ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርአያ
የምስሉ መግለጫ,ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርአያ

ከ 5 ሰአት በፊት

“እጅግ መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ አካታች ምክክሮችን በማካሄድ የተሻለ አገራዊ መግባባትን መገንባት”ን ሰንቆ የተቋቋመው የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራውን ከጀመረ ድፍን ሁለት ዓመታት አልፈዋል።

በእነዚህ ጊዜያትም ኮሚሽኑ ሥራዎቹን ‘ቅድመ ዝግጅት፣ ዝግጅት እና የምክክር ምዕራፍ’ በሚል ከፋፍሎ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጿል።

ከትግራይ ክልል ውጪ እና ግጭት ባለባቸው የአማራ እና የኦሮሚያ ክልልች አንዳንድ አካባቢዎችን ሳያካትት በ10 ክልሎችን እና የከተማ አስተዳደሮች ለምክክሩ የሚሳተፉ አካላትን ልየታ ማካሄዱን ለቢቢሲ ተናግሯል።

ኮሚሽኑ ለልዩነቶች እና አለመግባባቶች ምንጭ ናቸው በተባሉ ጉዳዮች ላይ ለሚያደርገው ምክክር ተሳታፊዎችን ከታች የማኅበረሰቡ ክፍል ነው የሚለየው።

ነገር ግን አንዳንዶች በአገሪቱ የሚታዩ አብዛኞቹ አለመግባባቶች እና ችግሮች ምንጫቸው ‘ሊሂቃኑ’ በመሆናቸው ምክክሩ መጀመር ያለበት ከእነሱ ሊሆን ይገባል የሚሉ አሉ።

ለዚህም እንደምክንያቱ የሚጠቅሱት በተለያዩ አካባቢዎች የሚካሄዱ ትጥቅ እንቅስቃሴዎችን ነው። ስዚህም ንግግሩ እነዚህን ቡድኖች ሳያካትት መካሄዱ እንቅፋት ሊፈጥር ይችላልም ይላሉ።

በአገሪቱ ባሉ ሁኔታዎች ምክንያት ሥራው የዘገየበት ኮሚሽኑ ግን፤ ከመንግሥት ጋር የትጥቅ ግጭት ውስጥ የገቡ ታጣቂ ቡድኖች “ነፍጣቸውን ወደ ጎን አድርገው” እንዲነጋገሩ እየወተወተ ነው።

ኮሚሽኑ ለመነጋገር ፈቃደኛ ለሆኑ ታጣቂዎች ደኅንነታቸውን ለመጠበቅ “የሰላም መንገድ” እንደሚያመቻች ለቢቢሲ ተናግሯል።

“ምክክሩ ‘ከልሂቃን’ ጋር መሆን ነበረበት”

የኢትዮጵያን ችግሮች ውስብስ ሲሉ የሚገልጿቸው አንዳንድ ወገኖች በኮሚሽኑ አካሄድ ጥያቄ አላቸው። በተለይም ኮሚሽኑ የተሳታፊ ልየታውን ከማኅበረሰቡ መጀመሩ “የችግሩን ቁልፍ እንዳለመለየት” የታየበት ሲሆን፤ “አካሄዱ ኢላማውን ያስተዋል” በሚል ትችት ይቀርብበታል።

ለዚህም የሀሳብ ልዩነቶች እና አለመግባባቶች በአመዛኙ ከልሂቃን እንደሚነሱ በመጠቆም ምክክሩ ‘ከችግሩ ባለቤት’ ከላይ [ከሊሂቃን] መጀመር ነበረበት የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ።

እንደዚህ ዓይነት ጥያቄዎች ከተለያዩ አካላት እንደሚደርሳቸው የሚያነሱት ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርአያ ኮሚሽኑ ይህን ቢያደርግ “ሥራው ይቀልለት ነበር” ይላሉ። ዋና ኮሚሽነሩ ሊሂቃኑ የችግሮች ምንጭ መሆናቸው “ሳይታለም የተፈታ ነው” ቢሉም ምክክሩ በልሂቃን ብቻ እንዳይካሄድ ማቋቋሚያ አዋጁ እንደሚገድባቸው ተናግረዋል።

“ስድስት አጀንጃዎች ላይ ጉልበት ያላቸውን፣ ልሂቃን ነን፤ ምሁራን ነን የሚሉትን መርጦ አሰባስቦ እዚህ ላይ ተወያዩ ማለት ይቻላል። ለእኛ በጣም ይቀለንም ነበር። እስካሁንም ብዙ መሄድ እንችል ነበር” ብለዋል።

