
28 መጋቢት 2024, 12:36 EAT
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስራኤል በጋዛ ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀመች ስለመሆኑ “አሳማኝ” ምክንያት እንዳለ ገለጸ።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኃላፊ ቮልከር ቱርክ በጋዛ ለተፈጠረው ሰው ሰራሽ ረሃብ እስራኤል ዋነኛ ተጠቃሽ መሆኗንም ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት ቮልከር ቱርክ ይህንን አሳማኝ ምክንያት ማረጋገጥ ከተቻለም የጦር ወንጀል ነው ብለዋል።
በጋዛ ያጋጠመውን የምግብ እጥረት በተመለከተ ለወራት ያህል ማስጠንቀቂያ የሰጠው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በግዛቲቷ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ ከፍቶ ሰው ሰራሽ ረሃብ መንሰራፋቱንም በጠንካራ አሃዛዊ መረጃዎች በተደገፈው ሪፖርቱ አውጥቷል።
እስራኤል የፍልስጤም ሰላማዊ ዜጎችን ለመጠበቅ ኃላፊነቷን እንድትወጣ እና በቂ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲገባ እንድታደርግም ጫና እያደረገ ይገኛል።
የእስራኤል የምጣኔ ኃብት ሚኒስትር ኒር ባርካታት በበኩላቸው የሰብዓዊ መብት ኃላፊውን ማስጠንቀቂያ በማጣጣልም “ከንቱ ነገር ነው። ሙሉ በሙሉ የተናገሩት ኃላፊነት የጎደለው ነው” ብለዋል ።
ልክ እንደ ሌሎቹ የእስራኤል ባለስልጣናት ሚኒስትሩም እስራኤል ከአሜሪካ እና ከተቀረው ዓለም እየቀረበ ያለውን እርዳታ እንዲገባ እያደረገች መሆኑን ተናግረዋል።
ነገር ግን መሰረታዊ የሚባሉ የእርዳታ ቁሳቁሶችን የጫኑ የጭነት መኪናዎች በግብጽ የድንበር ማቋረጫ ራፋህ በኩል ተደርድረው ታይተዋል።
እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ እርዳታ ለማስገባትም የሚቻለው ከእስራኤል በኩል ፈቃድ መገኘት ያለበት ሲሆን ውስብስብ የቢሮክራሲ እንዲሁም በርካታ ፍተሻዎችን በኬላዎች ካለፉ በኋላ ነው።
- የጋዛ ንግግር መቋረጡን ተከትሎ አደባባይ የወጡ የእስራኤል የታጋች ቤተሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ28 መጋቢት 2024
- ሚስቱን እና ሦስት ልጆቹን ጨምሮ 103 ዘመዶቹን ያጣው ፍልስጤማዊ አባት27 የካቲት 2024
- የሳተላይት ምስሎች ግማሽ የሚሆኑት የጋዛ ሕንጻዎች በእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ መውደማቸውን አሳዩ31 ጥር 2024
በቂ እርዳታ ወደ ጋዛ አለመግባቱንም ተከትሎ ዮርዳኖስ፣ አሜሪካ እና ዩኬን ጨምሮ ሌሎች አገራት እርዳታን ከአየር ላይ በፓራሹት እንዲጣል ለማድረግም እየሰሩ ነው ተብሏል።
ሰብዓዊ እርዳታዎችን ለማድረስ የተመረጠ አይደለም የተባለው ይህ መንገድ አደገኛ መሆኑም ታይቷል።
እርዳታው በባህር ላይ መውደቁን ተከትሎ እርዳታ ለማግኘት ሰጥመው ህይወታቸው ካለፉት በተጨማሪ እርዳታ የያዘ ፓራሹት ወድቆም የፍልስጤማውያንን ህይወት ቀጥፏል።
እስራኤል ወደ ጋዛ ለሚገባው እርዳታ መንገዶችን ክፍት ብታደርግ እንዲሁም ከጋዛ ሰርጥ ግማሽ ሰዓት ያህል ርቀት የሚገኘኘውን አሽዶድ ወደብን መጠቀም ቢቻል እርዳታዎች በተፋጠነ መንገድ እንደሚገቡ እና እነዚህ አደገኛ መንገዶች አላስፈላጊ በሆኑ ነበር ተብሏል።
የሰብዓዊ መብት ኃላፊውን እስራኤል እርዳታ የማስገባት ሂደትን እያዘገየች ወይም እርዳታን እየከለከለች ስለመሆኑ ማስረጃዎች መገኘታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ሪፖርቱን ያጠናቀረው ኢንተግሬትድ ፉድ ሴኩሪቲ ፌዝ ክላሲፊኬሽን (አይፒሲ) ሲሆን ይህ ተቋምም የረሃብን መጠን ለመለካት ለመንግሥታት፣ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የእርዳታ ኤጀንሲዎችን መረጃዎችን ይሰጣል።
ሪፖርቱ በጋዛ 1.1 ሚሊዮን ህዝብ በረሃብ ሊጠቃ እንደሚችልም የሚገልጽ ሲሆን በሚቀጥሉት ስምንት ሳምንታት ውስጥ የተኩስ አቁም ካልተደረሰ ወይም እርዳታ ወደ ጋዛ መግባት ካልቻለ ረሃብ እንደሚያጋጥምም አብራርቷል።