Bowls of factory-made breakfast cereals

ከ 7 ሰአት በፊት

በእንግሊዝኛው አልትራ-ፕሮሰስድ ፉድስ ይባላሉ። በፋብሪካዎች ውስጥ ተመርተው እና ተቀነባብረው በየሱቁ መደርደሪያ ላይ የምናገኛቸው የታሸጉ ምግቦች።

እነዚህ ምግቦች ከ30 በላይ የጤና ችግር ያመጣሉ ይባላሉ። የልብ ህመም፣ ካንሰር እና ጭንቀትን እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።

በዩናይትድ ስቴትስ እና በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙ ነዋሪዎች ከሚመገቡት ምግብ 50 በመቶውን እኒህ ምግቦች ይይዛሉ።

አልፎም ኢትዮጵያን ጨምሮ በተቀረው ዓለም አሁን አሁን እየተለመዱ መጥተዋል።

ምግቦቸ የትኞቹ ናቸው?

እነዚህን ምግቦች በአንድ ቃል መግለጽ ከባድ ነው። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ ቤት ውስጥ የማንጠቀምባቸውን ንጥረ ነገሮች በውስጣቸው የያዙ ናቸው።

አብዛኞቹ ኬሚካል ናቸው። ማቅለሚያ እና ማጣፈጫ ተካቶባቸው ምግቡ አምሮ እና ተውቦ እንዲሁም ጣፍጦ እንዲቀርብልን ይሆናል።

ጣፋጭ እና ኃይል ሰጭ መጠጦች፣ ከረሜላ እና መሰሎቹ፣ ከዶሮ ሥጋ የሚሠሩ ምግቦችን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።

ነገር ግን እንዲህ በቀለማት ባሸበረቀ መጠቅለያ ታሽገው የሚመጡትን ብቻ ሳይሆን እንደ ዳቦ፣ የቁርስ ምግቦች እና እርጎን በጥንቀቃቄ መመልከት ያሻል።

ምግቦች

ከሌሎች የፋብሪካ ምግቦች በም ይለያሉ?

አልትራ ፕሮሰስድ የሚባሉ ምግቦችን ከሌሎች የፋብሪካ ምግቦች የሚለዩት በምን እንደሆነ ለማወቅ በአራት ምድብ እንለያቸዋለን።

የመጀመሪያው ‘አንፕሮሰስድ’ [ተፈጥሯዊ] የሚባል ሲሆን ሁለተኛው በትንሹ ‘ፕሮሰስ’ [በተወሰነ ለውጥ የተደረገበት] ነው። ሦስተኛው ምድብ ‘ፕሮሰስ’ [በምርት ሂደት ለውጥ የተደረገበት] ነው፤ አራተኛው ደግሞ አልትራ ፕሮሰስድ ወይም በከፍተኛ ደረጃ በፋብሪካ የምርት ሂደት ለውጥ የተደረገበት የሚባል ነው።

ፍራፍሬዎች፣ አትክልት፣ ለውዝ እና እንቁላል ፕሮሰስድ ከሚባሉ የምግብ ዓይነቶች መካከል ናቸው። ምግብ ለማብሰል የሚሆኑ አንዳንድ ሰብሎችም ከእነዚህ መካከል ይካተታሉ።

ለምሳሌ ከስንዴ ዱቄት፣ ውሃ፣ ጨው እና እርሾ የተሠራ ዳቦ ‘ፕሮሰስድ’ ምግብ ነው የሚባለው።

ነገር ግን ይህ ዳቦ ቀለሙን ለመቀየር የሚሆን ንጥረ ነገር አሊያም ብዙ ጊዜ እንዲቆይ ማድረጊያ ኬሚካል ከተጨመረበት ‘አልትራ-ፕሮሰስድ’ ምግብ ይሆናል ማለት ነው።

እንዴት መለየት እንችላለን?

