የጦር ሄሊኮፕተር

ከ 5 ሰአት በፊት

የፖላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክ አውሮፓ በ“ቅድመ ጦርነት” ሁኔታ ውስጥ እንደምትገኝ አስጠነቀቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዩክሬን እና የሩሲያን ጦርነትን በመጥቀስም ዩክሬን ለአህጉሪቱ ሲባል በሩሲያ መሸነፍ የለባትም ሲሉም አጽንኦት በመስጠት ነው የተናገሩት።

ጦርነት “ከእንግዲህ እንደ ቀድሞው ጽንሰ ሃሳብ አይደለም። እውታው የተጀመረውም ከሁለት ዓመት በፊት ነው” ብለዋል።

ለዩክሬን አስቸኳይ ወታደራዊ እርዳታ እንዲደረግ እየጠየቁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ሁሉንም ነገር እንደሚወስን አስጠንቅቀዋል።

“ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ በኋላ ወሳኝ በሆነ ወቅት ላይ እንገኛለን” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአህጉሪቱ መሪዎች መከላከያቸውን እንዲያጠናክሩም አሳስበዋል።

ከኔቶ ጋር ትይዩ የሆነ ሌላ የፀጥታ መዋቅር አህጉሪቱ ማቋቋም አያስፈልጋትም ቢሉም፤ ነገር ግን አውሮፓ በወታደራዊ ኃይል ራሷን የምትችል ከሆነ ለአሜሪካ የበለጠ አጋር ትሆናለች ብለዋል።

ፖላንድ 4 በመቶ የሚሆነውን ምጣኔ ሃብቷን ለመከላከያ የምታውል ሲሆን፣ ሌሎች የአውሮፓ አገራት ግን በኔቶ የተቀመጠውን 2 በመቶ መዋጮ ማሳካት አልቻሉም።

የአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደምም አውሮፓ ለጦርነት መዘጋጀት አለባት ሲሉ አስጠንቅቀው ነበር።

ሩሲያ በዚህ ሳምንት በዩክሬን የኃይል አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ጥቃት መሰንዘሯን ተከትሎ ነው የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተያየት የተሰጠው።

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዚህ ሳምንት አገራቸው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል አገራት ላይ “ጥቃት የመፈጸም ዕቅድ እንደሌላት” ተናግረዋል።

በዓለም ላይ ግዙፍ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች ባለቤት የሆነችው አገራቸው የኔቶ አባላት በሆኑት በፖላንድ፣ በባልቲክ ግዛቶች እና በቼክ ሪፐብሊክ ላይ ጥቃት ትፈጽማለች የሚለው እሳቤ “ከንቱ ነው” ሲሉ ያጣጥለውታል።

ሆኖም ዩክሬን ስሪታቸው የምዕራባውያን የሆኑትን ኤፍ-16 የጦር አውሮፕላኖችን ከሌሎች አገራት የአየር ማረፊያዎች እንኳን ብትጠቀም ሩሲያ “ባሉበት ቦታ ኢላማ” እንደምታደርጋቸው አስጠንቅቀዋል።

ሩሲያ ከሦስት ዓመት ገደማ በፊት በዩክሬን ላይ ወረራ መፈጸሟን ተከትሎ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ግንኙነቷ ሻክሮ እየተካረረ ይገኛል።

ሩሲያ በቅርቡ በዩክሬን ላይ በፈጸመችው ጥቃት ወደ 100 የሚጠጉ ሚሳኤሎች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቅም ላይ የዋሉ ሲሆን፣ በርካታ ግዛቶች በከፊል የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መቋረጥ አጋጥሟቸዋል።

ሩሲያ የዩክሬንን መከላከያ ለማዳከም በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ በዚህ ደረጃ ጥቃት ስታደርስ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ይህንን የሩሲያን የጥቃት ስልት “የሚሳኤል ሽብር” ሲሉ የጠሩት ሲሆን፣ በሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫዎች ላይ የሚደረጉ ጥቃቶች ከፍተኛ የአካባቢ ጥፋት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።