሉ፡፡
ሪፖርተር፡- የኅብረት ሥራ ማኅበራት በተለይ ባንኮች ብዙም ማበደር በማይችሉበት ሁኔታ ያላቸውን ሚና ቢገልጹልን?
ወ/ሮ ቅድስት፡- አሁን ላይ በአገሪቱ ከፍተኛ የጥሬ ገንዘብ እጥረት (የሊኪውዲቲ) አለ፡፡ ስለዚህ ከባንኮች ብድር ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ የቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበራትና ማይክሮ ፋይናንስ ናቸው ብድር የሚሰጡት፡፡ ሰዎች ከእነዚህ ብድር እየወሰዱና እየተጠቀሙበት ብድር እየመለሱና ሌላውም እንዲጠቀም እያደረጉ ነው፡፡ ለምሳሌ ከስድስት ወራት በፊት መኪና የገዙ ሰዎች ከገዙበት ዋጋ እስከ 400 ሺሕ ብር ድረስ የመኪና ዋጋ ጨምሯል፡፡ ቢዝነስ የሌላቸው ገንዘብ ተበድረው የጀመሩና ለሌሎች የሥራ ዕድል የፈጠሩ አሉ፡፡ በተለይ ሴቶች ጥሩ ሥራ እየሠሩ ነው፡፡ ሴቶች ያላገባች ከሆነች እህት፣ ወንድም፣ እናት አባቷን ደግፋ ትሠራለች፡፡ ካገባች ደግሞ ባለቤቷንና ልጆቿን ደገፋ ትሠራለች፡፡ ስለዚህ በይበልጥ መሥራት የምንፈልገው ሴቶች ላይ ነው፡፡ የተማሩ፣ ቢዝነስ የሚሠሩና በዕውቀት የበለፀጉ ሴቶች አሉ ማለት አዎንታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው፡፡ የልጆች ቁጠባም አለ፡፡ እናት ጠንካራ ከሆነች ጎበዝ የሚሠሩ ልጆችን ታፈራለች፡፡ በዚህ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- ወለድ አልባ አገልግሎት አላችሁ?
ወ/ሮ ቅድስት፡- ለሙስሊም ደንበኞቻችን ወለድ አልባ የብድር አገልግሎት መስጠት ጀምረናል፡፡ ይህ ሰዎች እንዲሠሩና እንዲበረታቱ እያደረገ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በዘርፉ ላይ ያሉ ችግሮች ምንድናቸው?
ወ/ሮ ቅድስት፡- የግንዛቤ ችግሮች አሉ፡፡ በማኅበረሰቡ ዘንድ ብዙ ጊዜ የግንዛቤና የመረጃ ክፍተት አለ፡፡ በማይክሮ ፋይናንስና በቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበራት የታቀፈው ሕዝብ አንድ በመቶ አይሆንም፡፡ ስለዚህ ችግሩን መፍታት ያስፈልጋል፡፡ በርካታ ብር ቢኖረንና ከባንኮች ጋር አብረን ብንሠራም ብዙዎች የሚጠቀሙበትና ሕይወታቸውን ሊቀይሩ የሚችሉበትን መንገድ መክፈት እንችላለን፡፡
ሪፖርተር፡- የሌሎች አገሮችን ልምድ እንዴት ይገልጹታል?
ወ/ሮ ቅድስት፡- እስያ ላይ በደንብ ተለምዷል፡፡ ከአፍሪካ ኬንያ ውስጥ ትልልቅ ብድርና ቁጠባ ተቋማት አሉ፡፡ በሚሊዮንና ቢሊዮን ዶላር የሚያንቀሳቅሱ ናቸው፡፡ ለብዙዎች ሥራ መፍጠርና ሕይወት መቀየር ችለዋል፡፡ ሀብት እንዲኖራቸው አስችሏል፡፡ እኛ አገር ትልልቅ ብለን ከምናስባቸው ባንኮች የተሻለ አቅም ያላቸው የቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበራት አሉ፡፡ መንግሥት ዘርፉን ያበረታታል፡፡ ደቡብ አፍሪካና ናይጄሪያ ውስጥም በእነዚህ ተቋማት ትልልቅ ገንዘቦች ይዘዋወራሉ፡፡ የሚጠቀማቸው ማኅበረሰብም በርካታ ነው፡፡ ሀብትም እያካበቱ፣ የሥራ ዕድል እየፈጠሩም ነው፡፡ ከመቀጠር ባለፈም ሠርቶ ማሠራት እንደሚቻል የሰዎችን አስተሳሰብ እየቀየሩ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በምን ያህል ካፒታል ነው የተነሳችሁት?
ወ/ሮ ቅድስት፡- መጀመሪያ የተቋቋመው በ136 ሰዎች ነው፡፡ ራዕዩም አባላትን ሥራ ፈጣሪና መካከለኛ ገቢ ያላቸው የማድረግ ነው፡፡ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የሠለጠነና በሥነ ምግባር የታነፀ የሰው ኃይል ማደራጀት ዓላማችን ነው፡፡ በትንሽ ብር ካፒታል ነበር የተነሳው፡፡ ከተቋቋመ ዓመት ሆኖታል፡፡ በዓመት ውስጥ ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ሰጥቷል፡፡ 16 ሰዎች መኪና ገዝተዋል፡፡ የብድር ጣሪያው ሁለት ሚሊዮን ነው፡፡ ከድንገተኛ ችግር መውጫ ጀምሮ እስከ 1.5 ሚሊዮን ድረስ ተበድረዋል፡፡ ድንገት ለደረሰ ችግር ሐዘን ሊሆን ይችላል፡፡ ገንዘብ ሲያስፈልግ ምንም ዋስትና ሳያስይዙ በጠለፋ ዋስትና ብር መውሰድ ይቻላል፡፡ የወለድ መጠኑ ለመኪና ሲሆን 14.5 በመቶ ነው፡፡ እስካሁን ለቤት መስጠት አልጀመርንም፡፡ እንደ የብድር ዓይነቱ ከአሥር በመቶ ጀምሮ እስከ 14.5 በመቶ ወለድ አለ፡፡
ሪፖርተር፡- አባላት ምን ያህል መቆጠብ አለባቸው?
ወ/ሮ ቅድስት፡- በወር ዝቅተኛው መደበኛ ቁጠባ 750 ብር ነው፡፡ የፈቃድ ቁጠባ ማለት የፈለጉትን ያህል ማስገባትና ማውጣት የሚችሉበትም አለ፡፡ ለብድር 30 በመቶ ቅድሚያ ማስቀመጥ ይጠበቃል፡፡