ቢያንስ አምስት ዓይነት ንጥረ-ነገሮች የተካተቱበት ምግብ አልትራ-ፕሮሰስድ የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ ነው ይላሉ የናቫራ ዩኒቨርሲቲው የሕብረተሰብ ጤና ፕሮፌሰሩ ማይራ ቤስ-ራስትሮሎ።

እነዚህ ምግቦች ብዙውን ጊዜ በርካታ ጨው ያላቸው፣ ስኳር የሚበዛባቸው እና የተጣራ ስብ የሚታከልባቸው ናቸው።

በዩናይትድ ኪንግደም እና በአንዳንድ አገራት አምራቾች እነዚህን ንጥረ-ነገሮች ማሸጊያው ላይ የመፃፍ ግዴታ አለባቸው።

አንዳንድ ምግቦች ገና “ትኩስ” ቢሆኑም ቶሎ እንዳይበላሹ የሚያደርግ ንጥረ-ነገር ይጨመርባቸዋል።

ተጠቃሚዎች ምግቦቹን ሲገዙ የሶዲየም ቤንዞየት፣ ናይትሬት እና ሰልፋይት መጠናቸውን እንዲመረምሩ ይመከራሉ።

አገራት

ምን ያህል ተስፋፍቷል?

ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ ያሉ ሰዎች አልትራ ፕሮሰስድ ምግቦችን በስፋት በመጠቀም ይታወቃሉ።

በአውሮፓውያኑ 2023 ብቻ የአሜሪካ አዋቂዎች ከተመገቡት ካሎሪ 58 በመቶው እነዚህ ምግቦች ናቸው። ሕፃናትም እንዲሁ ከተመገቡት ምግብ 66 በመቶው አልትራ ፕሮሰስድ ምግብ ነው።

ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ሕፃናት እና አዋቂዎች ስንመጣ ይህ ቁጥር በ1 በመቶ ብቻ ነው የሚቀንሰው።

እስያ ስንሄድ ደግሞ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ከ20 እስከ 30 በመቶ ምግባቸው ይህ ነው። እንደ ብራዚል እና ቺሊ ያሉ የደቡብ አሜሪካ አገራትም ተመሳሳይ መጠን ያለው አልትራ-ፕሮሰስድ ምግብ ይወስዳሉ። የደቡብ አፍሪካ አሀዝ 39 በመቶ ነው።

ጎጂ ናቸው?

አልትራ-ፕሮሰስድ ምግቦችን መመገብ ጎጂ ነው ወይ? የሚለውን ጥያቄ በቀላሉ መመለስ ከባድ ነው።

ነገር ግን በቅርቡ በብሪቲሽ ሜዲካል ጆርናል ላይ የወጣ 9.9 ሚሊዮን ተሳታፊዎች ያሉት አንድ ጥናት እንደሚጠቆመው እነዚህ ምግቦች ከታች ከተዘረዘሩት የጤና እክሎች ጋር ግንኙነት አላቸው፡

ነገር ግን ጥናቱ እኒህን የጤና እክሎች ያመጣው ፕሮሰስድ ምግብ ነው አይልም። ነገር ግን አብዛኞቹ ምግቦች ከፍተኛ መጠን ያለው ስኳር፣ ጨው እና ስብ እንደያዙ ያሳያል።

ጨው፣ ስኳር እና ስብ አብዝቶ መመገብ ለክብደት መጨመር፣ ዓይነት 2 የስኳር በሽታ፣ የልብ ድካም እና ካንሰር ሊያጋልጥ ይችላል።

ውፍረት ቻርት

ከመጠን ያለፈ ውፍረት

በሥነ-ምግብ ላይ የፃፉት የለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተመራማሪው ክሪስ ቫን ቱሌኬን “አልትራ-ፕሮሰስድ ምግቦች ከልክ ላለፈ ውፍረት እንደሚያጋልጡ ምንም ጥርጥር የለውም” ይላሉ።

“ከፍተኛ የስብ መጠን አላቸው። ስኳር እና ጨውም በብዛት ይጨመርባቸዋል። ተጨማሪ ጣዕም፣ ቀለም እና ቃና ስለሚታከልባቸው ሰዎች በብዛት እንዲበሏቸው ተደርገው ነው የሚመረቱት።”

የለንደን ኢምፔሪካል ኮሌጅ የሠራው ጥናት እንደሚሳየው ከዓለማችን ሕዝብ አንድ ቢሊዮን ያክሉ ከመጠን ያለፈ ውፍረት አላቸው። ይህ ማለት ከስምንት ሰው አንዱ ማለት ነው።

ጥናቱ አክሎም ከ1992 እስከ 2022 ባለው ጊዜ የሴቶች የውፍረት መጠን እጥፍ ያደገ ሲሆን፣ የወንዶች ከመጠን ያለፈ ውፍረት በሦስት እጥፍ አድጓል። ሕፃናት እና ታዳጊዎች ደግሞ በአምስት እጥፍ ከመጠን በላይ ወፍረዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት እና ግሎባል ሄልዝ ኦብዘርቫቶሪ በአውሮፓውያኑ 2016 ያወጡት ጥናት ደግሞ በአሜሪካ አገራት የውፍረት መጠን 28 በመቶ አድጓል።