ነገር ግን [የማቋቋሚያ] አዋጁ 1265/2014 ዋና ዓላማው፤ መርሆቹ አካታችነት፣ ግልጽ መሆን፣ ተኣማኒነት፣ መቻቻል እና መከባበር፣ ምክንያታዊነት፣ ገለልተኛ አመቻችነት… መቀመጣቸውን በመጥቀስ የትኩረታቸውን ምክንያት ገልጸዋል።

“ስለዚህ አካታችነትና ግለጸኝነት ወይም አሳታፊነት ከተባለ ምሁራንን፣ ልሂቃንን፣ ፖለቲከኞችን ብቻ ብሎ አዋጁ ስላላስቀመጠ፤ ሁላችንንም ኢትዮጵያውያን ማለት [ነው]” ሲሉ ምላሽ ይሰጣሉ።

ገፈት እየቀመሰ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ አጀንዳ አለው የሚሉት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ከልሂቃን ከሌሎች ክፍሎች ጋር ይወያዩ ማለት “ዲሞክራሲያዊ አካሄድ” ነው ይላሉ።

“. . . ሕዝቦች ኢትዮጵያውያን ነን ብለው መቀጠል ካለባቸው በሚኖረው ማኅበራዊ የጋራ ውል ውሳኔ ላይ ሙሉ ተሳትፎ ሊኖራቸው ይገባል” በማለት መከራከሪያ ያቀርባሉ።

ከሁሉም የተውጣጡ እርሳቸው “ከልሂቅ እስከ ደቂቅ” ካሏቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች በተመረጡ እና ቅድሚያ በሚሰጣቸው አጀንዳዎች “በእኩልነት” በጋራ በብሔራዊ ምክክር ጉባኤው ይወያያሉ ብለዋል።

“ሶማሌ ዳር ያለው አርብቶ አደር፤ ዛላምበሳ ካለው አርሶ አደር ጋር እኩል መክሮ፤ ኢትዮጵያ ስለምትባለው አገር በጋራ ምግባባት ላይ ይደርሳል ማለት ነው” ሲሉ የኮሚሽኑን አካሄድ “ሁሉንም ያቀፈ” ብለው የሚገልጹት ፕ/ር መሥፍን፤ ልሂቃንን ግን የገፋ አይደለም ይላሉ።

ታጣቂ ኃይሎች እና ምክክሩ

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን “ሁሉም አሸናፊ ይሆንበታል” ለሚለው ምክክር ከታጣቂ ኃይሎች ጋር የመነጋጋገር ፍላጎት እንዳለው በተደጋጋሚ ቢገልጽም፤ ለዚህ ውይይት ግን ታጣቂዎች ‘ነፍጥን ማስቀመጥ’ አለባቸው ብሏል።

“አንቺም ‘ክላሽንኮቭሽን’ እኔም ‘ማካሮቬን’ ይዤ አወያይ ይዘን በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ አንልም። ይሄ የታወቀ ነው። ስለዚህ ትጥቅን ወደ ጎን እናድርገው እና ለምክክሩ ለመግባባቱ ዝግጁ ሆነን ወደ ምክክሩ ቦታ እንምጣ” በማለት ስለ ታጣቂዎች እና ምክክሩ ያነሳሉ።

ምክክር በመጀመሪያ “የሰላም መንፈስ” ያስፈለገዋል የሚሉት ዋና ኮሚሽነር መሥፍን፤ ትጥቅን ወደ ጎን በማድረግ ለመግባባት ዝግጁ መሆን አስፈላጊ መሆኑንም ያሰምራሉ። ለምክክሩ ውጤትም ታጣቂዎችን ጨምሮ የሁሉም አካላት ተሳትፎ ወሳኝ ነው የሚል እምነት አላቸው።

ይሁን እንጂ ታጣቂዎች ነፍጣቸውን አውርደው ለመነጋገር ከመንግሥት ስጋት እንዳለባቸው ያነሳሉ።

ኮሚሽኑም እስካሁን ጥሪውን ተቀብለው የመጡ ታጣቂ ኃይሎች እንደሌሉ ተናግሯል። በቅርቡ ከመንግሥት ጋር ስምምነት ላይ የደረሰው እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚንቀሳቀስ ቡድን (ጉሕዴን) ጋር መነጋገራቸውን ግን ጠቅሰዋል።

“አዲስ አበባ ቁጭ ብሎ ታጣቂዎችን ማግኘት የሚቻል ነገር አይደለም። ይሄን ለማድረግ ከታጣቂዎችም በኩል ፈቃደንኝቱ መኖር አለበት። በእኛ በኩል ምንጊዜም ፈቃደኝነት አለ። በዚህ ሁኔታ የት ጋ እንደምንገናኝ፣ የት እንደምንነጋገር፣ እንዴት ወደ ምክክር መምጣት እንደሚቻል፣ ከመንግሥት ጋር የተያያዙትን ደረጃ በደረጃ የምንፈታቸው ነው የሚሆነው” ይላሉ።

