እኔ የምለዉ የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴና የ1966 ሕዝባዊ አብዮት ዋዜማ (ክፍል ሦስት)

አንባቢ

ቀን: March 31, 2024

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)

  1. የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ እ.ኤ.አ. ከ1950-1975

… ጭንቅ ብሎኛል ኢትዮጵያዊ ማን ነው?

ወጣት ሽማግሌው አገር ሲጠየቅ፣

አንዱ ጐጃም ነኝ ሲል ሌላው በጌምድር፣

አንዱ ኤርትራ ሲል ሌላው ተጉለት፣

አንዱ መንዝ ነኝ ሲል ሌላው ጋሙ ጎፋ፣

ኢትዮጵያዊ ነኝ ባይ ብፈልገው ጠፋ፣

እስቲ አዋቂዎች እናንተ ንገሩኝ፣

እኔን ያስጨነቀው ኢትዮጵያዊው ማን ነው…?!

(በ1950ዎቹ በዚያን ጊዜው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ የአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበረው ኢብሳ ጉተማ ‹‹ኢትዮጵያዊ ማነው?!›› ከሚለው ግጥሙ ተቀንጭቦ የተወሰደ)፡፡

በአፍሪካና በመላው ጥቁር ዓለም የናኘውና ከፍ ብሎ ከተሰማው የዓድዋው ድል ለአገራችን ፖለቲካዊ እንጂ የሚጠበቀውን ያህል ኢኮኖሚያዊ ድል እንዳላጎናፀፈን ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ጣሊያን ለአርባ ዓመታት ዝግጅት አድርጎ፣ አቅሙን አጠናክሮና በሠለጠነ ወታደራዊ ኃይል፣ በተራቀቁ ወታደራዊ መሣሪያዎች ዘመናዊ ተዋጊ ጄቶች ጭምር ታጥቆ ነበር ፋሽስት የሮማን የቀደመ ክብር አስመልሳለሁ በሚል ቁጭት ወደ ኢትዮጵያ የዘመተው፡፡

‹‹… የዚያን ጊዜዋ ኢትዮጵያ ግን በወታደራዊ ኃይልም ሆነ በኢኮኖሚ አቅም ረገድ ከዓድዋው ጊዜ እምብዛም የተሻለ አቋም ላይ አልነበረችም፤›› ይላሉ የታሪክ ምሁሩ ባሕሩ ዘውዴ (ፕሮፌሰር) ኢትዮጵያና ኢጣሊያ ከአርባ ዓመት በኋላ በሁሉም ረገድ የነበራቸውን ልዩነት ሲቃኙ፡፡   

የፋሽስት ጦር የኢትዮጵያን ጦር በአጭር ጊዜ ውስጥ አዳክሞ መዲናዋን አዲስ አበባን ሲቆጣጠር፣ በእውነትም በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የኃይል ሚዛን ጎልቶ ታየ፡፡ ከጣሊያን ወረራ በኋላ ራሳቸው ንጉሠ ነገሥቱ ኃይለ ሥላሴም እንዳመኑት ከዓድዋ ድል አርባ ዓመታት በኋላ በፋሽስቱ ኢጣሊያ ፊት የነበረችው ኢትዮጵያ ይህን ነው ሊባል በሚችል ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊና ማኅበራዊ ለውጥ አላሳየችም ነበር፡፡ ይህ ደግሞ በቀላሉና ለጊዜውም ቢሆን በአውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች እግር ሥር እንድትወድቅ እንዳደረጋት የታመነ ጉዳይ ሆኖ ነበር፡፡ እናም አፄ ኃይለ ሥላሴና መንግሥታቸው አገሪቱ በለውጥና በዕድገት ጎዳና ላይ እንደትጓዝ ለማድረግ ፈጣንና በቀላሉ ሊገታ የማይችል ሁለተናዊ ዘመቻ ነበር የከፈቱት፡፡

