የቪንሰንት ቫን ጎ ሥዕል
የምስሉ መግለጫ,የቪንሰንት ቫን ጎ የራስ ምሥል

ከ 8 ሰአት በፊት

ስመ ገናናው አርቲስት ቪንሰንት ቫን ጎ የአዕምሮ ጤና ችግር ነበረበት። የግራ ጆሮውን የቆረጠበት አጋጣሚ ደግሞ መቼም አይዘነጋም። ከሁለት ዓመት በኋላ (እአአ በ1890) ደግሞ እራሱን አጠፋ። የህመሙ ትክክለኛ ባህሪ ግን ብዙ አከራክሯል።

ሕይወቱ ያለፈን ሰው ህመም ለመመርመር መሞከር ውስብስብ ሥራ ይጠይቃል። ቫን ጎ ያጋጠሙትን ሁኔታዎች የሚተነትኑ ብዙ ንድፈ ሐሳቦች ግን አሉ።

እአአ በ2020 የኔዘርላንድስ ምሁራን ተሰባሰቡ። አንድ ሺህ የሚጠጉ ደብዳቤዎቹንም ሰበሰቡ። ደብዳቤዎቹን እንደ ማስረጃ ተጠቅመው ህመሙን ለመመርመር ነው መሰባሰባቸው።

የዓለም ባይፖላር (በተቃራኒ የስሜት ጽንፎች ውስጥ መዋለል) ቀን በየዓመቱ በሠዓሊው የልደት ቀን መጋቢት 21 ይከበራል።

ቫን ጎ ባይፖላር የአእምሮ ጤና ችግር ነበረበት?

ቫን ጎ ፈረንሳይ ውስጥ ሆስፒታል በነበረበት ጊዜ የሳለው ሥዕል
የምስሉ መግለጫ,ቫን ጎ ፈረንሳይ ውስጥ ሆስፒታል በነበረበት ጊዜ የሳለው ሥዕል

ቪንሰንት ቫን ጎ ከጉርምስና ዕድሜው ጀምሮ በተለያዩ የአዕምሮ ጤና ችግሮች ይሠቃይ ነበር። ካጋጠመው የአእምሮ ጤና ቀውስ በኋላ የግራ ጆሮውን በከፊል ቆርጧል።

በ1890 ከፓሪስ ወጣ ብሎ በሚገኝ መስክ ላይ እራሱን በጥይት ተኩሶ መትቷል። በደረሰበት ጉዳትም ከሁለት ቀናት በኋላ በ37 ዓመቱ ሕይወቱ አልፏል።

አርቲስቱ እራሱን ከማጥፋቱ በፊት በነበሩት ዓመታት ስለ አእምሮ ጤንነቱ በርካታ መላ ምቶች ይሰጡ ነበር። አንደኛው መላ ምት ደግሞ ቫን ጎ ባይፖላር ዲስኦርደር ወይም በተቃራኒ የስሜት ጽንፎች ውስጥ መዋለል ነበረበት የሚል ነው።

ባይፖላር ዲስኦርደር ምንድን ነው?

ይህ ባይፖላር ዲስኦርደር [በተቃራኒ የስሜት ጽንፎች ውስጥ መዋለል] ከስሜት ጋር የተያያዘ የአእምሮ ጤና ችግር ሁኔታ ሲሆን ከአንዱ ጽንፍ ወደ ሌላኛው የሚደረግ አስደናቂ መለዋወጥ በመሆን ይታወቃል።

ይህም ጥቂት የማይባሉ ሰዎችን የሚያጋጥም የተለመደ የአእምሮ ጤና ችግር ሲሆን፣ በዓለም ላይ ከ100 ሰዎች ውስጥ አንዱን እንደሚያጠቃ ይገመታል።

የተለያዩ የባይፖላር ዓይነቶች አሉ። የመጀመሪያው ዓይነት ያለባቸው ሰዎች የማኒያክ ከፍተኛ የደስታ እና የመንፈስ ጭንቀት ጊዜያቶችን ያሳልፋሉ።

ሁለተኛው ዓይነት ያለባቸው ደግሞ ከባድ ድባቴ እና አነስ ያለ የደስታ ጊዜ ያሳልፋሉ። ይህም ሃይፖማኒያ በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ነው።

ሳይክሎቲሚያ ያለባቸው ሰዎች ደግሞ አነስ ያለ የስሜት መለዋወጥ የሚያጋጥማቸው ቢሆንም፣ ረዘም ላለ ጊዜ ሊቆይባቸው ይችላል።

ሁሉም ወንዶች እና ሴቶች ለባይፖላር ዲስኦርደር የመጋለጥ ዕድላቸው ተመሳሳይ ነው። ይህ እክል በየትኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ ሊከሰት ቢችልም፣ በተለይም በአሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ በተለይም በ15 እና 19 መካከል ባሉት ያሉት የበለጠ ተጋላጭ ናቸው።

እያንዳንዱ ከባድ ባይፖላር ዲስኦርደር ለብዙ ሳምንታት (ወይም ከዚያ በላይ) ሊቆይ ይችላል።

ቫን ጎ ከባልደረባው ፖል ጉጊን ጋር የጻፈው ደብዳቤ
የምስሉ መግለጫ,ቫን ጎ ከባልደረባው ፖል ጉጊን ጋር የጻፈው ደብዳቤ

ሕክምና አለው?