ኮሚሽኑ ከታጣቂዎች ጋር ተገናኝቶ ለመነጋገርና ስጋቱን ለመቅረፍ “የሰላም መንገድ” (ደኅንነት ዋስትና) እንደሚያመቻች ፕ/ር መሥፍን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“በሰላም ወደ ምክክሩ መጥቶ፤ ተሳትፎ ወደ መግባባት በሚኬድበት ሂደት ውስጥ በመንግሥት በኩል፤ በሕጉ በኩል የሚደረጉ ጫናዎች ካሉ አዋጁ በሰጠን ሥልጣን መሠረት ከመንግሥት ጋር ተነጋግረን የሰላም መንገድ የሚባለውን ነገር ማመቻቸት እንችላለን” ብለዋል።

“አገሪቱ ምን እስክትሆን ነው የሚጠብቀው?”

አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሲመሠረት ኢትዮጵያ “ደም አፋሳሽ” በሚባል ጦርነት ውስጥ ነበረች። አሁንም በተለይ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የትጥቅ ግጭት እየተካሄደ ነው።

ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም አገራዊ ምክክሩ የሚጀምርበትን ቀን ቆርጦ ቢያሳውቅም እንደወጠነው ሳይሆን ቀርቷል።

የቀጠሉ ግጭቶች ኮሚሽኑ ሥራውን እንዳያከናውን መሰናከል እንደሆኑበትም በተደጋጋሚ አንስቷል።

ምክክር ከሚያስፈልግባቸው ምንያቶች ውስጥ የሰላም እጦትን ለመፍታት እንደሆነ የሚያነሱት ፕ/ር መሥፍን፤ ‘አገሪቱ ምን እስክትሆን ነው የሚጠበቀው?’ ለሚለው የበርካቶች ጥያቄ መልስ አላቸው።

ምክክሩ መዘግየቱን የሚያምኑት ዋና ኮሚሽነሩ፤ “በዕቅዳችን መሠረት ብንሄድ ኖሮ በዚህ ዓመት አገራዊ ምክክሩ እየተካሄደ፤ ብዙ አጀንዳዎች ወደ መግባባት ተደርሶባቸው፤ ባላግባቡት ላይ ደግሞ ሌሎች አካሄዶች እንዲጠበቁ ተደርጎ መሄድ ይቻል ነበር። ነገር ግን ዘግይቷል” ብለዋል።

“ከእኛ አቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮች አሉ” በማለት በአገሪቱ ያሉ ግጭቶች እንቅፋት እንደሆኑ የሚያነሱት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ሁኔታው ውሳኔ የሚፈልግ ነው ይላሉ።

የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ በብዙዎች የሚጠበቀውን አገራዊ ምክክር ለማድረግ የሚያስችል ቀን ለመቁረጥ ፈታኝ እንዳደረገውም ፕ/ር መሥፍን አንስተዋል።

“በዚህ ጊዜ እንጀምራለን ቢባል [የአገሪቱ ሁኔታ] በጣም ተቀያያሪ ነው። ይሄ በደንብ መታየት እና መፈተሽ አለበት” ሲሉ ኮሚሽኑ ቀን ለመቁረጥ ስለመቸገሩ ተናግረዋል።

“ተቃውሞው ዳር ሆኖ ቆሞ ማየት ነው”

የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቃውሞ የገጠመው ገና ከጥንስሱ ነበር። የኮሚሽነሮች ምርጫ ውዝግብ ያስነሳ ሲሆን፣ በተለይም የገለልተኝነት ጥያቄ አሁን ድረስ ይነሳበታል።

ኮሚሽኑ በተቋቋመ ማግስት ጥቂት የማይባሉ የሚቆጠሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች “የተቃዋሚ ፓርቲዎች ኮከስ” በመመሥረት ኮሚሽኑን ከአመሠራረቱ ጀምሮ እስከ ሂደቱ ኮንነዋል።

ዋና ኮሚሽነር ፕ/ር መሥፍን የገለልተኝነት ጥያቄ እንደሚነሳባቸው ገልጸው፤ ነገር ግን ከአፍ ባለፈ በማስረጃ መቅረብ አለበት ይላሉ።

“ዝም ብሎ በገደምዳሜው እነከሌ እንዲህ ነበሩ፤ እንደዚያ ነበሩ እየተባለ፤ እንዲያውም አልፎ ተርፎ ከእኛ ጋር የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለመከፋፈል ይጥራሉ” በማለት ወቅሰዋል።

እንደ ኦነግ እና ኦፌኮን የመሰሉ ፓርቲዎች የሚያነሱት ተቃውሞ በምክክር ሂደቱ ቅቡልነት እና ውጤታማነት ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል ተብለው የተጠየቁት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ተጽዕኖውን ሳይደብቁ ሕዝቡ ላይ ማተኮራቸውን ገልጸዋል።