የዚህ ዘመቻ ዋነኛው ቁልፍ ጉዳይ ትምህርት መሆኑ የገባቸው አፄ ኃይለ ሥላሴ ሳይውሉ ሳያድሩ ነበር በርካታ ትምህርት ቤቶችን የከፈቱት፡፡ ከዚህም ባሻገር ከአገሪቱ የተለያዩ ጠቅላይ ግዛቶች ታዳጊ ልጆችን በራሳቸው ወጪ እያመጡ እንዲማሩ አድርገው ነበር፡፡ በተጨማሪም በርካታ ተማሪዎችን ወደ አሜሪካና አውሮፓ ሄደው እንዲማሩ ሰፊ ዕድልም ተመቻችቶላቸው ነበር፡፡ እነዚህ በውጭ አገር የተማሩ ኢትጵያውያን ወጣቶችም ወደ አገራቸው ሲመለሱ አገራቸው ያለችበት ድህነት፣ ኋላቀርነትና ጭቆና በእጅጉ ያንገበግባቸው ጀመር፡፡

ከዓመት ወደ ዓመት ከውጭው ዓለም ጋር ግንኙነት የነበራቸው ኢትዮጵያውያን ሌሎች ዜጎችን በተገናኙና ስለሌሎች አገሮች የዕድገት ደረጃ ባነበቡ ቁጥር፣ የአገራቸው መሪነት ሳይሆን ጭራነቷ ወደ እውነታ የሚጠጋ ሀቅ እንደሆነ እየተገነዘቡ መጡ፡፡ በሚያስደንቅም ሁኔታ ነገሮች ለውጥ ማሳየት የጀመሩት ወጣቱ ትውልድ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መሪነት በመንግሥት ላይ የፖለቲካ ተበቃይ ኃይል ሆኖ ብቅ ባለባቸው በ1950ዎቹ መጨረሻ ዓመታት ውስጥ ነበር፡፡

ለተማሪዎቹ አየል ብሎ መውጣት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች መካከል የ1953ቱ የከሸፈው የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ አንዱ መሆኑን የታሪክ ምሁራንና የፖለቲካ ተንታኞች በአንድ ድምፅ ይስማሙበታል፡፡

ቀደም ሲል በ1953 ዓ.ም. ትምህርቱን በአሜሪካ አገር በተከታተለው በግርማሜ ንዋይ በወንድማቸው በጄ/ል መንግሥቱ ንዋይ የተሞከረው የመፈንቅለ መንግሥት የንጉሡን የ‹‹ሥዩመ እግዚአብሔር›› ካባ በመግፈፉ፣ ሥልጣናቸው ተበጋሪ የሆነ ግለሰብ እንደሆኑ አሳየ፡፡ ከዚህ አልፎ ሙከራው በኅብረተሰቡ ውስጥ የነበሩትን ኢኮኖሚያዊና ማኅበረሰባዊ መበላለጦች ቁልጭ አድርጎ አሳየ፡፡ በከሸፈው በሁለቱ ወንድማማቾች የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራም የዛን ጊዜዎቹ የቀ.ኃ.ሥ ተማሪዎች ሙሉ ድጋፋቸውን ሰጥተውት እንደነበር በጊዜው ወጥተው የነበሩት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

እንዲያውም ብርጋዴር ጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ በመፈንቅለ መንግሥቱ ዋዜማ ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ባደረጉት ንግግራቸው እንዲህ ብለው መናገራቸው ይጠቅስላቸዋል፡፡

‹‹እናንተ የነገይቱ ኢትዮጵያ ተስፋዎች የሆናችሁ ተማሪዎች እኛ የለውጥ መስኮቱን ከፍተናል፣ ታላቁን የለውጥ በር የምትከፍቱት ግን እናንተ ናችሁ››፡፡ በእርግጥም ይህ ትንቢታዊ ሊባል የሚችል የወቅቱ የጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ ንግግር ከአሥር ዓመት በኋላ አገሪቱን ከዳር እስከ ዳር ለለውጥ በእንዴት ያለ ኅብረትና አንድነት፣ በእንዴት ያለ ቁጣና እልህ ሁሉንም እንዳንቀሳቀሰው እውነታው በተግባር ታይቷል፡፡

