
28 መጋቢት 2024, 17:10 EAT
ምዕራባውያን እና የየመን ሁቲ አማጺያን በተፋጠጡበት በአሁኑ ጊዜ የሩሲያ ባሕር ኃይል የጦር መርከብ ወደ ኤርትራ ዋነኛዋ የቀይ ባሕር ወደብ ምጽዋ ደረሰች።
በኢራን የሚደገፉት ሁቲ አማጺያን በቀይ ባሕር በኩል በሚያልፉ መርከቦች ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት ለማስቆም በአሜሪካ የሚመሩ አገራት በቀይ ባሕር ላይ ኃይሎቻቸውን ማሰማራታቸው ይታወቃል።
የዓለማችን ዋነኛው የንግድ መርከቦች መተላለፊያ በሆነው ቀይ ባሕር ላይ የተለያዩ አገራት ኃይሎች በተሰማሩበት ጊዜ ነው የሩሲያዋ የጦር መርከብ ሻፖሺንኮቭ ባልተለመደ ጉብኝት ምጽዋ የደረሰችው።
የጦር መርከቧ ወደ ኤርትራ ወደብ ዛሬ ሐሙስ ስትደርስ ከፍተኛ የኤርትራ ወታደራዊ አዛዦች እና ባለሥልጣናትን ጨምሮ በኤርትራ የሩሲያ አምባሳደር ተገኝተዋል።
የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል በኤክስ ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት፣ የጦር መርከቧ በፓሲፊክ ያለው የሩሲያ ባሕር መድብ አባል ናት።
- በሁቲ አማጺያን ጥቃት ከተፈጸመባቸው መካከል የመጀመሪያዋ መርከብ ሰመጠች3 መጋቢት 2024
- የዓለማችን ግዙፍ የጭነት መርከቦች እየሸሹት ያለው ቀይ ባሕር30 ጥር 2024
- በቀይ ባህር ላይ መርከቦችን እያጠቁ ያሉት የየመን ሁቲ አማጽያን እነማን ናቸው?22 ታህሳስ 2023
ሻፖሺንኮቭ የጦር መርከብ ወደ ኤርትራ ወደብ ለአምስት ቀናት የመጣችው “ኤርትራ እና ሩሲያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበትን 30ኛ ዓመት ለማሰብ ነው” ብለዋል የማስታወቂያ ሚኒስትሩ።
የሩሲያ ተቀናቃኝ አሜሪካ ሁቲዎች በንግድ የጭነት መርከቦች ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት ለመከላከል የባሕር ኃይል ቡድኗን በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ ማሰማራቷ ይታወቃል።
በአካባቢው የምዕራባውያን ወታደራዊ እንቅስቃሴን በጥርጣሬ የምትመለከተው ኤርትራ፣ በቅርቡ ከሩሲያ ጋር ያላትን ግንኙነት የሚያጠብቅ ስምምነት መድረሷ ይታወቃል።
ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ማብቂያ ላይ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ግብዣ በሞስኮ ጉብኝት በማድረግ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ምክክር አድርገው ነበር።
ቀደም ሲልም የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በኤርትራ ጉብኝት ማድጋቸው አይዘነጋም።
በቀይ ባሕር ላይ ረጅም የባሕር ጠረፍ ካላት ኤርትራ ባሻር በምትገኘው የመን ያሉት የሁቲ ታጣቂዎች በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ነው በጭነት መርከቦች ላይ በሚሳኤል እና በድሮን ጥቃት መፈጽም የጀመሩት።
በዚህም ጥቂት የማይባሉ የጭነት መርከቦች እና የምዕራባውያን የባሕር ኃይል መርከቦች ጥቃት የደረሰባቸው ሲሆን፣ አደጋውን በመሸሽም በርካታ መርከቦች የጉዞ መስመራቸውን ለመቀየር ተገደዋል።