“እንኳን እነኚህ ትልልቅ ፓርቲዎች ይቅርና ትንሽ እንኳ የማኅበረብ ክፍል በዚህ ምክክር ውስጥ አለመካተቱ፤ አለመካፈሉ ተጽዕኖ አለው” የሚሉት ፕ/ር መሥፍን፤ ፓርቲዎቹ ፍላጎት ከሌላቸው እንዲሳተፉ ማስገደድ እንደማይችሉ ተናግረዋል።

“በየሄድንበት ቦታ ሁሉ ‘ሰላም እንፈልጋለን፤ ግን ፖለቲከኞቻችን እንዴት ነው ወደ መድረኩ የሚመጡት?’ የሚል ጥያቄ እኛንም ይጠይቁናል። ይሄን ጥያቄ እኛ ወደ እነርሱ ነው የምንመልሰው። ለምን? በእኩልነት የሚፈልጉትን ነገር ኮሚሽኑ ውስጥ ገብቶ አብሮ በማገልግል፤ ይሄ ምክክር ለሁላችንም እኩል ውጤት እንዲያመጣ ማድረግ ይችላሉ” በማለት የፖለቲከኞችን አቋም “ዳር ሆኖ ቆሞ ማየት ነው” በማለት ዋና ኮሚሽነሩ ይገልጹታል።

ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ አምስቱ አባላት ከእኛ ጋር ለመሥራት ዝግጁ ሆነዋል ያሉ ሲሆን፤ ኮሚሽኑ ከ40 በላይ ከሆኑ ፓርቲዎች ጋር በቅርበት እሠራ ነው ብለዋል።

ኮሚሽኑ በተሰጠው ጊዜ ሥራውን ይጨርሳል?

ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሆነው የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በማቋቋሚያ አዋጁ የሥራ ዘመኑ ሦስት ዓመት እንደሆነ ያትታል።

የሥራ ዘመኑ የሚጀምረውም የኮሚሽነሮች ሹመት ከጸደቀበት የካቲት 14/2014 ዓ.ም. አንስቶ ሲሆን፣ ሁለተኛ ዓመቱን ባለፈው ወር ደፍኗል። ስለዚህም ኮሚሽኑ የቀሩ ሥራዎቹን በቀረው ጊዜ ማጠናቀቅ ይችል ይሆን የሚለው የሚነሳ ሌላ ጥያቄ ነው።

ዋና ኮሚሽነር ፕ/ር መሥፍን አርአያ ግን በአገሪቱ ውስጥ ባጋጠሙ እና እያጋጠሙ ባሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች ምክንያቶች ሥራው የተጓተተበት አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጊዜ የሚጠበቅበትን ያከናውናል ይላሉ።

“እንደ ማንኛውም የትምህርት የመጨረሻ ቀን እንደተቆረተለት ተማሪ ለሦስት ዓመት ተመድበናል። በሦስት ዓመት ሥራችንን አገባደን ለመውጣት እየሰራን ነው። ስለዚህ በቀሪ ጊዜያት አጀንዳ መሰብሰብ እንጀምራለን” ብለዋል።

ፕ/ር መሥፍን ከቀረው ጊዜ አንጻር የምክክር ምክረ ሃሳቦችን ገቢራዊነት ግን በእርግጠኝነት ለመከታተል ጊዜ እንደሚያጥራቸው ጠቁመዋል።

“አዋጁ ላይ እንደተቀመጠው የምክክር ሃሳቦችን ለተግባሪ አካላት ሰጥቶ፤ አስተግብሮ ለሕዝቡ ሪፖርት የምናደርግበት ጊዜ ግን የቀረው ጊዜ እጅግ አጭር ከመሆኑ የተነሳ ይህን ሥራ እንተገብራለን ብዬ አላምንም” ብለዋል።

በማቋቋሚያ አዋጁ ኮሚሽኑ ከተሰጡት ተግባር እና ኃላፊነቶች መካከል “. . .በምክክሮቹ የተገኙ ምክረ ሃሳቦችን እንዱሁም ምክረ ሃሳቦቹ በተግባር ላይ ሊውሉ የሚችሉበትን ስሌት የሚገልጽ ሰነድ በማዘጋጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለአስፈጻሚ አካላት እና ለሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ያቀርባል፤ ለሕዝቡም ይፋ ያደርጋል” ይላል።

አዋጁ ጨምሮም ኮሚሽኑ “የምክረ ሃሳቦቹን አፈጻጸም መከታተል የሚያስችል ሥርዓት ይዘረጋል” በማለት ኃላፊነት ሰጥቶታል።