
29 መጋቢት 2024, 18:17 EAT
ከስምንት ወራት በኋላ ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡት የሕዝብ ተወካዮች እንዲሁም የአማራ ክልል እና የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባላት “እንደመደበኛ ታሳሪ እንዲታዩ” ፍርድ ቤት ትዕዛዝ አስተላለፈ።
ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ያቀረበው ጥያቄ በፍርድ ቤቱ ውድቅ እንደተደረገም የተከሳሾቹ ጠበቃ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ የሕገ መንግሥት እና ፀረ ሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ይህንን ትዕዛዝ ያስተላለፈው ዛሬ አርብ መጋቢት 20/2016 ዓ.ም. ከሰዓት በነበረው የፍርድ ቤት ውሎ ነው።
በዚህም ችሎቱ በፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ጄኔራል በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ክስ የተመሠረተባቸው 52 ግለሰቦችን ጉዳይ ተመልክቷል።
ከተከሳሾቹ ውስጥ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ክርስቲያን ታደለ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል ዮሐንስ ቧያለው እና የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል ዶ/ር ካሳ ተሻገር ይገኙበታል። በአማራ ክልል በትጥቅ እንቅስቃሴ ላይ የሚገኙት እስክንድር ነጋ እና ዘመነ ካሴ እንዲሁም የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሊቀመንበር ዶ/ር ጫኔ ከበደም በዚህ የክስ ዝርዝር ውስጥ ተካትተዋል።
የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ክሱን አስመልክቶ ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው ግለሰቦቹ ክስ የተመሠረተባቸው “የፖለቲካ ርዕዮትን በኃይል ለማስፈጸም በማሰብ ከአማራ ፋኖ አንድነት ምክር ቤት ጋር በመደራጀት” ነው።
“የአማራ ርስት ናቸው የሚሏቸዉን መሬቶች በወታደራዊ ኃይል ለማስመለስ እና አገር ‘በአማራ እሳቤ ብቻ መገዛት አለባት’ በሚል ስምምነት ላይ ደርሰዋል” የሚል ሀሳብ በክሱ ውስጥ እንደተካተተም ቢሮው አስታውቋል።
ይህንን ጉዳይ ለመመልከት አርብ በተሰየመው ችሎት ላይ የተሰየመው ችሎት ላይ የተገኙት ተከሳሾች ብዛት የምክር ቤት አባላቱን ጨምሮ 14 መሆኑን ጠበቃው አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“[በዛሬው ችሎት ላይ] ፍርድ ቤቱ መደበኛ ሂደቱን ለመቀጠል ሲያስብ፤ በእኛ በኩል አቤቱታ ነው የቀረበው። የቀረበው አቤቱታ ‘ደንበኞቻችንን ዛሬ ነው ያገኘነው፤ ስለዚህም ቀጣይ ሂደቶችን ለመቀጠል እስረኞችን ማናገር ስለምንፈልግ ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጥልን’ አልን” ሲሉ መደበኛው የክስ ሂደት በመጀመሪያው ዕለት እንዳይካሄድ መጠየቃቸውን ገልጸዋል።
ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ታሳሪዎቹ የሚገኙበት የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ “በእስረኞች የተጣበበ በመሆኑ ተከሳሾቹ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲዛወሩ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ይስጥልን” የሚል ጥያቄ ማቅረቡን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።
- አዋሽ አርባ፡ በኢትዮጵያ ከጅምላ እስር ጋር ስሙ የሚነሳው ‘የበረሃው ጓንታናሞ’24 ጥር 2024
- የምክር ቤት አባላቱ ጠበቃ እንዳያገኙ መከልከላቸውን ጠበቃቸው እና የቤተሰብ አባሎቻቸው ተናገሩ22 መጋቢት 2024
- በአንድ ሳምንት ውስጥ ሦስተኛው የምክር ቤት አባል ያለመከሰስ መብት ተነሳ24 የካቲት 2024
ይህንን ጥያቄ መቃወማቸውን የገለጹት ጠበቃው፤ “በዛሬው ዕለት በአቆያየት፣ በዋስትና ላይ ክርክር ባላደረግንበት ሁኔታ ተከሳሾቹ ‘ወደ ማረሚያ ቤት ይዘዋወሩ’ የሚለው የዐቃቤ ሕግ ጥያቄ ሥነ ሥርዓታዊ አይደለም” ብለው ተከራክረው፣ የዐቃቤ ሕግ ጥያቄም ውድቅ እንዲደረግ መጠየቃቸውን ጠቅሰዋል።
