March 30, 2024 – Konjit Sitotaw
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ፣ ዛሬ በጽሕፈት ቤታቸው ከአሜሪካ የላይኛው የሕግ አውጭ ምክር የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ አባላት ጋር በፕሪቶሪያው ግጭት ማቆም ስምምነት አተገባበር ዙሪያ እንደተወያዩ የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቧል።
ጌታቸው፣ የግጭት ማቆም ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ባለመኾኑ፣ የትግራይ ሕዝብ ለተለያዩ ችግሮች እንደተዳረገ ለልዑካን ቡድኑ ማብራራታቸውን ዘገባው አመልክቷል።
የትግራይ ግዛቶች ወደነበሩበት እንዲመለሱ፣ የጦርነቱ ተፈናቃዮቹ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱና ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲኾን የአሜሪካ መንግሥትን ጨምሮ ኹሉም አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጌታቸው ጥሪ ማድረጋቸውን ዘገባው ጠቅሷል።
የልዑካን ቡድኑም፣ ለግጭት ማቆም ስምምነቱ ተግባራዊነት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብቷል ተብሏል።