ይህንን የአእምሮ ጤና ሁኔታን ለማከም እና ለመቆታጠር የተለያዩ መፍትሔዎች ይመከራሉ። ከእነዚህም መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል

ምንጭ፡ የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የጤና አገልግሎት

መጀመሪያ ላይ በ1938 በወጣው የጀርመን መጽሐፍ ላይ ጽንሰ-ሐሳቡ መገለጹን ተከትሎ ቫን ጎ ከባይፖላር ዲስኦርደር ጋር ተያይዞ ነበር።

እንደ ስኪዞፍሪንያ፣ ኒውሮሲፊሊስ ወይም ከሌሎች በሽታዎች ይልቅ ይህ እክል እንዳለበት እንዴት ማረጋገጥ እንችላለን?

መልሱ ትቶት በሄደው ማስረጃ ላይ ይገኛል።

የቫን ጎ ደብዳቤዎች

በ2020 የወጣው ጥናት አዘጋጅ የሆኑት ጡረተኛው የሥነ አእምሮ ፕሮፌሰር ዊሌም ኖለን “ቫን ጎ ለወንድሙ እና ለሌሎች ወዳጆቹ የከተባቸውን ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ደብዳቤዎችን በማጥናታችን ዕድለኞች ነን” ይላሉ።

ደብዳቤዎቹ የሕመሙን ምልክቶች ለማየት ዕድል እንደሰጣቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፀሐፊያኑ ዓላማ የቫን ጎን የሥነ አእምሮ ደኅንነት ለመተንተን “ሰፊ የምርመራ ቃለ መጠይቅ” ማካሄድ ነበር። ምንም እንኳን ሠዓሊው ደብዳቤዎቹን ለሐኪሙ አለመጻፉን በመገንዘብ ሁሌም እውነቱን ላይጽፍ ይችላል የሚለውንም ከግምት አስገብተዋል።

“ብዙ ገንዘብ እና ተጨማሪ ድጋፍ ለማግኘት ሲልም ለወንድሙ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ምልክቱን አጋንኖ ሊሆንም ይችላል። እናቱን ጨምሮ ለሌሎች የቤተሰብ አባላት ሲጽፍ ደግሞ እንዳይጨንቃቸው በማለት ምልክቶቹ እንዳቃለለ መገመት ትችላላችሁ” ሲሉ ፕሮፌሰር ኖለን ገልጸዋል።

ፕሮፌሰር ኖለን ስድስቱንም የደብዳቤዎቹን ቅጾች ስብስብ ተመልክተውታል። በኔዘርላንድስ ቪንሴንት ቫን ጎ ሙዚየም ውስጥ የሚሠሩ ሦስት የተለያዩ የጥበብ ታሪክ ፀሐፊያን ለጥናቱ ሲባል ቃለ-መጠይቅ ተደርጎላቸዋል። ሁሉም ደግሞ የሠዓሊውን ሕይወት እና ሥራ የሚያውቁ ባለሙያዎች ናቸው።

ቫን ጎ የጻፋቸው ደብዳቤዎችን የያዙ ስድስት ቅጾች
የምስሉ መግለጫ,ቫን ጎ የጻፋቸው ደብዳቤዎችን የያዙ ስድስት ቅጾች

ተመራማሪዎች ያቀረቡት መደምደሚያ ቫን ጎ ባይፖላር ዲስኦርደር ገጥሞታል የሚል ነው። የስብዕና መታወክ ባህሪያቶችም ነበሩበት። ይህም “በአልኮል እና በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ተባብሶ” ሊሆን ይችላል ይላሉ።

ቫን ጎ በሕይወት እያለ ምን ችግር እንዳለበት ሙሉ በሙሉ አልተረዳም ነበር። “የአእምሮ ወይም የነርቭ ትኩሳት ወይም እብደት፣ ብቻ ምን ብዬ መግለጽ ወይም እንዴት መሰየም እንዳለብኝ አላውቅም” ይል ነበር። መጀመሪያ ላይ “ቀላል የአርቲስት እብደት” በማለትም ገልጾታል። ምናልባትም ይህንን ያለው ቤተሰቡን ለማረጋጋት ሊሆን ይችላል።

