የሄዝቦላ ታጣቂ ቡድን አባላት
የምስሉ መግለጫ,የሄዝቦላ ታጣቂ ቡድን አባላት (ፋይል ፎቶ)

ከ 1 ሰአት በፊት

እስራኤል በሶሪያ ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 36 ሰዎች መገደላቸው የሶሪያ መከላከያ ሚኒስቴር ገለጸ።

ከአሌፖ ከተማ በቅርብ ርቀት በሚገኘው አካባቢ በአገሪቱ ሰዓታት አቆጣጠር ሐሙስ መጋቢት 19/2016 ዓ.ም. እኩለ ሌሊት ላይ በርካታ የአየር ጥቃቶች መፈጸማቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

መቀመጫውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው ሶሪያ ኦብዘርቫቶሪ ፎር ሂዩማን ራይትስ የተባለ ቡድን የጥቃቱ ዒላማ የነበሩት በሶሪያ ያሉ የሄዝቦላህ አባላት ናቸው ብሏል።

ቡድኑ እንደሚለው ከሆነ በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ የአየር ጥቃቱ በተፈጸመበት አካባቢ የጦር መሳሪያ ማካማቻ ስፍራ አለው።

እስራኤል ጥቃቱን በተመለከተ ያለችው ነገር የለም። ቴል አቪቭ ከዚህ ቀደም መሰል ጥቃቶችን በተመለከተ አስተያየት አትሰጥም።

ሮይተርስ የዜና ወኪል የደኅንነት ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው በአየር ጥቃቱ አምስት የሄዝቦላህ ታጣቂዎችን ጨምሮ 38 ሰዎች ተገድለዋል።

ሶሪያን ኦብዘርቫቶሪ ፎር ሂዩማን ራይትስ ደግሞ በጥቃቱ ሕይወታቸውን ካጡት በተጨማሪ በርካታ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሏል።

ቡድኑ የጥቃቱ ዒላማ ከአሌፖ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አቅራቢያ ያለ ቦታ መሆኑን ጨምሮ ገልጿል።

እአአ 2011 ላይ ሶሪያ የእርስ በእርስ ውስጥ ከገባች በኋላ እስራኤል በኢራን በሚደገፉ እና ሐማስን የሚደግፉ ቡድኖችን ዒላማ ያደረጉ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአየር ጥቃቶችን ስትሰነዝር ቆይታለች።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሐማስ በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ እነዚህ የአየር ጥቃቶች ተበራክተዋል።

በሶሪያ የእስራኤል ዒላማ ውስጥ ገብቶ የቆየው ሄዝቦላህ ደግሞ ከደቡባዊ ሊባኖስ ሆኖ እስራኤል ላይ የሮኬት ጥቃቶችን እያደረሰ ይገኛል።

የሶሪያ መከላከያ ሚኒስቴር በእስራኤል ተፈጽሟል ያለው የአየር ጥቃት መድረሱን ይፋ ባደረገበት መግለጫ ድብደባው የተፈጸመው “በአሸባሪ ድርጅቶች” የድሮን ጥቃቶች ከደረሱ በኋላ ነው ብሏል።

መከላከያ ሚኒስቴሩ በመግለጫው አሸባሪ ድርጅቶች ብሎ የገለጻቸውን ቡድኖች ማንነት ይፋ አላደረገም። እንዲሁም የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃቱ መቼ እና የት እንደተፈጸ እና ያደረሰውን ጉዳት በተመለከተም የሰጠው መረጃ የለም።