ኩላሊትዎን ለመጠበቅ የሚያግዙ 6 መንገዶች

ከ 5 ሰአት በፊት

በደም ውስጥ ያለን ቆሻሻ እያጣራ በሽንት መልክ የሚያስወጣው ኩላሊት በጣም አስፈላጊ ከሆኑ የሰውነት ክፍሎች አንዱ ነው።

እንደ ዓለም አቀፉ ኒፍሮሎጂ ማኅበር ደግሞ የደም ግፊትን ከመቆጣጠር ባለፈ በሰውነት ውስጥ ያለን የኬሚካል ሚዛን ለመጠበቅ ያግዛል።

በጣም ወሳኝ ሆነው አገልግሎቱ ደግሞ ቀይ ደም ህዋስ እንዲዘጋጅ ድጋፍ ማድረጉ ነው።

ስለዚህም ኩላሊት ሲጎዳ መዘዙም ብዙ ነው። በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም በርካታ ሰዎች በኩላሊት ህመም ይሰቃያሉ።

ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት የኩላሊት ህመም በከፍተኛ ፍጥነት መጨመሩን ባለሙያዎች እየገለጹ ነው።

በኢትዮጵያ በኩላሊት ህመም ምክንያት ጥሪታቸው ለህክምና ከማዋል ባለፈ የሰው እጅ ለማየት የተገደዱ ሰዎች በርካታ ናቸው።

ህመሙ የጸናባቸው በሕይወት ለመቆየት ዳያሊሲስ (የኩላሊት እጥበት) ለማድረግ ይገደዳሉ። ያውም ቢያንስ ቢያንስ በሳምንት ሁለት ጊዜ።

ይህ ደግሞ በበጎ አድራጎት ወይም በመንግሥት ድጋፍ ካልተደረገ ቀላል የሚባል ገንዘብን የሚጠይቅ ነገር አይደለም።

ይህ የኩላሊት እጥበት (ዳያሊሲስ) እክል በገጠመው ኩላሊት ምትክ በማሽን እገዛ የሚደረግ የደም ማጣራት ሥራ ነው።

እየተስፋፋ የበርካታ ሰዎችን ጤና እያስተጓጎለ ከሚገኘው የኩላሊት ችግር ላይ ከመደረሱ በፊት ግን የተለያዩ ጥንቃቄዎችን በማድረግ እንደሚቻል ባለሙያዎች ይመክራሉ።

ታሞ ከመማቀቅ. . . እንደሚባለውም ባለሙያዎች የሚከተሉትን ስድስት ወሳኝ ነጥቦች በመተግበር የኩላሊትን ጤና መጠበቅ ይችላል ይላሉ፡

1. በቂ ውሃ ይጠጡ

ኩላሊታችንን ጨምሮ ለአጠቃላይ ሰውነታችን ጤንነት አስፋለጊ የሆነውን በቀን ስምንት ብርጭቆ ውሃ ይጠጡ።

እንደ የስኳር በሽታ፣ የደም ግፊት እና የመሳሰሉ ለበሽታው ተጋላጭ የሚያደርጉ የጤና እክሎች ካሉ ደግሞ ውሃ መጠጣት ይበልጥ ይመከራል።

የቀዶ ሕክምና ያደረጉ ሰዎችም ከሕክምናው በኋላ በቂ ውሃ እንዲጠጡ ባለሙያዎች ይመክራሉ።

2. አልኮል እና ሲጋራ ማቆም

አልኮል እና ሲጋራ ከኩላሊት ጋር ዐይና እና ናጫ ናቸው። በመሆኑም ሁለቱን መለያየት አስፈላጊ ነው። የሚወስዱትን አልኮል መጠን ይቀንሱ፤ ሲጋራ ማጤስም ያቁሙ።

እነዚህን ማድረግ ደግሞ ለኩላሊት ባቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ የሰውነታችን ጤና እጅግ መጣም ጠቃሚ በመሆናቸው ተግባራዊ ማድረግ ጥቅሙ ብዙ ነው።

3. ከእጸዋት ከተቀመሙ ነገሮች ይጠንቀቁ

ለጤና እና ለሌሎች የተለያዩ ነገሮች በቅርብ ሰዎች ወይም ባለሙያ ነን በሚሉ ሰዎች ምክር ከተለያዩ ነገሮች የተቀመሙ ነገሮችን ከመጠጣታችን በፊት ቆም ብለን ማሰብ ይኖርብናል።

