ተመስገን ተጋፋው

March 31, 2024

የግብርና ኖራ አቅርቦትና ሥርጭትን አስመልክቶ የተደረገ ውይይት

በ2016 እና በ2017 ዓ.ም. ምርት ዘመን በከፍተኛ አሲድ የተጠቃ የእርሻ መሬትን በኖራ ለማከም፣ መንግሥት 50 በመቶ ወጪ ለአርሶ አደሮች ለመሸፈን 1.4 ቢሊዮን ብር ለክልሎች በድጎማ መስጠቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ግብርና ሚኒስቴር ይህንን ያስታወቀው የ2016 እና የ2017 ዓ.ም. ምርት ዘመን የግብርና ኖራ አቅርቦትና ሥርጭትን አስመልክቶ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር  ተመስገን ጥሩነህ፣ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ የማዕድን ሚኒስትር ሀብታሙ ተገኘ (ኢንጂነር) እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም. በተደረገ ውይይት ነው፡፡

በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ከሚታረሰው 16 ሚሊዮን ሔክታር የእርሻ መሬት ውስጥ 3.7 ሚሊዮን ሔክታር በከፍተኛ አሲድ መጠቃቱን፣ ከዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉን እንኳን ለማከም መቸገሩን የግብርና ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

የግብርና ኖራ አቅርቦትና ሥርጭት ማስፈጸሚያ ሰነድ ያቀረቡት የግብርና ሚኒስቴር የኢንቨስትመንትና ግብዓት ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ አሲዳማ አፈር የሚከሰትበት ዋነኛ ምክንያት የአፈሩ ኬሚካላዊ ይዘት (PH) ከሰባት በታች ሲሆን ነው፡፡

የአፈሩ ኬሚካላዊ ይዘት ከሰባት በታች ሲሆንና አንዳንድ ጊዜም የአልሙኒየም ንጥረ ነገሮች መጠን ከፍ ሲል የእርሻ መሬት በአሲድ ሊጠቃ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

በተለይ ከፍተኛ ዝናብ በሚዘንብባቸው አካባቢዎች የችግሩ ተጠቂ እንደሚሆኑ ገልጸው፣ የእርሻ ድግግሞሽ ሲበዛ የእርሻ መሬት በቀላሉ በአሲድ ሊጠቃ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በፊት በተደረገው የጥናት ዳሰሳ በከፍተኛ አሲድ ከተጠቁ ክልሎች ውስጥ ትልቁን ቦታ የሚይዘው የኦሮሚያ ክልል መሆኑንና አማራ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ሲዳማና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ከኦሮሚያ ቀጥሎ ትልቁን ድርሻ የሚይዙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የአሲዳማነት ሽፋን በአሥርና በሃያ አምስት ዓመታት ውስጥ ምን ያህል እየተቀየረ ነው የሚለው ሲታይ፣ በሃያ አምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከ3.2 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ውስጥ 41 በመቶ የሚሆነው በአሲዳማነት መጠቃቱን አብራርተዋል፡፡

በ2014 ዓ.ም. ደግሞ ከ34 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ውስጥ 43 በመቶ በአሲዳማነት መጠቃቱን፣ ይህም ማለት ደግሞ ከዚህ በፊት በአሲዳማነት ያልተጠቁ መሬቶች በአሁኑ ጊዜ በአሲድ እየተጠቁ መሆናቸውን የሚያሳይ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ አሲዳማ መሬትን ለማከም ከሚወሰዱ አማራጮች አንዱና ዋነኛው ኖራ እንደሆነ ያስታወሱት ሚኒስትር ደኤታዋ፣ ኢትዮጵያ ከ900 ሚሊዮን ቶን በላይ የኖራ ድንጋይ እንዳላት የማዕድን ሚኒስቴር ጥናት ያሳያል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከ20 በላይ ኖራና ሲሚንቶ የሚያመርቱ የግልም ሆነ የመንግሥት ድርጅቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ድርጅቹ በዓመት 1.1 ሚሊዮን ቶን ኖራ ማምረት እንደሚችሉ አክለዋል፡፡   