የጥናቱ አዘጋጆች ግን በጉርምስና ወቅት በድብርት እንደተሰቃየ፣ የስብዕና መታወክን መስፈርት እንዳሟላ፣ ብዙ መጠጥ እንደሚጠጣ እና እራሱን የመጉዳት ምልክት የሚያሳይ ማስረጃ አግኝተዋል።

እሱ በተለየ ሁኔታ ድባቴ እና ከፍተኛ የስሜት ደረጃዎች ውስጥ እንዳለፈ ምልክቶች መኖራቸው ባይፖላር ዲስኦርደር መኖሩን ያመለክታሉ።

“በየትኛው ባይፖላር ዲስኦርደር እንደተሰቃየ ሙሉ በሙሉ ግልፅ አይደለም። ምክንያቱ ደግሞ ምንም እንኳን የመንፈስ ጭንቀቱ ያለበት ሁኔታ በጣም ከባድ ቢሆንም፣ ከፍተኛ መነሳሳት እንዳለው ግን ከደብዳቤዎቹ ማወቅ አንችልም” ሲሉ ፕሮፌሰር ኖለን ተናግረዋል።

 ቢያንስ 35 ከሚሆኑ የራሱ ምሥሎች አንዱ
የምስሉ መግለጫ,በሕይወት ዘመኑ ከሳላቸው ቢያንስ 35 ከሚሆኑ የራሱ ምሥሎች አንዱ

ከሥነ ጥበባዊ ውጤቱ የምንረዳው በቫን ጎ ሕይወት ውስጥ በተለይም በሕይወቱ መጨረሻ ዓመታት በጣም ውጤታማ የሆነበት ነበር። በርካታ ዝናን ያተረፉ ሥዕሎችንም አቅርቧል።

ፕሮፌሰር ኖለን እንደሚሉት ቫን ጎህ ሃይፖማኒክ በሆነበት ሁኔታ ውስጥ የበለጠ ሥዕል ይሠራ ነበር። ይህ የባይፖላር ዲስኦርደር አንዳንድ ጊዜ ከፈጠራ ሥራዎች ጋር ይያያዛል። እንደ ማሪያ ኬሪ፣ ዴሚ ሎቫቶ፣ ሴሌና ጎሜዝ እና ቤቤ ሬክስ ያሉ ታዋቂ ሰዎች ከህመሙጋር በጣም ተመሳሳይ የሆኑ ምልክቶችን እንዳሉባቸው ገልጸዋል።

በቫን ጎ ደብዳቤዎች እና የሥነ ጥበብ ሥራዎች ውስጥ የበሽታውን የድባቴ ደረጃ የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ አለ ይላሉ ፕሮፌሰር ኖለን።

“ቢያንስ 10 የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው አጋጣሚዎች ነበሩት። ከአንድ ዓመት በላይ በበሥነ አእምሮ ሆስፒታል ውስጥ ሕክምና ቢከታተለም ችግሩ በጣም ከባድ ሆነ” ይላሉ።

ሥር እና ግንድ የተሰኘው የቫን ጎ ሥዕል
የምስሉ መግለጫ,ቫን ጎ ከመሞቱ በፊት የሳለው ነው የሚባለው ሥዕል

ፕሮፌሰር ኖላን እንደሚሉት ቫን ጎ ብዙ ሥዕሎችን አይስልም። አንዳንዴም ብሩሹን የማያነሳበት ጊዜም አለ። “ወይም የሚሠራቸው ሥዕሎች ከሌሎች ጋር ሊወዳደሩ የማይችሉ እና በጣም አሳዛኝ ይሆናሉ” ብለዋል ፕሮፌሰሩ።

ቪንሰንት ቫን ጎ በሕይወት ዘመኑ በሙሉ ኑሮን ለማሸነፍ ሲታገል ነው የኖረው። ይህ ደግሞ በሙያው (ከሥራዎቹ አንድ ሥዕል ብቻ ነው የሸጠው) እና በአእምሮ ጤንነቱ ይገለጻል።

ፕሮፌሰር ኖለን እንደሚሉት ከሆነ አርቲስቱ ዛሬ በሕይወት ቢኖር ኖሮ ታሪኩ ምናልባት ከዚህ የተለየ ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ።

“ምናልባት ሊመረመር ይችላል። እንዳይጠጣ ምክር ይሰጠው ነበር። ምናልባትም ወደ ድባቴ አይወድቅም ነበር።”

“በሠዓሊነቱ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል ወይ የሚለውን ለመናገር በጣም ከባድ ቢሆንም ግን ምናልባትም እራሱን አያጠፋም ነበር” ብለዋል።