
28 መጋቢት 2024, 12:41 EAT
የአማራ ክልል መንግሥት ከቀናት በፊት በክልሉ የመማሪያ መጽሐፍት ላይ ያለውን ካርታ በተመለከተ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ለወጣው ማስጠንቀቂያ ምላሽ ሰጠ።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ሰኞ መጋቢት 16/2016 ዓ.ም. ሁለቱ ክልሎች በይገባኛል የሚወዛገቡባቸው አካባቢዎችን ወደ አማራ ክልል ያካተተ ካርታ በመማሪያ መጽሐፍት ላይ መታተሙን በተመለከተ መግለጫ አውጥቶ ነበር።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ በዚህ መግለጫው የአማራ ክልል በመማሪያ መጽሐፍት ላይ ያውጣው ካርታ በአስቸኳይ ማስተካከያ እንዲያደርግ ማስጠንቀቁ ይታወሳል።
የአማራ ክልል በበኩሉ ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 19/2016 ዓ.ም. በሰጠው ምላሽ የጊዜያዊ አስተዳደሩን መግለጫን “የዛቻ እና የጠብ አጫሪነት” ነው ሲል ጠርቶታል።
የዛሬው የአማራ ክልል መግለጫ አክሎም፤ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ያወጣው መግለጫ፤ “በተሳሳተ ካርታ ወደ አማራ ክልል ተካተዋል ያላቸውን አካባቢ ሕዝቦች ታሪካዊ እውነታን፣ ተጨባጭ ማስረጃዎችን እና ነባራዊ ሐቅን የካደ፣ አሳሳች እና የጠብ አጫሪነት ፍላጎትን የተሸከመ” ሲል አጣጥሎታል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ ባለፈው ሰኞ ባወጣው መግለጫ፤ “የአማራ ክልል የተቆጣጠራቸውን አካባቢዎች የሚያካትተው ካርታን የማያርም ከሆነ ለሚፈጠረው ችግር ኃላፊነቱን ይወስዳል” ሲል አስጠንቅቆ ነበር።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ በመግለጫው ያመላክታቸው አካባቢዎች “ካለፉት 30 ዓመታት በፊት ጀምሮ የማንነት ጥያቄ ያሉባቸው ወረዳዎች የማንነት እና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎችን ሲቀርቡባቸው የነበሩ ቦታዎች” መሆናቸውን አማራ ክልል በመግለጫው አስታውሷል።
በመግለጫው ላይ “የማንነት ጥያቄ ያሉባቸው” ተብለው የተዘረዘሩት አካባቢዎች የወልቃይት ጠገዴ፣ ጠለምት እንዲሁም የወፍላ ወረዳዎች እና የራያ አካባቢዎች መሆናቸው ተጠቅሷል።
- የአማራ ክልል በመጽሐፍት ላይ ያወጣውን ካርታ በአስቸኳይ እንዲያስተካክል የትግራይ ክልል አስጠነቀቀ25 መጋቢት 2024
- የአማራ እና ትግራይ ክልሎች በሚወዛገቡበት ራያ አላማጣ በተከሰተ ግጭት የሰዎች ሕይወት ጠፋ27 መጋቢት 2024
- የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከታጣቂዎች ጋር ለመነጋገር “የሰላም መንገድ” አመቻቻለሁ አለ28 መጋቢት 2024
እነዚህ አካባቢዎች የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እስከተቀሰቀሰበት ጊዜ ድረስ በወቅቱ ለነበረው መንግሥት “የማንነት እና የራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎችን” ሲያቀርቡ እንደነበር መግለጫው አስታውሷል።
መግለጫው አክሎም የአካባቢዎቹ “የማንነት እና ራስን በራስ የማስተዳደር” ጥያቄዎች የሰሜኑ ጦርነት እስከሚጀመር ጊዜ ድረስ ምላሽ አለማግኘታቸውን አክሏል።
የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሲቀሰቀስ “የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄዎቹ ለዘመናት የታፈኑበት ሕዝብ” ከማዕከላዊ መንግሥት ጎን ተሰልፎ “የበኩሉን አስተዋጽዖ ማበረክቱን” መግለጫው አውስቷል።
ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በፊት ጀምሮ “የአማራ ክልል እንደሌሎቹ ዞኖች እና የልማት ትሩፋቶች ሁሉ የአካባቢው ሕዝብም በትምህርቱም መስክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል” ሲል በመግለጫው አመልክቷል።
መግለጫው አክሎም “አካባቢዎቹን በተመለከተ የነበረው፣ ያለው እና የሚኖረው እውነታ ይሄ [ነው]” በማለት አካባቢዎቹን በተመለከተ ክልሉ አቋሙን ገልጿል።
የአካባቢው ህጻናት “የመማር መብታቸው እንዲከበር” የአማራ ክልል “ግዴታውን መወጣቱን” ክልሉ በመግለጫው ጠቅሶ “[ይህን] ሰበብ በማድረግ በአማራ ክልል ላይ ጥቃት ከመፈጸም የማይመለስ መሆኑን የሚገልጽ ጠብ አጫሪ መግለጫ” ነው ሲል የአማራ ክልል የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መግለጫን አጣጥሎታል።
“የተፈጠሩ ችግሮችን በሕግ አግባብ እንዲፈታ” አማራ ክልል የራሱን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን የጠቆመው ክልሉ፤ “የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ለአገሪቱ ቋሚ ቀውስ ምንጭ ከሚሆኑ ተግባራት እንዲታቀብ” ሲል አስጠንቅቆ “…የሕዝብን ፍላጎት ማዕከል ባደረጉ ውይይቶች ላይ እንዲያተኩር” አሳስቧል።
የሁለቱ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱባቸው አካባቢዎች ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በፊት በትግራይ ክልል አስተዳደር ስር ነበሩ። ከጦርነቱ መነሳት በኋላ ግን የአማራ ክልል አካባቢዎቹን እያስተዳደር ይገኛል።
በእነዚህ አካባቢው ባለፉት ጥቂት ወራት ውጥረቶች እና አልፎ አልፎም ግጭቶች እየተስተዋሉ ይገኛሉ። በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በራያ አላማጣ ወረዳ በተከሰተ ግጭት የወረዳው ሚሊሻዎች ሕይወት ማለፉን የወረዳው አስተዳዳሪ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል የዛሬው መግለጫም ላይ በራያ አላማጣ ወረዳ ቀበሌዎች ግጭት መኖሩን የሚያመለክት ነው።
ሁለቱ ክልሎች በሚወዛገቡባቸው አካባቢዎች ላይ ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ ስምምነት ላይ መደረሱን የፌደራል መንግሥቱ ገልጾ ነበር።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ግን “ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ ከስምምነት ላይ ተደርሷል” መባሉን “ፍጹም የተሳሳተ” ሲል አስተባብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄም (አብን) ከሰሞኑ የተሰማውን መግለጫ እና ግጭትን መሠረት አድርጎ ባወጣው መግለጫ “ህወሓት ለአራተኛ ዙር ጦርነት እየተዘጋጀ ነው” በማለት ከሶ፣ የፌደራል መንግሥቱ አና የአማራ ክልል መስተዳደር ያለውን እንቅስቃሴ በትኩረት እንዲከታተሉ አሳስቧል።