የዚህ መፈንቅለ መንግሥት መንስዔው አገሪቱ የነበረችበት ድህነትና የሕዝቡም መከራና ጉስቁልና ነበር፡፡ ምንም እንኳን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ብርቱ ፍላጎትና ጥረት የተጀመረው የኢትዮጵያ ሥልጣኔና የዕድገት ሒደት ሥር ነቀል ለውጥ ያመጣል ተብሎ ቢታሰብም የኋላ ኋላ በራስ ወዳድነትና ስግብግብነት ምክንያት የተጓጓለትንና የተጠበቀውን ያህል የረባ ዕድገትና ለውጥ ማሳየት ሲሳነው ማስተዋል ለህሊና የሚቆጠቁጥ ሐቅ ሆነ፡፡ በመሆኑም በፊውዳሊዝም ቅሪቶች ላይ ለሚካሄደው ዘመቻ በንጉሡ ይተማመን የነበረው የብዙዎች ምኞት ቀስ በቀስ እንደ ጉም መትነን ጀመረ፡፡

እንደውም የገዥው መደብ አምርሮ በሚቃወማቸው የመሬት ስሪት ለውጥን በመሳሰሉ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ አፄ ኃይለ ሥላሴ ለውጥ ለማካሄድ ፍላጎት ወይም ችሎታው እንዳልነበራቸው ግልጽ እየሆነ መጣ፡፡ ቀስ በቀስም በንጉሠ ነገሥቱ የሚመራው መንግሥት ራሱ ለአገሪቱ ዕድገት ዋንኛው እንቅፋት ስለሆነ መነሳት አለበት የሚለው ግንዛቤ መልክ እየያዘና እየተጠናከረ መጣ፡፡ በቀ.ኃ.ሥ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ተማሪዎችና አንዳንድ ምሁራንም አገሪቱ ለውጥ እንደሚያስፈልጋት በማመን ሌሎችንም ለማሳመን ጥረት በማድረግ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመሩ፡፡

ተማሪዎቹ በየዓመቱ በግቢያቸው በሚያቀርቡት የግጥም ውድድርም የዘውዱን ሥርዓት የሚሞግቱና አገሪቱ ያለችበትን አስከፊ የሆነ ኋላ ቀርነት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብም የሚገኝበትን አሰቃቂ ድህነትና ጭቆና የሚያጋልጡ ግጥሞችን ማቅረብ ጀመሩ፡፡ እነዚህ ንጉሠ ነገሥቱና ባለሟሎቻቸው ሳይቀር በሚገኙበት መድረክ የሚቀርቡ ግጥሞች ንጉሡንና ተከታዮቻቸውን ማስኮረፍ ብቻ ሳይሆን በሒደትም ግጭት ውስጥ አስገባቸው፡፡ በ1954 ዓ.ም. ለዩኒቨርሲቲው ቀን/በኮሌጆች ቀን የሚቀርቡት ግጥሞች በተቀዳሚ ለሳንሱር እንዲሰጡ ተጠየቀ፡፡ ተማሪዎቹም እምቢኝ ጽሑፎቻችንን አንሰጥም አሉ፡፡

