ራያ አላማጣ

27 መጋቢት 2024

የአማራ እና ትግራይ ክልሎች ይገባናል በሚሉት የራያ አላማጣ ወረዳ ሰኞ ዕለት በተከሰተ ግጭት የአራት ሚሊሻዎች ሕይወት መጥፋቱን የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ተናገሩ።

መጋቢት 16/2016 ዓ.ም. በተፈጠረው ግጭት ከሞቱት በተጨማሪ ሌሎች አስራ ሁለት ሰዎች ደግሞ ቀላል እና ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው አስተዳዳሪው አቶ ሞላ ደርበው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሃብቱ ኪሮስ በበኩላቸው “ግጭት የሚባል ነገር የለም። የት አካባቢ የተፈጠረ ግጭት እያሉ እንደሆነ አላውቅም” ሲሉ አስተባብለዋል።

አቶ ሃብቱ ይሄን ቢሉም የራያ አላማጣ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሞላ ግን ከሰኞ ምሽት አራት ሰዓት ጀምሮ እስከ ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ስምንት ሰዓት የነበረውን ግጭት “የህወሓት ታጣቂዎች” ጀምረውታል ሲሉ ከሰዋል።

ዋና አስተዳደሪው ክስቱን ሲያያረዱ “ሰኞ ከአራት እስከ ስድስት ሰዓት ወደ ተራራው ተጠጉ። እኛም ኃይል አስጠግተን አደርን ትናንት እስከ ስምንት ሰዓት ድረስ ውጊያ ላይ ነበርን” ይላሉ።

ግጭቱ ከመጀመሩ በፊትም፤ “ከእኛ ድንበር በ150 ሜትር ርቀት ላይ ምሽግ ቆፈረዋል” ሲሉ ያክላሉ ዋና አስተዳዳሪው።

ይህን ክስተት በአካባቢው ለሚገኙ የመከላከያ ሠራዊቱ ማስታወቃቸውን የሚገልጹት አቶ ሞላ፣ በጊዜ ምላሽ አለማግኘታቸውን አመልክተዋል።

አክለውም፤ “እንደዚህ ዓይነት ችግር ሲፈጠር እንዲቆም የሚቆጣጠሩ፤ ኬላ የሚጠብቁ መከላከያ ሠራዊት አባላት አሉ። ይሄን አካባቢ እየመራ ላለው ለሚመለከተው ለመከላከያ ሠራዊት ቢነገረውም እነሱን [የህወሓት ታጣቂዎችን] ሊያስቆማቸው አልቻለም” ይላሉ።

ይህን ተክተሎም “የሚመለከተው አካል ብናስታውቅም ሊደርሱ ስላልቻሉ፣ የወረዳው ሚሊሻ ያለውን መሳሪያ ይዞ ነው የገባው። ከገባ በኋላ ኃይለኛ ተኩስ ተደረገ” በማለት ጥቃት የተከፈተው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ ነው ብለዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ከትላንት በስቲያ ሰኞ ባወጣው መግለጫ፤ የአማራ ክልል በመማሪያ መጽሐፍት ላይ በታተመው ካርታ ላይ በአስቸኳይ ማስተካከያ እንዲያደርግ ጠይቋል።

ጨምሮም ክልሉ ይህንን የማስተካከል እርምጃ የማይወስድ ከሆነ “በቀጣይ ለሚፈጠር ችግር የአማራ ክልል ሙሉ ኃላፊነቱን ይወስዳል” ሲል ጊዜያዊ አስተዳደሩ ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ አውጥቶ ነበር።

ካቢኔው መግለጫውን ያወጣው፤ የአማራ ክልል ሁለቱ ክልሎች ይገባናል የሚሏቸው እና በአማራ ክልል ቁጥጥር ስር የሚገኙ አወዛጋቢ ቦታዎችን ያካተተ ካርታ የታተመበት የመማሪያ መጽሐፍት ማሳተሙን ተከትሎ ነው።

