ትምህርት ቤት

ከ 4 ሰአት በፊት

በፈረንሳይ ትምህርት ቤት ውስጥ አንዲት ሙስሊም ታዳጊ “መምህሬ የጸጉር መሸፈኛ ጨርቄን እንዳወልቅ ጥቃት አድርሶብኛል” ስትል ያቀረበችው ውንጀል ሀሰተኛ ነው ያለው መንግሥት ታዳጊዋን እንደሚከስ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ተናገሩ።

መምህሩ በፈረንሳይ ህግ መሰረት ተማሪዋ ትምህርት ቤት ወስጥ መሸፈኛውን እንድታወልቅ ከመንገር በዘለለ ያደረሰው ጥቃት እንደሌለ ተገልጿል።

በዚህ ምክንያት በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጩ ዛቻዎችን ተከትሎ መምህሩ ስራ ለቋል።

በተመሳሳይ ምክንያት በፈረንሳይ ሁለት መምህራን ከተገደሉ በኋላ በፈረንሳይ ትምህርት ቤቶች የተፈጠረው ስጋት እጅግ የከፋ ሆኗል።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2020 እና ከአምስት ወራት በፊት ሁለት መምህራን ተገድለዋል።

በሰሞነኛው ጉዳይ ሰሙ የተነሳው መምህር ከስራ መልቀቁን ባለፈው አርብ በላከው ኢሜይል ለባልደረቦቹ አሳውቋል።

በመጨረሻም ስራዬን ለማቆም ወስኛለሁ ያለው በስም ያልተጠቀሰው መምህር 45 ዓመታት በትምህርት ዘርፍ ላይ ቆይቷል።

ከአንድ ወር በፊት በጋጠመው በዚህ ክስተት ርዕሰ መምህሩ ሶስት ሴት ተማሪዎችን የጸጉር መሸፈኛችሁን በማውለቅ የፈረንሳይን ህግ ማክብር አለባችሁ ብሏቸዋል።

ሁለቱ ተማሪዎች ለማውለቅ አሸፈረኝ ሲሉ ሶስተኛዋ ግን አውልቃለች። በዚህም ምክንያት በርዕሰ መምህሩ እና በሁለቱ ተማሪዎች መካከል ከፍተኛ ጭቅጭት ተነስቷል።

ትምህርት ቤቱ ጉዳዩን ለሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስቴር አሳውቋል። ከቀጣዩ ቀን ጀምሮ ግን መምህሩ ላይ የግድያ ዛቻ እንደደረሰበት እንደሆነ ተነግሯል።

የግድያ ዛቻ እንዳደረሱ የተጠረጠሩ ሁለት ስዎች መታሰራቸውን አቃቤ ህግ ገልጿል። የተጠርጣሪዎቹ ማንነት ይፋ ባይሆንም ከትምህርት ቤቱ ጋር ግንኙት እንደሌላቸው ትምህርት ሚኒስቴር ገልጿል።

ተማሪዋ በርዕሰ መምህሩ ጥቃት እንደደረሰባት የሚያሳይ ማስረጃ እንደሌለ ፖሊስ ገልጿል። ሀሰተኛ ውንጀላ በማቅረብ ክስ እንደሚመሰረትባት የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋብሬል አታላ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሯ መንግስታቸው ህግን ከሚጥሱት ጋር ከሚጋፈጡ ሰዎች ጎን ይቆማል ሲል ተናግረዋል።

በሀገሪቱ የሚገኙ የቀኝ እና ግራ ዘመም ፖለቲከኞች በኢንተርኔት አማካኝነት በደረሰ ማስፈራረሪያ አንድ መምህር ስራ እንዲያቆም በመገደዱ የተሰማቸውን ቅሬታ እየገለጹ ነው።

በሌላ ዜና በፓሪስ የሚገኙ በርካታ ትምህርት ቤቶች ጽንፈኞች ያደርሱታል ተብሎ በታሰበው የቦምብ ጥቃት ምክንያት ትላንት ረቡዕ ዝግ ሆነው ለመዋል ተገደዋል።

ባለፈው ሳምንትም በፓሪስ 30 ትምህርት ቤቶችም ተመሳሳይ ዛቻ ደርሷቸዋል።

የጸጥታ አካላት ጉዳዩን በከፍተኛ ሁኔታ እየተከታተሉት ቢሆንም የሩስያ የሀሰተኛ መረጃ አካል ሊሆን እንደሚችልም ተጠርጥሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኣታላ የሩስያ መንግሥት ፈረንሳይ ለዩክሬን ባላት ድጋፍ ምክንያት ከፍተኛ የሀሰተኛ ዘመቻ እንደጀመረች ተናግረዋል።