የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አምበል ሃሪ ኬን (ከመሃል)፣ ከባየር ሙኒኮቹ ማኑኤል ኑዌር (ከግራ) እና ቶማስ መከለር (ቀን) ጋር
የምስሉ መግለጫ,የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አምበል ሃሪ ኬን (ከመሃል)፣ ከባየር ሙኒኮቹ ማኑኤል ኑዌር (ከግራ) እና ቶማስ መከለር (ቀን) ጋር

29 መጋቢት 2024, 11:25 EAT

ብሪታኒያ በመጪው ክረምት ጀርመን ውስጥ የሚካሄደውን የአውሮፓ ዋንጫ ጨዋታዎችን ለመመልከት ወደ ጀርመን የሚሄዱ የእግር ኳስ ደጋፊዎች ቢራ ሲጠጡ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የሚመክር ማሳሰቢያ አወጣች።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በመጪው ሰኔ እና ሐምሌ ከሚካሄደው የእግር ኳስ ውድድር አስቀድሞ ማሳሰቢያውን ያወጣው የጀርመን ቢራ ከብሪታኒያ ቢራ ጠንካራ በመሆኑ ነው።

በዩሮ2024 ላይ ተሳታፊ የሆኑትን የእንግሊዝ እና የስኮትላንድ ቡድኖችን ለመደገፍ በርካታ የብሪታኒያ ዜጎች ወደ ጀርመን እንደሚሄዱ ስለሚታሰብ ይህን ማሳሰቢያ ለደጋፊዎች ማውጣት አስፈልጓል ተብሏል።

ብሪታኒያውያኑ እንደ አገራቸው መስሏቸው ጠንካረውን የጀርመን ቢራ በርከት አድርገው ከጠጡ ስታዲየሞች እንዳይገቡ ሊከለከሉ ይችላሉ ተብሏል።

የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ የጀርመን ቢራ “በዩናይትድ ኪንግደም ካለው በአልኮል መጠኑ ጠንካራ ሊሆን ስለሚችል፤ ስትጠጡ በኃላፊነት፣ መጠናችሁን አውቃቸው እና የአገሪቱን ሕግ አክብራችሁ ሊሆን ይገባል” በማለት አብዝተው ከጠጡ ወደ ስታዲየሞች መግባት እንደማይችሉ አስጠንቅቋል።

በአስር የጀርመን ከተሞች ውስጥ የሚስተናገደው የአውሮፓ ዋንጫ ውድድርን ለመመልከት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ብሪታኒያውያን ወደዚያው ይሄዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በአልኮል መጠጥ ዙሪያ የሚሠራው ድርጅት እንደሚለው በዩናይትድ ኪንግደም አማካዩ የቢራ የአልኮል መጠን 4.4 በመቶ ሲሆን፣ የጀርመን ቢራ ጥንካሬ ግን በአብዛኛው በ4.7 በመቶ እና 5.4 በመቶ መካከል መሆኑን ይገልጻል።

ጀርመን በቢራ ምርት እና ዜጎቿም በቢራ ወዳጅነታቸው የሚታወቁ ሲሆን፣ በየዓመቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ቢራ በአገሪቱ ውስጥ ይጠመቃል። በተለያዩ ጊዜያትም የቢራ ፌስቲቫሎችን በማካሄድ አገሪቱ ትታወቃለች።

የወጣውን ማስጠንቀቂያ በተመለከተ የስኮትላንድ እግር ኳስ ደጋፊዎች ማኅበር መሥራች ከሆኑት መካከል አንዱ ፖል ጉድዊን ለቢቢሲ እንደተናገረው፤ በርካታ የሚያሳስቡ ነገሮች ባሉበት ሁኔታ የመንግሥት ማሳሰቢያ በቢራ ላይ ማተኮሩ እንደ ቀልድ ነው የተመለከተው።

“የስኮትላንድ ደጋፊዎች ጥንቃቄ ሊያደርጉባቸው የሚገቡ በርካታ ነገሮች አሉ፤ ነገር ግን የቢራ ጥንካሬን በተመለከተ የወጣው ማስጠንቀቂያ ከእነዚያ መካከል ሊሆን ይገባል ብዬ አላስብም” ሲል ተችቷል።

በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ ስኮትላንድ ከአዘጋጇ ጀርመን ጋር በሙኒክ ከተማ የመክፈቻውን ጨዋታ የምታደርግ ሲሆን፣ ከሁለት ቀናት በኋላ ደግሞ እንግሊዝ ከሰርቢያ ጋር ግልሴንኪርሸን ውስጥ ትጋጠማለች።

የዩናይትድ ኪንግደም አካል የሆኑት ዌልስ እና ሰሜን አየርላንድ በዩሮ2024 ውድድር ላይ ለመሳተፍ ማጣሪያውን ማለች ሳይችሉ ቀርተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከ1,600 የሚሆኑ እግር ኳስ እንዳይመለከቱ ዕገዳ የተጣለባቸው የእንግሊዝ እና የዌልስ ደጋፊዎች በዩሮ2024 ላይ እንዳይገኙ ፓስፖርታቸውን እንዲመልሱ ታዘዋል።