ለተቃውሞ የወጡ የታጋች ቤተሰቦች

ከ 4 ሰአት በፊት

ታጋቾችን ለማስፈታት የሚካሄደው ንግግር አለመሳካቱን ተከትሎ ለተቃውሞ ወደ ቴል አቪቭ አደባባዮች ወጥተው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል የታጋች ቤተሰቦች እንደሚገኙበት ታውቋል።

አንዳንድ የቤተሰብ አባላት እና የመብት ተሟጋቾች በሐማስ ቁጥጥር ስር የሚገኙትን ታጋቾች ለማስፈታት የበለጠ እንዲሠራ በመጠየቅ ማክሰኞ ምሽት የከተማዋን ዋና መንገድን በብረት አግዳሚዎች ለመዝጋት ሞክረዋል።

ተደራዳሪዎች ከኳታር ከተመለሱ በኋላ ጥያቄያቸው ተስፋ አስቆራጭ እየሆነ መጥቷል።

አንድ የእስራኤል ባለስልጣን በተዘዋዋሪ ሲካሄድ የቆየው ውይይት “ውጤት አልባ ደረጃ ደርሷል” ብለዋል።

ከቀሪዎቹ 130 ታጋቾች መካከል 40ዎቹን ለማስለቀቅ እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን ጥቃት ለስድስት ሳምንታት እንድታቆም ለማድረግ አሸማጋዮች ሲሞክሩ ነበር። እስካሁን ቢያንስ 30 ታጋቾች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ይታሰባል።

ማክሰኞ ቴል አቪቭ በሚገኘው የእስራኤል ጦር ዋና መሥሪያ ቤት ደጃፍ በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ 300 ያህል ሰዎች ተሳትፈዋል። የተወሰኑት ራሳቸውን በብረት ፍርግርጎች ውስጥ በማሰር፣ የተወሰኑት ደግሞ “የትኛውም ዋጋ ውድ አይደለም” የሚል መፈክር ይዘው ታይተዋል።

“ሁከት መፈጠሩን” ተከትሎ የእስራኤል ፖሊስ አራት ተቃዋሚዎችን ማሰሩን ገልጿል።

“ፖሊስ አስፈላጊውን የጥንቃቄ እርምጃ በመውሰድ አንዳንድ የታጋች ቤተሰቦች ህጋዊ ባይሆንም ተቃውሞ እንዲያደርጉ ፈቅዷል” ሲል መግለጫው አክሎ ገልጿል።

“ሆኖም አንዳንድ ተቃዋሚዎች ወደ አያሎን አውራ ጎዳና በመግባት የትራፊክ ፍሰትን በመዝጋት አሽከርካሪዎችን እና እራሳቸውን ለአደጋ ዳርገዋል” ብሏል።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥ ሁለቱ የ79 ዓመቱ ታጋች አቭረሃም ሙንደር ዘመዶች መሆናቸውን የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የታጋቹ የወንድም ልጅ ሆነው ሻሃር ሞር ዛሂሮንን በቁጥጥር ስር ከዋሉት አንደኛው ሲሆን ከሦስት ሰዓታት እስር በኋላ መለቀቁን ከፖሊስ ጣቢያ ደጃፍ ሆኖ ባሰራጨው ቪዲዮ አረጋግጧል።

ሙንደር ከባለቤታቸው ሩት፣ ከልጃቸው ከረን እና ከልጅ ልጃቸው ኦሃድ ጋር ታግተው የተወሰዱት የሐማስ ተዋጊዎች መስከረም መጨረሻ ወደ ደቡብ እስራኤል ዘልቀው በመግባት አንድ ሺህ 200 የሚጠጉ ሰዎችን ሲገድሉ እና 253 ታጋቾችን በያዙበት ወቅት ነው።

በህዳር ወር ለአንድ ሳምንት በዘለቀ የተኩስ አቁም ስምምነት ወቅት ሩት፣ ከረን እና ኦሃድ ተፈትተዋል። በተኩስ አቁም ስምምነቱ መሰረት 105 ታጋቾች በሐማስ ሲለቀቁ እስራኤል በምላሹ እስር ላይ የነበሩ 240 ህጻናት እና ሴቶች ፍልስጤማውያን ፈታለች።