ይህንን መከራከሪያ የተቀበለው ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግን ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን አቶ ሰለሞን አስታውቀዋል።
በተከሳሾቹ በኩልም “አስቸኳይ የሆኑ ሁለት የመብት ጉዳዮች” እንዳሉ ለፍርድ ቤቱ መገለጹን የሚናገሩት ጠበቃው፤ ተከሳሾቹ ጉዳዩን እንዲያብራሩ ዕድል እንዲሰጥ መጠየቁን አንስተዋል። ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን ተቀብሎ ለመናገር ዕድል ያገኙት የአማራ ክልል ምክር ቤት አባሉ አቶ ዮሐንስ፤ በፌደራል ፖሊስ ቢሮ ቆይታቸው “ኢሰብአዊ አያያዝ” እንደተፈጸመባቸው መናገራቸውን ጠበቃው ገልጸዋል።
አቶ ዮሐንስ፤ “ስድስት ወር በአዋሽ አርባ፣ ሁለት ወር በሜክሲኮ ወንጀል ምርመራ ክፍል ጨለማ ቤት ውስጥ ታስረን እንገኛለን። በኃላፊዎች ማዋረድ፣ ማመናጨቅ ደርሶብናል። በአግባቡ እንኳን [ለመፀዳዳት] እንዳንችል በር ተቆልፎብን ተቀምጠናል። ከጠበቆች እና ከሃይማኖት አባቶች ጋር እንዳንገኛኝ እንዲሁም በቂ ህክምና እንዳናገኝ ተከልክለናል” ማለታቸውን ጠበቃው ተናግረዋል።
በቀጣይ ለመናገር ዕድል ያገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ አቶ ክርስቲያን ታደለ በበኩላቸው፤ ታሳሪዎቹ በእጃቸው ላይ ካቴና ተደርጎ መቆየቱ ለአለርጂ እንዳጋለጣቸው መናገራቸውን አቶ ሰለሞን ጠቅሰዋል። አቶ ክርስቲያን፤ “ፍርድ ቤቱ በካቴና እንዳንታሰር ትዕዛዝ ይስጥልን” የሚል ጥያቄ አቅርበዋል ተብሏል።
እንደ ጠበቃው ገለጻ በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሽ የሰጡት የፌደራል ፖሊስ ኃላፊ “ጨለማ ቤት አላሰርንም” በሚል የቀረበውን አቤቱታ ስተባብለዋል። ከጠበቃ እና ሃይማኖት አባት ጋር መገናኘትን በመሚለከትም፤ ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመሆኑ ይህ ተፈጻሚ አለመሆኑን ማስረዳታቸውን ጠበቃው ገልጸዋል።
ይህንን አቤቱታ የተመለከተው ፍርድ ቤቱ ግለሰቦቹ ክስ የተመሠረተባቸው በመሆኑ እንደማንኛውም መደበኛ እስረኛ እንዲታዩ ትዕዛዝ እንዳስተላለፈ አቶ ሰለሞን አስታውቀዋል።
ፍርድ ቤቱ የተሰጠው ትዕዛዝ፤ “ከዚህ በኋላ እስረኞቹ በኮማንድ ፖስት ስር አይደሉም፤ መደበኛ እስረኛ ናቸው። መደበኛ እስረኞች እንደሚቀርቡት ይቀርባሉ። መደበኛ እስረኞች የሚያገኙትን መብቶች ያገኛሉ። ከዚህ በኋላ የጨለማ ቤት እስር የለም። ጠበቃ፣ የሃይማኖት አባት የማግኘት መብት አላቸው። እንደሌሎች እስረኞች በተፈቀደው ሰዓት ቤተሰቦቻቸውን የማግኘት መብት አላቸው” የሚል እንደሆነ ጠበቃው አስረድተዋል።
ፍርድ ቤቱ፤ የተከሳሾች ጠበቃ ከደንበኞቻቸው ጋር አለመገናኘታቸውን በመጥቀስ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጥ የቀረበውን ጥያቄም ተቀብሎ ለሚቀጥለው ሳምንት አርብ መጋቢት 27/2016 ዓ.ም. ቀጠሮ መስጠቱን ጠበቃው አቶ ሰለሞን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡት የምክር ቤት አባላቱ በዋናነት በአማራ ክልል ከተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉት ባለፈው ዓመት መጨረሻ ነበር።
ለወራት በአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ ታስረው የነበሩት ተከሳሾቹ፤ ጥር ወር ላይ በአዲስ አበባ ሜክሲኮ አካባቢ ወደሚገኘው የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ተዘዋውረዋል።
በየካቲት እና መጋቢት ወራትም የሦስቱ የምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብት በየምክር ቤቶቻቸው እንዲነሳ ተደርጓል። የአቶ ክርስቲያን ያለመከሰስ መብት በተነሳበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ተገኝተው ማብራሪያ የሰጡት የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞትዮስ፤ ጥያቄው የቀረበው በአቶ ክርስቲያን ላይ “በፍርድ ቤት ክስ ለማቅረብ እንዲቻል” መሆኑን ተናግረው ነበር።