ንጉሡም በዚሁ ተቀይመው በበዓሉ ላይ ሳይገኙ ቀሩ፡፡ በዓሉ ተከበረ፣ ግጥሞቹም ተነበቡ፡፡ አሸናፊ የሆኑት ግጥሞችም በፀረ መንግሥትነት ተከሰሱ፡፡ ሦስት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማኅበር መሪዎችም ከትምህርት ገበታቸው ተባረሩ፡፡ በየጊዜው በሚከበረው የዩኒቨርሲቲ ቀን ከቀረቡት ዝነኛ ግጥሞች መካከልም፣ ‹‹ምላሴን ተውልኝ!›› በአበበ ወርቄ፣ ‹‹በረከተ መርገም!›› በኃይሉ ገ/ዮሐነስ/ገሞራው፣ ‹‹የገደል ሥር አጥንት›› በዮሐንስ አድማሱ፣ ‹‹ኢትዮጵያዊ ማነው?!›› በኢብሳ ጉተማ፣ ‹‹ልረሳሽ እሻለሁ!›› በዋለልኝ መኮንን ይገኙበታል፡፡

በዚህ የተሟሟቀ የለውጥ ሒደትም የተማሪዎቹ እንቅስቃሴ ቀስ በቀስ እየተደራጀና ሌላ መልክ እየያዘ በመምጣቱ በመንግሥት ዘንድ እምብዛም አልተወደደለትም ነበር፡፡ ከዚህም የተነሳ የተማሪውና የመንግሥት ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ በሚሄድበት ወቅት ቆራጥ የተማሪ መሪዎችን የሚያሰባስብ የድርጅት አስኳል በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ተጣለ፡፡

በ1956 ዓ.ም. ቀደም ሲል የተፈጠረው ስብስብ/ማኅበር ተጠናክሮ አዞዎቹ (Crocodiles) የተባለ ጠንካራ የሆነ ስብስብ ሊፈጥር ቻለ፡፡ በዚሁ ዓመትም ብሔራዊ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማኅበርን የሚያቋቁመው ስብሰባ በይፋ ተደረገ፡፡

በዚህ ጉባዔም ማሳረጊያ አሥራ ሁለት ገጾች የአቋም መግለጫዎችና ውሳኔዎች ተላለፉ፡፡ የመንግሥትን ቅጣትና ተፅዕኖ ሳይፈራ በኢትዮጵያ የተንሰራፋውን ችግርና አስከፊ ድህነት ለመታገል ወደኋላ እንደማይል ማኅበሩ አስገነዘበ፡፡ የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ማሻሸያ ዕርምጃዎችን ይወስድ ዘንድም ጠየቀ፡፡

ተማሪዎቹ በዚህ ጥያቄያቸውም በአርሶ አደሩ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል በጢሰኛውና በባለመሬቱ መሀል ያለው ግንኙነት ሕጋዊ እንዲሆን ጠይቀው ነበር፡፡ በዚህ ስብሳባ ላይ በተካሄደው ምርጫም ብርሃነ መስቀል ረዳ የብሔራዊው ኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማኅበር የመጀመሪያው ዋና ጸሐፊ ሆኖ ሲመረጥ፣ ባሮ ቱምሳ ደግሞ የዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ማኅበር ፕሬዚዳንት ሆኖ ተመረጠ፡፡

  1. የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴና የመሬት ላራሹ ጥያቄ

‹‹መሬት ላራሹን የምትሹ፣

ተዋጉለት አትሽሹ፡፡››

በ1957 ዓ.ም. ብሔራዊ ማኅበሩ ለኃይለ ሥላሴ ፓርላማ አንድ ወሳኝ የሆነ ጥያቄ ይዞ መጣ፡፡ ይኸውም፣ ‹‹የሰባ አምስት በመቶ የአርሶ አደሩን ምርት ባለ መሬቱ እንዲወስድ የሚደነግገው የፍትሐ ብሔር ሕግ ወደ ሰላሳ በመቶ እንዲወርድ፤›› የሚጠይቅ ነበር፡፡

