
ከ 5 ሰአት በፊት
ከለንደን የሚተላለፈው የኢራን ቴሌቪዢን አቅራቢ ለንደን ከሚገኘው ቤቱ ውጪ በተደጋጋሚ በስለት መወጋቱን ጣቢያው አስታወቀ።
ከአንድ ዓመት በፊት በኢራን ውስጥ የተቀሰቀሰውን ፀረ መንግሥት ተቃውሞ በስፋት ሲዘግብ የነበረው ‘ኢራን ኢንተርናሽናል’ የተባለው ቴሌቪዢን አቅራቢ ፑሪያ ዜራቲ ጥቃቱ የተፈጸመበት በቡድን ነው ተብሏል።
የለንደን ፖሊስ የፀረ ሽብርተኝነት መኮንኖች ቡድን በቴሌቪዥን አቅራቢው ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ምርመራ እየመራው መሆኑ ተገልጿል።
ጥቃቱ የተፈጸመበት ግለሰብ በአሁኑ ጊዜ ሆስፒታል ውስጥ በደህና ሁኔታ እንደሚገኝም ፖሊስ አስታውቋል።
ምርመራ እያደረገ ያለው ፖሊስ እንዳለው፣ የጥቃቱ ሰለባ የሆነው ግለሰብ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በሚገኝ የፋርስ ቋንቋ የመገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኛ መሆኑን ገልጿል።
በተጨማሪም ከዚህ በፊት በጣቢያው ላይ ይሰነዘሩ በነበሩ ማስፈራሪያዎች ምክንያት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተከታተለ ሲሆን፣ ለቅድመ ጥንቃቄም አስፈላጊውን ጥበቃ እንደሚደረግ ፖሊስ አስታውቋል።
ከጥቃቱ ጋር በተገናኘ አስካሁን በቁጥጥር ስር የዋለ ሰው የለም።
- ንጉሣዊውን አገዛዝ የገረሰሰው የኢራን እስላማዊ አብዮት ግቡን አሳካ ወይስ. . .?23 መጋቢት 2024
- በቴህራን ባቡር ጣቢያ ራሷን ስታ የወደቀችው ኢራናዊት ወጣት ሕይወት እንዴት አለፈ?30 ጥቅምት 2023
- እስር ላይ የምትገኘው ኢራናዊቷ የኖቤል ሎሬት ናርገስ ሞሐመዲ የረሃብ አድማ መታች7 ህዳር 2023
ኢራን ኢንተርናሽናል የተባለው መቀመጫውን ለንደን ያደረገው የቴሌቪዥን ጣቢያ ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮ በኢራን ውስጥ የሚካሄደውን ፀረ መንግሥት ተቃውሞን በተመለከተ ዘገባዎችን በማቅረብ ቀዳሚ ነው።
በአውሮፓውያኑ ኅዳር 2022 ለጣቢያው የሚሠሩ ሁለት የብሪታኒያ ዜግነት ያለቸው ኢራናውያን ጋዜጠኞች በሕይወታቸው ላይ አደጋ ሊያጋጥም እንደሚችል በመግለጽ ፖሊስ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧቸው ነበር።
ለጥበቃ ሲባልም የታጠቁ ፖሊሶች በቴሌቪዥን ጣቢያው ስቱዲዮ አቅራቢያ የተመደቡ ሲሆን፣ ከህንጻው ውጪም በሲሚንቶ የተሠሩ ማገጃዎች እንዲቀመጡ ተደርጓል።
በወቅቱም የኢራን የደኅንነት ሚኒስትር ኢስማኤል ኻቲብ ‘ኢራን ኢንተርናሽናል’ ቴሌቪዢን በኢራን መንግሥት የሽብር ድርጅት ተብሎ መፈረጁን አስታውቀው ነበር።
የቴሌቪዥን ጣቢያው የኢራን መንግሥትን የሚቃወሙ አመጾችን በማቀጣጠል ክስ ቀርቦበታል።
ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ ደግሞ ቴሌቪዥን ጣቢያው በለንደን የሚገኘውን የሥርጭት ስቱዲዮውን ለጊዜው ዘግቶ ወደ ዋሽንግተን ተዘዋውሮ ነበር።
ለዚህ ውሳኔውም የፋርስ ቋንቋ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሆነው ኢራን ኢንተርናሽናል በሰጠው ምክንያት “በኢራን መንግሥት በሚደገፉ ወገኖች የሚደርስብን ማስፈራሪያ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ ነው” ብሎ ነበር።
ጣቢያው ለንደን ውስጥ ከአዲስ ቦታ ሥርጭቱን መልሶ የጀመረው ባለፈው መስከረም ወር ነው።
ከአውሮፓውያኑ 2022 ወዲህ መኖሪያቸውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረጉ እና የኢራን መንግሥት በጠላትነት በፈረጃቸው ሰዎች ላይ ሊፈጸሙ የነበሩ 15 የአፈና ወይም የግድያ ሴራዎችን ማክሸፉን የለንደን ፖሊስ ገልጿል።
በቴሌቪዥን ጣቢያው አቅራቢ ላይ ለንደን ውስጥ የተፈጸመው የስለት ጥቃት የብሪታኒያን ከፍተኛ ባለሥልጣናትን አስቆጥቷል።