አቶ ሞላ “ይህንን መግለጫ ተከትለው የአርሚ 24 ሙሉ ኃይል ነው የተሰለፈው” ይላሉ። አስተዳዳሪው “መንግሥት ምንም እንኳን መሳሪያ አስረክበዋል ኃይልም ተበትኗል ቢልም በመካናይዝድ ደረጃ ክፍለ ጦር ደረጃ አላቸው” ሲሉ ያክላሉ።

እንደ አቶ ሞላ ገለጻ ሰኞ ወደ ራያ አላማጣ ወረዳ ተጠጋ ያሉት “አርሚ 24” በወረዳው ታኦ እና አዲስ ብርሃን የተባሉ ቀበሌዎችን ተቆጣጥሯል።

የትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን ዋና አስተዳዳሪው አቶ ሃብቱ ግን፤ “እነሱ አስበው ከሆነ አላውቅም። አሁን እያሉ ካለው መነሻ አድርገው ምን ይፈጠር ይሆን የሚለውን አላውቅም። እስካሁን ግን የተፈጠረ አዲስ ነገር የለም” ብለዋል።

የህወሓት ታጣቂዎች በሁለቱ ቀበሌዎች “እስከ 12 ኪሎሜትር ገብተዋል” የሚሉት አቶ ሞላ ግን ግጭት ከመኖሩም አልፎ አራት ሚሊሻዎች በተኩስ ልውውጡ መሞታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ከሞቱት ሚሊሻዎች በተጨማሪ ሌሎች 12 ሚሊሻዎች ቆስለው ህክምና ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል። ከእነዚህ ሚሊሻዎች መካከል ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሦስቱ ለተሻለ ህክምና ወደ አዲስ አበባ “ሪፈር” መባላቸውንም አክለዋል። ቀሪዎች ደግሞ በአላማጣ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በአካባቢው ያለው ግጭት እስከ ትላንት [ማክሰኞ] እኩለ ቀን ድረስ ከቀጠለ በኋላ የመከላከያ ሠራዊት ጣልቃ ገብቶ የተኩስ ልውውጡ እንደቆመ አቶ ሞላ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ነገር ግን የራያ አላማጣ ወረዳ ስር ናቸው ያሏቸውን ቀበሌዎች አሁንም በህወሓት ታጣቂዎች ስር ናቸው ብለዋል።

የአማራ እና ትግራይ ክልሎች በሚወዛገቡባቸው አካባቢዎች ውጥረት ሲነግስ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ከአንድ ወር በፊት የካቲት አጋማሽ ላይም ተመሳሳይ ውጥረት ነግሶ ነበር። ከራያ አካባቢዎች መካከል አንዱ በሆነው የዛታ ወረዳ የነበረው ውጥረት የተኩስ ልውውጥ ድረስ የዘለቀ ነበር።

በራያ አካባቢ የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎች ወፍላ ወረዳ፣ ዛታ ወረዳ፣ ኮረም ከተማ፣ አላማጣ ከተማ፣ አላማጣ ወረዳ እና ራያ ባላ ወረዳ ናቸው።

የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት መቀስቀስ ተከትሎ እነዚህ አካባቢዎች የአማራ ክልል ተቆጣጥሮ እያስተዳደራቸው ይገኛል።

የፌደራል መንግስቱ ከሁለት ወራት በፊት ጥር መጨረሻ ባወጣው መግለጫ፤ “የአከራካሪ ቦታዎችን ሁኔታ በዘላቂነት ለመፍታትም በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ ጉዳዩ በዋናነት ከሚመለከታቸው ከአማራ እና ከትግራይ ክልሎች ጋር መግባባት ተደርሶ ነበር” ማለቱ ይታወሳል።

ይህ የፌደራል መንግሥቱ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በኩል ተቃውሞ ገጥሞታል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት በኩል የወጣውን መግለጫ “ፍጹም የተሳሳተ” ሲል ማስተባበሉ ይታወሳል።