‹‹መሬት ላራሹን›› በፊታውራሪነት ይዞ የተነሳው ተማሪዎቹ እንቅስቃሴ በተመሳሳይም አይነኬ የሚባሉ ሌሎች ጥያቄዎችን ይዞ ወደ አደባባይ ወጣ፡፡ የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ታሪክ ከ1950ዎቹ አጋማሽ በኋላ ‹‹መሬት ላራሹ›› በሚለው መፈክር ስም የዘመኑ ተማሪዎች ያደርጉት ነበረውን ተከታታይ የተቃውሞ የአደባባይ ሠልፍና በተለይም ደግሞ በ1961 ዓ.ም. ኅዳር ወር መግቢያ ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ልደት አዳራሽ የተካሄደው የተማሪዎቹ ስብሰባ የተማሪዎቹን እንቅስቃሴም ሆነ የአገሪቱን ፖለቲካ መሠረታዊ በሆነ መንገድ እንደቀየረው የታሪክ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡

በተጠቀሱት ሁለት ዘመናት መሀል የተማሪውን እንቅስቃሴ ርዕዮተ ዓለምን የአሳብ መደላድል ለመስጠት በማሰብ ራሳቸውን ‹‹ኮሮኮዳይል›› በሚል ስም የጠሩ ጥቂት ተማሪዎች የግራ ዘመም አሳቦችን የሚያብራሩ ሥራዎችን በማንበብና በአሳቡም ላይ መወያየት ጀመሩ፡፡

የኢትዮጵያን ተማሪዎች እንቅስቃሴ በማጥናት ቀዳሚ የሆኑት አውሮፓዊው ራንዲ ቫልሲቪክ፣ ‹‹Haile Selassie Students the Intellectual and Social Background to Revolution›› በሚለው ሥራቸው እንዳስነበቡት፣ ይኼ ኃይለኛ ምሥጢረኝነት፣ አይገመቴነትና በሌሎች ተማሪዎች ዘንድ አይነኬ የነበረው ከ10-15 ተማሪዎችን የሚይዘው የጥናት ቡድን አባል የነበረው የ27 ዓመቱ ወጣት የቀ.ኃ.ሥ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ ዋለልኝ መኮንን፤ ‹‹On the Question of Nationalities in Ethiopia›› በሚል ርዕስ የጻፈውን ባለ አራት ገጽ ጽሑፍ በዩኒቨርሲቲው አዳራሽ በይፋ አቀረበ፡፡

  1. የብሔር ብሔረሰቦች መብት ጥያቄ በኢትዮጵያ

ይህ በዋለልኝ መኮንን የቀረበው ዝነኛ ጽሑፍ፣ ‹‹ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች እስር ቤት/ማጎሪያ ናት፡፡ ኢትዮጵያዊነትም በአማራነት እንዲያም ሲል በትግሬነት ወይም ደግሞ በሰሜናዊ ኢትዮጵያ ባህልና ማንነት፣ በኦርቶዶክስ ሃይማኖት የተቀነበበ ማንነት ነው፤›› ሲል ወቀሰ፡፡ ይህ ባለ 5 ገጽ ጽሑፍም በተለይም ከኦሮሚያና ከደቡብ የአገራችን ክፍል ለመጡ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ትልቅ ደውልና ማንቂያ ሆኖ ነበር፡፡

‹‹የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል›› የሚለው የእስታሊን መርህም ለመጀመሪያ ጊዜ ለብዙዎች ተማሪዎች ጆሮ ደረሰው የዚያን ጊዜ ነበር፡፡ የለውጡ እንቅስቃሴ በጣሙን እየተጋጋለና እየደመቀ፣ ተማሪዎቹም እንደ ‹ታገል›፣ ‹ቻሌንጅ› ባሉ ጋዜጦቻቸው አሳባቸውን እያስፋፉ ትግሉን አፋፋሙት፡፡

ይህ የለውጥ እንቅስቃሴም አውሮፕላን እስከ መጥለፍና በሰሜናዊ አፍሪካና በመካለኛው እስያ ካሉ እንደ ፍልስጤም ነፃ አውጭ ድርጅት ጋር በጋራ ሥልጠና እስከመውሰድ የዘለቀ ግንኙነትን መፍጠር ችሎ ነበር፡፡ የኤርትራና የኦሮሞ ሕዝብ ነፃነት ጥያቄም ከዚሁ ‹‹የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል›› ጥያቄ ጋር ተሰናስሎ ነበር በዩኒቨርስቲው ግቢ ውስጥ ልደቱን አግኝቶ ወደ በረሃ የተመመው፡፡