በተለይም ክብደት ለመቀነስ እና ለተመሳሳይ ጠቀሜታ በቤት ውስጥ እና በሌላም ቦታ የሚዘጋጁ መጠናቸው እና ይዘታቸው የማይታወቁ የእጸዋት ውጤቶችን መውሰድ ችግር ሊያስከትል ይችላል።

በአሁኑ ወቅት ደግሞ ለጤና ጠቀሜታ አላቸው ተብለው የሚዘጋጁ እጸዋትን በተመለከ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት መረጃዎች ይሰራጫሉ። ሁሉንም ማመን ይከብዳል።

ስለዚህም እነዚህን የእጸዋት ውህዶች ከመውሰድዎ በፊትም ሐኪምዎን ማማከር ይመረጣል።

ይህንን ሲያደርጉ ደግሞ አንድም ኩላሊትዎን፣ ሁለትም ሙሉ ጤናዎን ከጉዳት ይታደጋሉ።

ኩላሊትን የሚያሳይ የሰው የውስጥ አካል

4. መድኃኒቶችን ያለአግባብ አይውሰዱ

ከሐኪም ካልታዘዘ በስተቀር መፍትሔ ነው ስለተባለ ወይም ሌሎችን ስላሻለ የትኛውንም ዓይነት መድኃኒት መውሰድ አይገባም።

በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ህመሞችን ለማስታገስ አዘውትረን የምንወስዳቸው መድኃኒቶች እፎይታን የሰጡን በሚመስለንም ለጉዳት ሊዳርጉን ይችላሉ።

አንዳንድ የህመም ማስታገሻዎች እና ሌሎች መድኃኒቶች የተለያዩ የአካል ክፍሎች ሊጎዱ ይችላሉ። ለዚህ አንደኛው ተጋላጭ ደግሞ ኩላሊት ነው።

ስለዚህም በባለሙያ ያልታዘዘ የትኛውንም መድኃኒት ከመውሰድዎ በፊት ሐኪም ምክር ማግኘት ሊከተል የሚችልን ያስቀራል።

በተጨማሪም መድኃኒቶችን በባለሙያዎች ከማይሸጡባቸው ቦታዎች አይግዙ፤ አይጠቀሙ።

5. ምርመራ ያድርጉ

በተቻለ አቅም ከስንት ጊዜ አንድ ጊዜ ኩላሊትን ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም የአካል ክፍሎቻችንን ጤንነት በምርመራ ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

በዚህ ጊዜ በተለያዩ ምክንያቶች እያቆጠቆጡ ያሉ ከባድ የጤና ችግሮችን ሥር ሳይሰዱ ለማቅ ስለሚቻል በጊዜ በመታከም ለመዳን ዕድል ይፈጠራል።

ለኩላሊት ደግሞ በተደጋጋሚ ሳይሆን ከተቻለ ባለሙያዎች በሚመክሩት የጊዜ ልዩነት ውስጥ የአልትራሳወንድ ምርመራ ማድረግ ጠቃሚ ነው።

ምንም ዓይነት ምልክት ባይታይ እንኳን ቢያንስ ከሁለት እስከ አምስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ አንዴ በአልትራሰውንድ መታየት ይመከራል።

ይህ ደግሞ የኩላሊትን እና የሌሎችንም የአካል ክፍሎችን ጤንነት ለማወቅ እና አስፈላጊውን ህክምና እንዲሁም ጥንቃቃ ለማድረግ ያግዛል።

6. የደም ግፊትዎን ይቆጣጠሩ

በአሁኑ ወቅት በዓለማችን እየተስፋፉ ካሉት ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች መካከል አንዱ የሆነው ከፍተኛ የደም ግፊት አንዱ ነው።

የደም ግፊት አንዱ የጤና እክል ሆኖ ሳለ መቆጣጠር ካልቻልን ሌሎች የጤና ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል።

ስለዚህም ከ40 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች የደም ግፊታቸው የጨመረ መሆኑን በሚረዱበት ጊዜ፣ ችላ ሳይሉ በቁም ነገር ሊከታተሉት ይገባል።

ከፍተኛ የደም ግፊት የምልክት አልባ የኩላሊት ችግር የመጀመሪያ ምልክት እንደሆነ ባለሙያዎች ስለሚገልጹ፣ የደም ግፊትን በመቆጣጠር የኩላሊትን ጤና መጠበቅ ይቻላል።