የ52 ዓመቱ ማላም ባካይ ሳንሃ

ከ 4 ሰአት በፊት

የጊኒ ቢሳው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ልጅ በአገሩ መፈንቅለ መንግሥት ማካሄድ ይችል ዘንድ አለም አቀፍ የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውርን ይመራ ነበር ተባለ።

ግለሰቡ ሄሮይን የተባለውን የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር ሽያጭንም በመምራት የአሜሪካ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ሆኖ አግኘቸዋለሁ ብሎም የስድስት ዓመት እስር ፈርዶበታል።

የ52 ዓመቱ ማላም ባካይ ሳንሃ ከአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር የሚገኘውንም ገንዘብ በመፈንቅለ መንግሥት የጊኒ ቢሳው ፕሬዚዳንት የመሆን ፍላጎቱን ለማሳካት አቅዶ ነበር ሲሉም ባለስልጣናቱ አስታውቀዋል።

ማላም ባካይ ከአውሮፓውያኑ 2009 እስከ ህይወተ ህልፈታቸው 2012 ድረስ ጊኒቢሳውን የመሩት የማካም ባካይ ሳንሃ ልጅ ነው።

ሳንሃ ጁኒየር ከሁለት ዓመታት በፊት ተሞክሮ ከከሸፈው መፈንቅለ መንግሥትም ጋር ግንኙነት አለው ተብሏል።

በአውሮፓውያኑ 2022 በታንዛንያ በቁጥጥር ስር ከዋለ ከሳምንታት በኋላም ለአሜሪካ ተላልፎ ተሰጥቷል።

የፍርድ ሂደቱ የጀመረው ብዙም ሳይቆይ ሲሆን ባለፈው ዓመት መስከረም ላይ በህገወጥ መንገድ መንገድ አደንዛዥ ዕጽ ለማስገባት በማሴር ጥፋተኛ መሆኑን አምኗል።

“ማላም ባካይ ሳንሃ ጁኒየር ተራ ዓለም አቀፍ የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪ ብቻ አልነበረም” ሲሉ የአሜሪካ የፌደራል የወንጀል ምርመራ ቢሮ፣ ኤፍ ቢአይ ወኪል ዳግላስ ዊልያምስ ተናግረዋል።

“ማላም የጊኒ ቢሳው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ልጅ ነው የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውሩንም ሲያካሂድ የነበረው በአገሩ መፈንቅለ መንግሥት አስነስቶ ፕሬዚዳንት መሆን ያስችለው ዘንድ ገንዘቡ ድጋፍ እንዲሆነው ለማድረግ ነው” ብለዋል።

ሳንሃ ጁኒየር ሄሮይንን ከተለያዩ በርካታ አገሮች ወደ ፖርቹጋል እንዲሁም ከአውሮፓ አገራት ወደ አሜሪካ በማስመጣትም ነው ክስ የተመሰረተበት።

ግለሰቡ አሜሪካዊ ዜጋ አለመሆኑንም ተከትሎ የእስር ጊዜውን ካጠናቀቀ በኋላ ከአገሪቱ ሊባረር እንደሚችልም ወኪሉ ተናግረዋል።

“ባካዚንሆ” በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀው ማላም በጊኒ ቢሳው አባቱ በስልጣን በነበሩበት ዘመን የምጣኔ ኃብት አማካሪያቸው ከመሆን በተጨማሪ በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊነቶች ውስጥም ድርሻ ነበረው።

ከሁለት ዓመታት በፊት ፕሬዚዳንት ኡማሮ ሲሶኮ ኢምባሎን ከስልጣን ለማውረድ በተደረገው እና 11 ሰዎች አብዛኛዎቹ የጸጥታ ኃይሎች በተገደሉበት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራም “እጁ እንዳለበት” መግለጹም ተዘግቧል።

ሳንሃ ጁኒየር ለአሜሪካ የመድኃኒት አስተዳደር (ዲኢኤ) ድብቅ ወኪሎች ከአደንዛዥ ዕጽ ያገኘውን ገንዘብ መፈንቅለ መንግሥቱን ለመደገፍ እንዳዋለው መናገሩንም የጀርመን መንግሥት ሚዲያ ዶቸይ ቬለ ባለፈው ዓመት መዘገቡ ይታወሳል።