የሕወሓት ታጋዮችም፣ ‹‹ፍትሕ ተነፍገናል፣ የጭቁን ሕዝባችንም መብቱ ተረግጧል እናም ሁሉም በአገሪቱ ያሉ ብሔረ ብሔረሰቦችና ነፃ ሊወጡ ይገባቸዋል!›› የሚል መርሕን አንግበው ነበር የዩኒቨርስቲና የኮሌጅ ትምህርታቸውን አቋርጠው፣ ‹‹እምቢ ለሕዝባችን፤ እምቢ ለነጻነታችን!›› በማለት ወደ ደደቢት በረሃ ያቀኑት፡፡

እዚህ ጋር ‹‹ከብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ›› ጋር በተያያዘ አንድ ማጥራት ያለብን እውነታ ያለ ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ብሔረሰብ መብት ጥያቄ አሁንም ድረስ ተጋግሎ ያለ ጥያቄ ሲሆን፤ ለኢትዮጵያ የመበታተን አደጋን የጋረጠ፣ የዛ ትውልድ ክፉ ዘር በሚል የዋለልኝን ጽሑፍ የሚረግሙና የሚተቹ በርካታዎች ናቸው፡፡ እውነታው ግን በአገራችን የብሔር ብሔረሰቦች መብት ጉዳይ ሲነሳ እንኳን የተማሪ ጥያቄ ቀርቶ የዛን ጊዜው የቀኃሥ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም አልተመሠረተም ነበር፡፡

የታሪክ ድርሳናት እንደሚጠቁሙትም የብሔር ጥያቄ ቀድሞ የተጀመረ ትግል ነው፡፡ ኤርትራ ውስጥ የትጥቅ ትግል የተጀመረው ለምሳሌ ከአብዮቱ ብዙ ዓመታት በፊት ፌዴሬሽኑ እንደፈረሰ ነበር፡፡ ከትጥቅ ትግሉ በፊት ደግሞ የፖለቲካ ትግሉ እንግሊዞቹ ሳሉ ጀምሮ ለአሥር ዓመታት ተካሂዷል፡፡ ትግራይ የመጀመሪያው የወያኔ አመፅ የተነሳው ዩኒቨርሲቲው ከመመሥረቱ በፊት ነው፡፡ በኦጋዴን የነበረው ችግርም ቀድሞ ነው የተፈጠረው፡፡

ለአብነትም በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ ለግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በጻፉት ‹‹የለውጥ ያለህ›› ተማፅኖና የማስጠንቀቂያ ደብዳቤያቸው፣ ‹‹የብሔር ብሔረሰቦች መብት ጥያቄ›› ውሎ አድሮ የአገሪቱ አደጋ፣ ቀውስ መሆኑ የማይቀር ሐቅ መሆኑን እንደሚከተለው ገልጸውላቸው ነበር፡፡ ‹‹… ከሁሉ በላይ ግርማዊነትዎ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያለው እንቅስቃሴ በተለይ የብሔሮች ጥያቄ አንድ ወቅት ፈንድቶ አደጋ እንደሚያመጣ እንዲገነዘቡት እፈልጋለሁ፡፡ ግርማዊነትዎ አቤቱታዬ እንደ ፊተኞቹ ደብዳቤዎቼ ያነጣጠረው የኢትዮጵያን ሕዝብ ለሥቃይና ለእንግልት የዳረጉትን ጭቆናዎችና ስሕተቶች እንዲያስተካክሉና አሁንም ቢሆን ጊዜው እንዳልመሸ ለማሳሰብ ጭምር ነው››፡፡ እንግዲህ ልብ ልንለው የሚገባው ጉዳይ ዩኒቨርሲቲ ሳይኖርና ተማሪው ትግል ሳይጀምር በፊት ነበር በአገራችን ‹‹የብሔር ብሔረሰቦች መብት›› ጥያቄ ይነሳ የነበረው፡፡

