
ከ 6 ሰአት በፊት
ዋነኞቹን የሄይቲ ታጣቂ የወሮበሎች ቡድንን የሚመራው ጂሚ ሼሪዢየር በተባበሩት መንግሥታት ድጋፍ በአገሪቱ ይሰማራል የተባለውን የኬንያ ፖሊስ ኃይል በወራሪነት እንደሚመለከቱት አስጠነቀቀ።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ ከአገር ውጪ ሳሉ ሥልጣን እንዲለቁ የተገደዱባት ሄይቲ በታጣቂ የወሮበላ ቡድኖች በሚካሄድ ግጭት ምክንያት ሥርዓት አልበኝነት ከሰፈነባት ወራት ተቆጥረዋል።
ይህንንም ለመቆጣጠር በተባበሩት መንግሥታት እና በአሜሪካ ድጋፍ በኬንያ የሚመራ የፖሊስ ኃይል አገሪቱን ለማረጋጋት እንዲሰማራ ጥረት እየተደረገ ነው።
የዋነኞቹ ታጣቂ ቡድኖች መሪ ግን የኬንያ ፖሊስ ኃይል ወደ ሄይቲ የሚሰማራ ከሆነ “ጠብ ጫሪ” እና “ወራሪ” ብለው እንደሚመለከቱት አስጠንቅቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ አሪየል ሄንሪ በአገራቸው ያለውን አለመረጋጋት ለመቆጣጠር የሚያግዙ ሰላም አስከባሪ ፖሊሶች ለማሰማራት የሚያስችል ስምምነትን ኬንያ ውስጥ ከተፈራረሙ በኋላ ታጣቂ ቡድኖች ወደ አገራቸው እንዳይገቡ ስላገዷቸው ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ መገደዳቸው ይታወሳል።
በዚህም ምክንያት ከአስራ አንድ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ድሃዋ የካሪቢያን አገር ሄይቲ ከመጋቢት መጀመሪያ አንስቶ ያለመሪ ትገኛለች።
ይህንንም ተከትሎ የተፈጠረውን ክፍተት ወሮበላ ቡድኖቹ ተጠቅመው በመላው አገሪቱ ያላቸውን ቁጥጥር በማስፋት በበርካታ ቦታዎች ሥርዓት አልበኝነት እንዲነግስ አድርገዋል።
- ‘ባርቢኪው’ – ሄይቲን እያሸበረ ያለው የቀድሞው የፖሊስ መኮንን፤ የአሁኑ የወሮበሎች ቡድን መሪ7 መጋቢት 2024
- ራፐሩ፣ የቀድሞው ፖሊስ እና ‘ታራሚው’ – ሄይቲን ለመምራት እየተራኮቱ ያሉት ወንበዴዎች14 መጋቢት 2024
- ታጣቂ ወሮበሎች 4,000 አስረኞች ባስመለጡባት ሄይቲ የአስቸኳይ ጊዜ ታወጀ4 መጋቢት 2024
በካሪቢያን አገራት እና በአሜሪካ ድጋፍም ሄይቲን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይመልሳታል የተባለ የሽግግር ምክር ቤት ተቋቁሞ ጥረት እያደረገ ይገኛል።
በሄይቲ ኃያል ከሆኑት የወሮበሎ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆው ታጣቂ ቡድኖች መሪም በአገሪቱ መንግሥት ምሥረታ ሂደት ውስጥ እንዲሳተፉ ከተፈቀደ ትጥቁን ለመፍታት እንደሚስማማ አስታውቋል።
አብዛኛውን የሄይቲን ዋና ከተማ በቁጥጥሩ ሥር ያደረጉትን ቡድኖች የሚመራው ጂሚ ሼሪዢየር የተባለው የታጣቂዎች ቡድን አገሪቱን ለማረጋጋት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ቦታ እንዲሰጠው እንደሚፈልግ ለስካይ ቲቪ ተናግሯል።
የታጣቂ ወሮበላ ቡድኖቹ መሪው ጨምሮም በሄይቲ እየተካሄደ ያው ግጭት በቀጣይ ቀናት እየተባባሰ ሊሄድ እንደሚችል አስጠንቅቋል።
ነገር ግን በቅጽል ስሙ ባርቢኪው ተብሎ የሚታወቀው ጂሚ ሼሪዢየር ለስካይ ኒውስ እንደተናገረው ግጭቱን ለማስቆም “ለመፍትሔ ዝግጁ ነን” ብሏል።
የዋና ከተማዋን ፖርት አው ፕሪንስን 80 በመቶ የተቆጣጠረው በጂሚ ሼሪዢየር የሚመራው ‘ሊቭ ቱጌዘር’ የተባለው የታጣቂ ወሮበላ ቡድኖች ጥምረት በአገሪቱ መንግሥት ለማቋቋም በሚደረገው ንግግር ውስጥ ቦታ ሊሰጠው እንደሚገባ ያምናል።
የቡድኑ መሪ ለስካይ ኒስውስ “ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ቁጭ ብለን እንድንነጋገር ዝርዝር ዕቅድ ይዞ ከመጣ እና በምን ላይ መስማማት እንዳለብን የማያስገድደን ከሆነ መሳሪያችንን መፍታት እንችላለን” ብሏል።
በሄይቲ ውስጥ እየተካሄደ ባለው ግጭት ደስተኛ አለመሆኑን የሚናገረው የታጣቂዎቹ መሪ “ሙሰኛ ፖለቲከኞችን” በመቃወም ትጥቅ ያነሱት ቡድኖች ወደፊት የሚቋቋመው መንግሥት አካል ካልሆኑ ቀውሱ ሊቀጥል ይችላል ሲልም አስጠንቅቋል።
በሄይቲ ያለውን ሁኔታ እጅግ አደገኛ በሚል የገለጸው የተባበሩት መንግሥታት እየተካሄደ በለው ግጭት ባለፉት ሦስት ወራት ከ1,500 በላይ መገደላቸውን እና 800 መቁሰላቸውን አመልክቷል።
የሰብአዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶችም ወደ ዋና ከተማ ምግብ እና ውሃ ለተቸገሩ ሰዎች ለማቅረብ አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸዋል፤ በዚህም ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በምግብ እጦት ከረሃብ አፋፍ ላይ ናቸው ብለዋል።