ከንቲባ አዳነች አቤቤ

28 መጋቢት 2024, 12:55 EAT

በአዲስ አበባ ከፒያሳ እና አካባቢው ከሳምንታት በፊት በተጀመረው ግንባታ ምክንያት ወደ 11 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች መነሳታቸውን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ ይህንን ያሉት በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ትናንት ረቡዕ መጋቢት 18/2016 ዓ.ም. ምሽት በተላለፈ ውይይት ላይ ነው።

በዚህ ውይይት ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት ሲያቀርቡ የታዩት ከንቲባዋ “በድምሩ ወደ 11 ሺህ ሰው ይሆናል ከዚያ አካባቢ [ከፒያሳ] ወደተሻለ ቦታ የወሰድነው” ብለዋል።

ነዋሪዎቹ ራስ መኮንን ድልድይ፣ ማህሙድ ሙዚቃ ቤት፣ አዲሱ የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም አካባቢ፣ አራት ኪሎ የሚገኘው አብርሆት ቤተ መጽሐፍት፣ ቴዎድሮስ አደባባይ እስከ ቸርችል ጎዳና ድረስ በሚያካልለው “የኮሪደር ልማት” ምክንያት የተነሱ ናቸው።

ይህ የኮሪደር ልማት ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ ባለው አካባቢ የሚገኝ ሲሆን፣ ወደ 8.1 ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍንም ከንቲባዋ ገልጸዋል።

አዳነች በዚህ ሪፖርት ላይ ከተነሺዎቹ መካከል አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት የቀበሌ ቤት ነዋሪዎች እንደሆኑ ጠቅሰው በድምሩ 1 ሺህ 989 ናቸው ብለዋል።

ቀድሞ ኪራይ ቤቶች አጀንሲ አሁን የቤቶች ኮርፖሬሽን የተባለው ተቋም በሚያስተዳድራቸው 490 ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችም ከአካባቢው ተነስተዋል።

ፒያሳ አከባቢ ከፈረሱ አካቢዎች አንዱ
የምስሉ መግለጫ,ከፈረሱ አካቢዎች አንዱ

ከንቲባዋ ከመንግሥት ቤቶች በተጨማሪ የግል የመኖሪያ፣ የንግድ እና የእምነቶች ቤቶች መነሳታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ በድምሩ 300 እንደሆኑም አስረድተዋል።

ሆኖም የትኞቹ የእምነት ተቋሞች እንዲነሱ እንደተደረገ የገለጹት ነገር የለም።

በሌላ በኩል ደግሞ በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው የነበሩ 886 ሼዶች፣ ኮንቴይነሮች እና ተለጣፊ ሱቆችም ፈርሰዋል። በተጨማሪም “ለጊዜው” ተብለው የተገነቡ 89 መጠለያዎች መነሳታቸውን አስረድተዋል።

ከመኖሪያ፣ ከንግድ እና ከእምነት ቤቶች በተጨማሪ አጥሮች፣ የእግረኛ ማቀወረጫ ድልድይ፣ የመብራት፣ የውሃ እና የስልክ መስመሮችን ጨምሮ በርካታ መሠረተ ልማት መነሳታቸውንም ከንቲባዋ ተናግረዋል።

ከንቲባ አዳነች ከአካባቢው ከተነሱት 11 ሺህ ነዋሪዎች 619 የሚሆኑት ተማሪዎች እንደሆኑም አመልክተዋል።

ከአካባቢዎቹ የተነሱት ነዋሪዎች እንደምርጫቸው የጋራ መኖሪያ ቤት ወይም የቀበሌ ቤት እንደተሰጣቸውም በሪፓርታቸው ላይ ገልጸዋል።

በቤቶች ኮርፖሬሽን ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ደግሞ በተቋሙ አማካኝነት ሌላ ቤት ለኪራይ ቀርቦላቸዋል ብለዋል።