  1. የዘውዱ መንግሥት የቁጣ በትር በተማሪዎች ላይ

የዘውዱን ሥርዓት ዙፋን ያነቃነቁ ጥያቄዎችን ይዞ የተነሳው የተማሪዎች የለውጥ እንቅስቃሴ በሥርዓቱ ላይ በፈጠረው ጫና የተነሳ መንግሥት ቀስ እያለ በተማሪዎቹ መሪዎችና አመራሮች ላይ የአፈና፣ የግዞትና የግድያ ዕርምጃዎችን እንዲወስድ ገፋፋው፡፡ በዚህ ሁኔታም በ1964 ዓ.ም. የተማሪዎች እንቅስቃሴ ዋና መሪ የነበረው ጥላሁን ግዛው ተገደለ፡፡ ይህ የመንግሥት ዕርምጃ ክፉኛ ያስቆጣቸው ተማሪዎችም፣

ጥላሁን ለምን ለምን ሞተ?

ዋለልኝ ለምን ለምን ሞተ?

ማርታ ለምን ለምን ሞተች?

በኃይል በትግል ነው፣

ነፃነት የሚገኘው፡፡

በሚል መፈክር የለውጥ እንቅስቃሴያቸውን ወደ ሌላ ወሳኝ ምዕራፍ እንዲሻገር አደረጉት፡፡ በነገራችን ላይ ጥላሁን ግዛው ከንጉሣውያኑ ቤተሰብ የተገኘ ቢሆንም ያን በተረት ተረትና በግብዝነት ላይ የተመሠረተ ማንነት አሽቀንጥሮ ጥሎ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ራሱን የጭቁኑ ኢትዮጵያውያን ወገን አድርጎ ነበር ሲቆጥር የነበረው፡፡

በአውሮፕላን ጠለፋ ሙከራ ወቅት የተገደሉት ዝነኛው የተማሪዎቹ እንቅስቃሴ መሪና ፖለቲከኛ ዋለልኝ መኮንንም በተመሳሳይ ሁኔታ ራሱን ከጭቁኑ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚመድብ ነበር፡፡ የጥቁር አንበሳ የሕክምና ዩኒቨርስቲ ተማሪ የነበረችውና በአውሮፕላን ጠለፋው ወቅት በጥይት ተደብድባ የሞተችው ማርታ መብራህቱም፣ አባቷ ጄ/ል መብራህቱ ፍስሐ የጃንሆይ ከፍተኛ መኮንንና ባለሥልጣን ነበሩ፡፡

እንደ እነ ጥላሁን ግዛው፣ ዋለልኝ መኮንን፣ ማርታ መብራህቱ የመሳሰሉ ኮከብ የሆኑ የትግል አጋሮቻቸውን በእስራት፣ በግዞትና በሞት የተነጠቁ ተማሪዎቹ ትግላቸው መስዋዕትነትን የሚጠይቅ መሆኑን አስተማሩበት፣ ቀሰቀሱበት፡፡ ዓድዋና የአምስት ዓመቱ የፋሽስት የኢጣልያን ወረራ ድል የመቶ ሺዎች ደምና አጥንት ውጤት መሆኑን ተገንዝቦ

ፋኖ ተሰማራ፣ ፋኖ ተሰማራ፣

እንደ ሆችሚኒ፣ እንደ ቼጉቬራ፣

በዱር በገደሉ፣ ትግሉን እንድትመራ፡፡

የሚሉት የቆዩ ወኔ ቀስቃሽ ዝማሬዎች የሰልፉና የተቃውሞው ማድመቂያና መቀስቀሻ ሆኑ፡፡ ማንነቱን ለሕዝብ መብትና ነፃነት አሳልፎ ሊሰጥ የተዘጋጀ በነፍሱ የቆረጠ ትውልድ በኢትዮጵያ ምድር ድምፁ እንደ ብዙ ውኆች ድምፅ ከፍ ብሎ ተሰማ፡፡ ቅድሚያ ጩኸቱ ለሀገርና ለሕዝብ ያደረገ ትውልድ፣ ያ ሩቅ አላሚ ቅርብ አዳሪ የሆነ ትውልድ፡፡

