ጥናቱ ይፋ በተደረገበት ወቅት

ማኅበራዊ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያውያ ሕዝብ በከፋ ድህነት ውስጥ እንደሚገኝ አንድ ጥናት አመላከተ

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

ቀን: March 31, 2024

በፅዮን ታደሰ

በዴሞክራሲ፣ በመንግሥት አስተዳደር፣ በኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የሕዝብን አመለካከት ለመለካት የዳሰሳ ጥናት የሚያደርገው አፍሮ ባሮ ሜትር የተባለው አፍሪካ አቀፍ የጥናትና የምርምር ተቋም ኢትዮጵያን አስመልክቶ ባካሄደው ሁለተኛ ጥናቱ፣ 61 በመቶ ያህል ኢትዮጵያውያን በከፋ ድህነት ውስጥ እንደሚገኙ መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል። 

በጥናቱ ከተሳተፉ 2,400 ሰዎች መካከል 66 በመቶ የሚሆኑት የገጠር ነዋሪዎች እንደተካተቱ የተገለጸ ሲሆን፣ 63 በመቶ የሚሆኑ ተሳታፊዎች ወጣቶች ናቸው ተብሏል። እ.ኤ.አ. በ2023 እንደተከናወነ በተገለጸው በዚህ ጥናት፣ 64 በመቶ የሚሆኑ ዜጎች ‹‹የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሁኔታ መጥፎ ነው›› ብለው እንደሚያምኑ ተመልክቷል። ተቋሙ ‹‹የድህነት መለኪያ›› በሚል ለጥናቱ በግብዓትነት የተጠቀመው የጥሬ ገንዘብ ገቢ እጥረት፣ በቂ ምግብ ማግኘት አለመቻል፣ የመጠጥ ውኃ፣ ሕክምና፣ እንዲሁም የምግብ ማብሰያ ችግር እንደሆነ በኢትዮጵያ የተቋሙ ተወካይ አቶ ሙሉ ተካ አስረድተዋል፡፡

በጥናቱ መሠረት 37 በመቶ የሚሆኑ ዜጎች በየዕለቱ የጥሬ ገንዘብ እጥረት እንደሚያጋጥማቸው አቶ ሙሉ ገልጸው፣ 26 በመቶ ያህሉ ደግሞ በቂ የመጠጥ ውኃና የሕክምና አገልግሎት እንደማያገኙ መናገራቸውን አስታውቀዋል። በተጨማሪም 18 በመቶ የሚሆኑት የምግብ እጥረት እንደገጠማቸው፣ 11 በመቶ ያህሉ የምግብ ማብሰያ እንደሚቸገሩ መግለጻቸውን አክለዋል፡፡ 

በእነዚህ መመዘኛዎች መሠረት 61 በመቶ ዜጎች በከፋ ድህነት ውስጥ እንደሚገኙ መረዳቱን አፍሮ ባሮ ሜትር አስታውቆ፣ ስድስት በመቶ የሚሆኑት ግን ከከፋ ድህነት ያመለጡ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ ብሏል። አፍሮ ባሮ ሜትር የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሁኔታ በዜጎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ለመመልከት ጥረት ማድረጉን በገለጸበት በዚህ ጥናት፣ ባለፉት 12 ወራት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የተናገሩ ዜጎች ቁጥር 64 በመቶ መሆኑን ገልጿል። 

እ.ኤ.አ. በ2020 በግል ኑሯቸው ደስተኞች የነበሩ 51 በመቶ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በ2023 ወደ 38 በመቶ ያሽቆለቆለ መሆኑን፣ የግል ኑሯቸው መልካም አለመሆኑን የገለጹ 38 በመቶ ዜጎች ቁጥርም ከፍ ብሎ 47 በመቶ ሆኗል ተብሏል።

በጥናቱ ላይ ያላቸውን ምልከታ የሰነዘሩት የኢኮኖሚ ባለሙያው አንዱዓለም ጎሹ (ዶ/ር)፣ ‹‹በኢትዮጵያ ያለው የድህነት መጠን 23 በመቶ ነው›› በሚል በመንግሥት የሚሰጠው መረጃ እ.ኤ.አ. በ2015 በተደረገ ጥናት መሆኑን ገልጸው፣ አፍሮ ባሮ ሜትር የሠራው ጥናት አገሪቱ ካለችበት እውነታ ጋር የተጣጣመ መሆኑን አስረድተዋል። ‹‹ጥናቱ እንደ ትምህርትና ፆታ ያሉ መመዘኛዎችን ሊያካትት ይገባ ነበር፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

ተቋሙ በበኩሉ ጥናቱን ሲያከናውን በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የፀጥታ ችግሮች አንዳንድ ሥፍራዎች ላይ መድረስ እንቅፋት ሆኖበት እንደነበር ገልጾ፣ ትልቅ የሚባል ክፍተት ግን አልተፈጠረብኝም ብሏል።