የእስራኤል ተቃዋሚ መሪ ያየር ላፒድ መንግስት “ለታጋች ቤተሰቦች የበለጠ ርህራሄ እና ድጋፍ ማሳየት አለበት” ብለዋል።

ኤክስ ላይም “እነሱ እና ቤተሰቦቻቸው ሰሚ አጥተዋል። ትግላቸው ከሁሉም የበለጠ ትክክለኛ ትግል ነው። ዝቅተኛው ሊደረግላቸው የሚገባው ነገር ጩኸታቸውን እንዲያሰሙ መፍቀድ ነው” ሲሉ ጽፈዋል።

የታጋች ቤተሰቦች በየቀኑ በሚባል ደረጃ ሰልፎችን ሲያካሂዱ ቆይተዋል። የእስራኤል ባለስልጣናት ልዑካቸው በኳታር፣ በግብጽ እና በአሜሪካ አሸማጋይነት በዶሃ ሲያደረግ ከነበረው ውይይት እንዲመለስ በማድረጋቸው ጭንቀታቸው ተባብሷል።

ለሞሳድ ዳይሬክተር ዴቪድ ባርኔያ (የእስራኤልን ተደራዳሪ ቡድን እየመሩ ናቸው) ቅርብ የሆነ አንድ የእስራኤል ከፍተኛ ባለስልጣን ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደገለጹት በሐማስ ጥያቄ ምክንያት ድርድሩ “ፈቀቅ ከማይልበት ደረጃ ደርሷል” ብለዋል።

እስራኤል በ40 ታጋቾች ምትክ የምትፈታቸውን ፍልስጤማዊያን እስረኞች ቁጥር በእጥፍ በማሳደግ 700 ወይም 800 ለማድረስ ተስማምታ ነበር። እንዲሁም የተወሰኑ ፍልስጤማውያን ተፈናቃዮችን ሰሜናዊ ጋዛ ወደ ሚገኘው ቤታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ተስማምታ ነበር ሲሉ ባለሥልጣኑ ተናግረዋል።

ሐማስ ባለፈው ሰኞ እንዳስታወቀው የቀረበውን የእርቅ ሃሳብ ውድቅ እንዳደረገ እና የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ ሙሉ በሙሉ እንዲወጡ የሚያስችል ዘላቂ የተኩስ አቁም እንዲደረግ የሚጠይቀውን የቀደመ አቋሙን መያዙን ገልጿል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በበኩሉ የሐማስ አቋም ስምምነቱ ላይ “ፍጹም ፍላጎት እንደሌለው” ያሳየ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት አፋጣኝ የተኩስ አቁም እንዲቆም የሚጠይቅ ውሳኔ ማሳለፉ ያደረሰውን “ጉዳትም” ያሳያል ብሏል።

አሜሪካ ግን የእስራኤል መግለጫ “ከሁሉም አንጻር ትክክል ያልሆነ እና ለታጋቾቹ እና ለቤተሰቦቻቸው ኢፍትሃዊ ነው” ብሏል። የሐማስ ምላሽ “የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ድምጽ ከመስጠቱ በፊት የተዘጋጀ ነው” ብሏል።

ኳታር በበኩሏ ንግግሮቹ “በሂደት ላይ መሆናቸውን” እና “አላቆሙም” ስትል አጥብቃ ገልጻለች።

በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጦርነቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በጋዛ ከ32 ሺህ 490 በላይ ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል። የተገደሉት አብዛኛዎቹ ህጻናት እና ሴቶች ሲሆኑ አሁን ባለው ሁኔታ የጦርነቱ የመቆም ዕድል ከመቼውም ጊዜ በላይ የራቀ ነው ተብሏል።

በሙሉ ከበባ ውስጥ ባለችው ጋዛ እርዳታ እየገባ ባለመሆኑ በርካቶች በምግብ ዕጦር እየተሰቃዩ ባለበት ወቅት በዚህ ሳምንትም ከአውሮፕላን የሚለቀቅ ምግብ ለማግኘት በርካታ ህዝብ በባህር ዳርቻዎች ሲጠብቅ ታይቷል።

ከባህር ውስጥ ምግብ ለማውጣት ሲሞክሩ የነበሩ ቢያንስ 18 ሰዎች መሞታቸው የተነገረ ሲሆን ሌሎች ደግሞ በመረጋገጥ መሞታቸው ተነግሯል።