ተው ስማኝ አገሬ፣ እረ ስማኝ አገሬ፣

ተው ስማኝ አገሬ፣ ሲከፋኝ ነው መኖሬ፡፡

ስማኝ ያገሬ ሰው፣ በአንድ ላይ ተነሳ፣

ድር ከተባበረ፣ ይጥላል አንበሳ በማለት የዘመናት ብሶት እንጉርጉሮውን አሰማ፡፡

  1. ለውጥ ፈላጊ የዚያን ጊዜው ተማሪዎች/ያ ትውልድ

‹‹ደሃ፣ ደሃ ምን ታየበት፣

እንዳይማር የሆነበት፤››

ብሎ ትምህርት ለሁሉም ብሎ የጮኸ ትውልድ ነው፡፡ ማንም የማንንም መብት ሰጪና ከልካይ አይደለም ብሎ፣ ‹‹የዲሞክራሲ መብት ያለገደብ ለሁሉም›› በሚል ደሙን አፍሶበታል፡፡ ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የተውጣጣ ‹‹ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት አሁኑኑ›› መፈክሩ በሥልጣን ጥመኞች ጥይት ሕይወቱን ገብሮበታል፡፡ ‹‹የሴቶች መብት ይረጋገጥ›› መፈክሩ ጀግና ሴቶችን ወደ ትግሉ አደባባይ አሰልፏል፡፡ ሕይወታቸውን እስከ ጽንሳቸው የከፈሉ ታሪክ መዘገባቸው የትግል እመቤቶችን አፍርቶበታል፡፡

‹‹የሃይማኖት እኩልነት መረጋገጥ›› መፈክሩ እስላምና ክርስቲያኑ በአንድ ዓላማ አሰልፎ፣ አስተቃቅፎ አታግሏል፡፡ ‹‹የብሔር ብሔረሰቦች መብት ያለገደብ›› ጩኸቱ ኦሮሞው፣ አማራው፣ ትግሬው፣ ጉራጌው፣ ወላይታው፣ አደሬው ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በጋራ እንዲሰለፍ አድርጎታል፡፡ እንግዲህ ይህ ሁሉ የተጠራቀመ የዘመናት ብሶት ወለደው የተማሪዎቹ እንቅስቃሴ በጊዜ ሂደት የ1966ቱን የየካቲት ሕዝባዊ አብዮትን የወለደው፡፡

ይቀጥላል…

(ይህ ጽሑፍ ማስታወሻነቱ በቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን የማይዳሰሱ ቅርሶች (Intangible Heritage) ከፍተኛ ኤክስፐርት፣ የኢትዮጵያና አፍሪካ ታሪክ ተመራማሪና ተቆርቋሪ ለነበረው ለወዳጄ ለነፍሰ ኄር አቶ ኃይለ መለኮት አግዘውና በቅርቡ በሞት ለተለየን ‹ለታሪክ አዋቂውና ለታሪክ ነጋሪው› ለነፍሰ ኄር ገነነ መኩሪያ/ሊብሮ ይሁንልኝ)፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በደቡብና በምዕራብ አፍሪካ ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ ሆነው ያገለገሉ፣ በአሁን ጊዜ ደግሞ በጥናትና ምርምር ዘርፍ ከፍተኛ ተመራማሪ፣ የታሪክና የቅርስ አስተዳደር ባለሙያ፣ እንዲሁም በዩኒቨርሳል ፒስ ፋውንዴሽን የሰላም አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው fikirbefikir@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