የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች

ከ 1 ሰአት በፊት

በዩናይትድ ኪንግደም ከአምስት መምህራን ቢያንስ አንዳቸው በተማሪዎቻቸው መመታታቸውን ቢቢሲ ያደረገው የዳሰሳ ጥናት አስታወቀ።

በመማር ማስተማሩ ሂደት ከተማሪዎች ጋር “መቋጫ የሌለው ትግል እናደርጋለን” ሲሉም ባህርያቸው እየከፋ መሆኑንም አንድ መምህር ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ተማሪዎች ወንበር መወርወር፣ ምራቅ መትፋት እና ስድብ መሳደብ በተደጋጋሚ የሚያደርጓቸው ክስተቶች ናቸው ብለዋል።

በተለይም ከኮቪድ ወረርሽኝ ወዲህ ተማሪዎች እርስ በርስም ሆነ በመምህኣረን ላይ የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች በከፋ ሁኔታ እየተባባሰ መሆኑንምየደረሳቸውንም ሪፖርት በማድረግ ማህበሩ ገልጿል።

የዩኬ የትምህርት ዲፓርትመንት በበኩሉ በትምህርት ቤቶች ያሉ የባህርይ ማዕከላትን ለመደገፍ 10 ሚሊዮን ፓውን አውጥቻለሁ ብሏል።

ቲቸር ታፕ የተሰኘ አንድ መተግበሪያን በመጠቀም ቢቢሲ ኒውስ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የሚገኙ እስከ 9 ሺህ የሚደርሱ መምህራንን የተማሪዎቻቸውን ባህርይ በተመለከተ ጥያቄ አቅርቦላቸዋል።

በዚህም ጥናት መሰረት 15 በመቶ የሚሆኑት መምህራን በሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የወሲብ ትንኮሳዎች በትምህርት ቤት ውስጥ እንደደረሰባቸውም ተናግረዋል።

የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ መምህራን በሰጡት ምላሽ ከሁለት ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጻር በተማሪዎች መካከል መጣላት፣ መገፋፋት እና ሌሎች አስከፊ ባህርያት እያዩ መሆኑን ሪፖርት አድርገዋል።

በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ለ35 ዓመታት ያስተማረችው ሎሬይን ሜህ የተማሪዎች ባህርይ እየከፋ መሄዱን ትናገራለች።

አምስት እና ስድስት ዓመታቸው የሆኑ የአጸደ ህጻናት ተማሪዎች ምራቅ መትፋት እና መሳደብን ጨምሮ መጥፎ እና አደገኛ የሆኑ እንደ ወንበር መወርወር ባህርይ እንደሚያሳዩም ይገልጻሉ።

“በአንድ መማሪያ ክፍል ውስጥ ቢያንስ 3 ወይም አራት ተማሪዎች እንዲህ አይነቶቹን ፈታኝ ባህርያት ያሳያሉ። በክፍል ውስጥ ከ30 በላይ ተማሪዎችን መቆጣጠር ከባድ ነው” ስትልም መምህሯ ታስረዳለች።

ሚድላንስድ በተሰኘ ትምህርት ቤት መምህር የሆነው ዛክ ኮፕሌይ የተማሪዎች ባህርይ በእርግጠኝነት እየከፋ መሄዱን እና “የማይቋጭ ትግል” ነው ሲልም አስረድቷል።

በአንድ ወቅት ተማሪዎች እርስ በርስ በቡጢ ሲደባደቡ የመማሪያ ክፍሉ ግድግዳ እንደፈረሰ ይኸው የኮምፒውተር ሳይንስ መምህር ያስረዳል።

ከክፍል እንዲወጡ የተደረጉ ሌሎች ተማሪዎች ደግሞ የክሪኬት መጫወቻ ዱላ ይዘው ክፍሉን ሰብረው ለመግባት እየሞከሩ እንደነበር ገልጿል።

የመምህራን ማህበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት ዶክተር ፓትሪክ ሮአች በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በተመለከተ መምህራን ሪፖርቶች የሚያደርጓቸው ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩንም ነው የገለጹት።