የፖሊስ መኪና

ከ 6 ሰአት በፊት

አንድ ርዕሰ መምህር በግድያ ዛቻ ምክንያት ሥራቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ ፈረንሳይ ተንቀሳቃሽ የደኅንነት ኃይል በትምህርት ቤቶች ልታቋቁም መሆኑን አስታወቀች።

ይህ ኃይል “ችግር እያጋጠማቸው ባሉ ትምህርት ቤቶች” ላይ የሚሰማራ ይሆናል ተብሏል።

ርዕሰ መምህሩ አንዲት ታዳጊ ሂጃብ ጠምጥመሻል በሚል ጥቃት አድርሰውባታል በሚል በሐሰት ከተወነጀሉም በኋላ ነው የግድያ ማስፈራሪያዎች የደረሷቸው።

የፈረንሳይ ትምህርት ሚኒስትር ኒኮል ቤሎቤት ተንቀሳቃሽ የደኅነነት ኃይሉ ዋነኛ ዓላማ መምህራን በመማር ማስተማሩ ሂደት ወቅት እንዲረጋጉ እንዲሁም ደኅንነት እንዲሰማቸው ለማድረግ ነው ብለዋል።

በአገሪቱ ሁለት መምህራን መገደላቸውን ተከትሎም በትምህርት ቤቶች ላይ ውጥረት ነግሷል።

ሳሙኤል ፓቲ የተሰኘው መምህር ከአራት ዓመት በፊት ነበር በፓሪስ ጎዳና ላይ አንገቱ ተቀልቶ ሲገደል፣ ሌላኛው መምህር ዶሚኒክ በርናርድ ደግሞ በሚያስተምርበት ትምህርት ቤት ውስጥ ከአምስት ወራት በፊት ተገድሏል። ጽንፈኛ የሆኑ የቀድሞ ተማሪዎች በሁለቱ መምህራን ግድያዎች ውስጥ እንደተሳተፉ ተገልጿል።

“መምህራን ብቻቸውን አይደሉም እናም በአካባቢያቸው፣ በትምህርት ቤቶቻችን ዙሪያ እንደ ጋሻ የሚሆናቸው ጥበቃ እያቋቁምን ነው” ሲሉም ሚኒስትሯ አንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን በጎበኙት ወቅት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

የፈረንሳይ ትምህርት ሚኒስቴር እንዳስታወቀው “ተንቀሳቃሽ የትምህርት ቤቶች የደኅንነት ኃይል” 20 ያህል የትምህርት የፀጥታ መኮንኖችን ያቀፈ ሲሆን፣ ከሚቀጥለው የትምህርት ዘመን ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል።

የአካባቢው ባለሥልጣናት በትምህርት ቤቶች ላይ ተጨማሪ ድጋፍ በሚፈልጉበት ወቅት በየ48 ሰዓታቱ ይሰማራሉ።

ለዚህም መነሻ የሆነው በቅርቡ በፓሪስ የሚገኘው ማውሪስ ራቬል ሊሴ የተሰኘው ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አንዲትን ታዳጊ በፈረንሳይ ሕግ መሠረት ሂጃቧን አንድታወልቅ ከመጠየቃቸው ጋር የተያያዘ ነው።

በዚህ ወቅትም በተከሰተ የጦፈ ክርክር ውስጥ ርዕሰ መምህሩ እንደመቷት ታዳጊዋ የተናገረች ሲሆን፣ ፖሊስ ደግሞ ይህንን የሚያረጋግጥ ምንም ዓይነት ማስረጃ አላገኘሁም ብሏል።

ሆኖም ርዕሰ መምህሩ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በርካታ የግድያ ዛቻዎች ደርሷቸዋል። ይህንም ተከትሎ ርዕሰ መምህሩ “ለራሴ እና ለትምህርት ቤቱ ደኅንንት በማሰብ” በማለት ከሥራ መልቀቃቸውን በዚሁ ሳምንት አስታውቀዋል።

ፖሊስ በዚህ ትምህርት ቤት አካባቢ የተሰማራ ሲሆን፣ ከግድያው ዛቻ ጋር በተገናኘ ሁለት ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል። ሁለቱ ሰዎች ከትምህርት ቤቱ ጋር ግንኙነት እንደሌላቸውም ተነግሯል።

ርዕሰ መምህሩ ሥራ መልቀቃቸውን ማሳወቃቸውን ተከትሎም የአገሪቱ የግራ እና የቀኝ ዘመም ፖለቲከኞች ቁጣቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋብርኤል አታል ተማሪዋ ሐሰተኛ ውንጀላ በመፈጸሟ በመንግሥት ልትከሰስ እንደሆነም በዚህ ሳምንት አስታውቀዋል።