ይህ ቁጥር በአውሮፓ 26 በመቶ ሲሆን፣ በምሥራቃዊ ሜዲቴራኒያን 19 በመቶ፣ በአፍሪካ ደግሞ 9 በመቶ ነው።

የስኳር በሽታ

ዓለም አቀፉ የስኳር ህመም ፌዴሬሽን እንደሚለው በርካታ ሰዎች ዓይነት 2 የስኳር በሽታ አለባቸው።

“አልትራ-ፕሮሰስድ ምግቦች ውስጥ የምናገኛቸው ስብ፣ ስኳር እና ጨው ዓይነት 2 የስኳር ህመም እንዲይዘን ምክንያት እየሆኑ ነው” ይላሉ የሄልሲንኪ ዩኒቨርሲቲ የፐብሊክ ሄልዝ ፕሮፌሰር ጃኮ ቱሚሌህቶ።

መካከለኛው ምሥራቅ እና ሰሜን አፍሪካ በተነፃፃሪ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በዓይነት 2 የስኳር በሽታ የተያዙባቸው ሥፍራዎች ናቸው።

“እዚህ አካባቢ ያሉ በርካታ አገራት ራሳቸው ምግብ አያመርቱም፤ እነዚህ ምግቦች ለመጓጓዝ ቀላል እና ብዙ ጊዜ የሚቆዩ በመሆናቸው ኩባንያዎች በገፍ እየላኳቸው ነው” ይላሉ ፕሮፌሰሩ።

የስኳር ህመም

ያልተመጣጠነ ምግብ

ዶክተር ጆንሰን እንደሚሉት በበርካታ ከሰሀራ በታች ባሉ አገራት አልትራ-ፕሮሰስድ የሚባሉት ምግቦች ላልተመጣሰጠነ ምግብ አስተዋፅዖ እያደረጉ ነው።

“በተለምዶ ከምናገኛቸው ምግቦች የምናገኛቸውን የምግብ ይዘቶች እነዚህ ምግቦች ውስጥ ማግኘት አንችልም። ለምሳሌ አይረን፣ ሚኔራል እና ቫይታሚን አናገኝባቸውም” ይላሉ።

ነገር ግን የአሜሪካው ፑርዱ ዩኒቨርሲቲ ሳይንቲስቶች አንዳንድ ጥቅም ሊኖራቸው ይችላል ባይ ናቸው። ለምሳሌ፡

የብሪታኒያ ኒውትሪሽን ፋውንዴሽንም እንዲሁ ሁሉም አልትራ-ፕሮሰስድ ምግቦች ተመሳሳይ ጉዳት አላቸው ማለት አይቻልም ይላል።

“ለምሳሌ ቁርስ ላይ የምንበላቸው ‘ሲሪያልስ’ እና ዳቦዎች እንዲሁም አንዳንድ እርጎዎች አነስተኛ ስብ፣ ጨው እና ስኳር ነው ያላቸው” ይላሉ የፋውንዴሽኑ የሳይንስ ዳይሬክተር ሳራ ስታነር።

ምን እርምጃ ተወሰደ?

የዩኬ መንግሥት በአውሮፓውያኑ 2018 ጣፋጭ መጠጦች ላይ በጫነው ታክስ ምክንያት በርካታ አምራቾች የስኳር መጠናቸውን ቀንሰዋል።

በ2023 ኮሎምቢያ ፕሮሰስድ ምግቦች እና ስኳር የሚበዛባቸው መጠጦች ላይ የ10 በመቶ ቀረጥ ጥላለች።

ከመጠን ያለፍ ውፍረት የሚያጠቃቸው በርካታ ሕፃናት ያሉባት ቺሊ በ2016 ባወጣቸው ሕግ መሠረት አምራቾች በርካታ ካሎሪ፣ ስኳር እና ስብ ያለባቸው ምግቦች ላይ ማስጠንቀቂያ የመፃፍ ግዴታ አለባቸው።

አልፎም ለሕፃናት የሚሆኑ ምግቦች ነገር ግን ከፍተኛ የስኳር፣ ጨው እና ካሎሪ መጠናቸው ከፍተኛ የሆኑ ምግቦችን ማስታወቂያ ከልክላለች።

ነገር ግን አሁንም በቺሊ ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያላቸው ሕፃናት ቁጥር እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አልመጣም።