በተመሳሳይ ለንግድ ተቋማትም ምትክ ቦታ ወይም በቦታው ላይ እንዲያለሙ ዕድል መስጠቱን ከንቲባዋ አስረድተዋል።

መንግሥት በአካባቢው ለልማት የሚፈልጋቸውን ቤቶች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ የማፍረስ ዕቅድ እንዳለው ያነሱ ሲሆን፣ እስካሁን 71 በመቶ ያህል መነሳቱንም ይፋ አድርገዋል።

ከንቲባ አዳነች በአካባቢው ምንም አይነት ህንጻ እንደማይፈርስ ተናግረው፤ ሆኖም በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ 102 ህንጻዎች መንግሥት በሚሰጠው መመሪያ መሠረት እንደሚታደሱ አመልክተዋል።

“በምን ዓይነት ማቴሪያል ነው መታደስ ያለበት? ምን ዓይነት መብራት ነው ሊኖረው የሚገባው? ምን ዓይነት ቀለም ነው ሊቀባ የሚገባው. . . የሚለውን በተመለከተ ጥናት ተደርጎ በዚያ መሠረት እንዲያድሱ መልሰን ሰጥተናቸዋል” ብለዋል።

በእነዚህ አካባቢዎች በቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን የተመዘገቡ ስድስት ቅርሶች እንደሚገኙ የተናገሩት አዳነች አቤቤ “እነሱን ባሉበት ቦታ የማደስ፣ የማሳመር የበለጠ ቅርስነታቸው ጎልቶ ከአድዋ ጋር ታሪካቸው ተያይዞ ለቱሪስት መስህብ መሆን እንዲችሉ ብቁ የማድረግ ሥራ እንሠራለን” ብለዋል።

ከአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ሲነሱ ተደጋጋሚ ውይይት እንደተደረገ የተናገሩት ከንቲባዋ፣ በአካባቢው መፍረስ ላይ “አንድም ሰው” ቅሬታ አላነሳም ብለዋል።

የአዲስ አበባ “የኮርሪደር ልማት” ምንድን ነው?

እንደ አዳነች ገለጻ የአዲስ አበባ “የልማት ኮሪደር” በአምስት አቅጣጫዎች የሚዘረጋ ሲሆን 40 .7 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ነው።

የመጀመሪያው ከፒያሳ አራት ኪሎ 8.1 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ሲሆን ከአራት ኪሎ፣ በእንግሊዝ ኤምባሲ እስከ መገናኛ ደግሞ 9.6 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ሁለተኛው አካባቢ ነው።

ሜክሲኮ፣ ሳር ቤት፣ ወሎ ሰፈር፣ ከሳር ቤት እና ቦሌ ሦስተኛው “የልማት ኮሪደር” መሆኑ ተጠቅሷል።

ከቦሌ፣ መገናኛ እስከ ሲኤምሲ ደግሞ አራተኛው አቅጣጫ ሆኖ 10.5 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል። የመጨረሻው ቦሌ፣ እስጢፋኖስ እስከ አራት ኪሎ 3.7 ኪሎ ሜትር የሚያካትት ነው።

እነዚህ “የልማት ኮሪደር” የመኪና አስፋልቶች፣ ሰፊ የእግረኛ መንገዶች፣ የሳይክል መስመሮች እና አረንዴ አካባቢዎችን በያዘ መልኩ ይገነባል ተብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ስለዚህ ሰፊ የግንባታ እንቅስቃሴ ሲናገሩ “አዲስ አበባን በዚህ ደረጃ ደፍሮ መልሶ ለመገንባት የሞከረ አመራር የለም” ብለዋል።

በዚህ ውይይት፣ “የልማት ኮሪደር” ሥራው በወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ እና ከንቲባዋ ደጋግመው አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሥራው ከተማን አፍርሶ ከመገንባት ጋር የሚስተካከል ስለሆነ ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል። ሆኖም ምን ያህል ገንዘብ እንደሚፈጅ እና የገንዘቡ ምንጭ ምን እንደሆነ ማብራሪያ አልሰጡም።