የኖራ ምርትን በዚህ ደረጃ ማግኘት ከተቻለ አሲዳማ መሬትን በተፈለገው መጠን ማከም እንደሚቻል ገልጸው፣ ኖራን በተገቢው መንገድ ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ክልሎች ትልቁን ድርሻ መወጣት አለባቸው ሲሉ አስረድተዋል፡፡  

በሌላ በኩል ባለፉት ዓመታት ውስጥ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ኖራ በማቅረብ 226 ሺሕ ሔክታር መሬት ለማከም ዕቅድ ተይዞ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ ሦስት ሚሊዮን ኩንታል ኖራ በማቅረብ 103 ሺሕ ሔክታር መሬት ወይም 36 በመቶ ማከም እንደተቻለ፣ ይህም አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆኑን ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

የአፈርን ጤንነት ለማሻሻል የተደረገው ጥረት አጥጋቢ እንዳልሆነ የገለጹት ሚኒስትር ደኤታዋ፣ በአሁኑ ወቅት 100 ሺሕ ሔክታር መሬት ለማከም 300 ሚሊዮን ኩንታል ኖራ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

በ2016 እና 2017 ዓ.ም. ምርት ዘመን ከ105 ሺሕ ሔክታር በላይ በአሲድ የተጠቃ መሬት ለማከም መንግሥት 50 በመቶ ኖራ ለአርሶ አደሩ የሚሆን 1.4 ቢሊዮን ብር ለክልሎች በድጎማ መስጠቱን ገልጸዋል፡፡

የግብርና መሬትን ሥራ ላይ ለማዋል በዓመት 6.2 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ጥቅም ላይ የሚውል መሆኑን፣ 70 በመቶ የሚሆነው የአፈር ማዳበሪያ ባክኖ እንደሚቀር ገልጸዋል፡፡

በዚህ መሠረት ኢትዮጵያ በአፈር አሲድ ምክንያት በዓመት 19 ቢሊዮን ብር እንደምታጣ ጠቅሰው፣ አርሶ አደሮች በአሲድ የተጠቃ መሬታቸውን በኖራ ለማከም ከ50 እስከ መቶ በመቶ ምርትና ምርታማነትን መጨመር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በአሲዳማ መሬት የተጠቃ ከ50 በመቶ በታች ምርትና ምርታማነትን እንዲቀንስ የሚያደርግ ሲሆን፣ ይህ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚያሳድር የግብርና ሚኒስትር ደኤታ ኢያሱ ኤልያስ (ፕሮፌሰር) ተናግረዋል፡፡ 

በተለይ በአሲድ የተጠቃ መሬትን በ30 ኩንታል ኖራ ማከም ከተቻለ፣ ለአምስት ዓመታት ያህል ያለ ምንም ተጨማሪ ኖራ ምርትና ምርታማነት ማግኘት እንደሚቻል አክለው ገልጸዋል፡፡

አሲዳማ መሬት ላይ ዘር ከመዘራቱ አንድ ወር አስቀድሞ ኖራው መጨመር እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው በቆሎ፣ ስንዴ፣ ጤፍና ሌሎች ምርቶች በአሲዳማ መሬት ላይ በበቂ ሁኔታ ማምረት እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

በዚህ መሠረት በአሲዳማ መሬት ላይ ድንችና ገብስ ሙሉ ለሙሉ እንደማይበቅል የገለጹት ሚኒስትር ደኤታው፣ ሻይ ቅጠል፣ ቡናና አናናስ ምርቶችን የመሬቱ አሲዳማነት የሚመቻቸው መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር በአሥር ዓመታት ዕቅድ ውስጥ ሦስት ሚሊዮን ሔክታር ጠንካራ አሲዳማ መሬትን ለማከም ዕቅድ መያዙን ገልጸው፣ ለዚህም በየዓመቱ 300 ሺሕ ሔክታር የእርሻ መሬት ማከም እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአሲዳማ አፈር ምክንያት በየዓመቱ ከፍተኛ ምርት እንደምታጣ የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

አሲዳማ አፈር በአብዛኛውን የሚከሰተው በደጋና በወይና ደጋ የኢትዮጵያ ክፍል አካባቢ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ ለዚህም ምክንያቱ መሬቱ በዝናብ ስለሚታጠብና በአንዳንድ የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም ላይ ችግር በመኖሩ ነው ብለዋል፡፡