እኔ የምለዉ የባንኮቻችንና የተቆጣጣሪው አካል ጉዞ ወዴት እየሆነ ነው?

አንባቢ

ቀን: March 31, 2024

በአንተነህ ዳኘው

በቅርቡ  የባንኮች ዓመታዊ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ የስብሰባ ጥሪዎችና ዓመታዊ የአፈጻጸም ሒደቶች ጋር በተያያዘ በርካታ የንግድ ባንኮች፣ በተለይ ገና ከአጀማመራቸው የት ይደርሳሉ የተባሉትና በአንደኛ አሊያም በሁለተኛ ትውልድ ዘርፍ ሊመደቡ ከሚችሉት ሳይቀሩ ውዝግብ ውስጥ እንደሆኑ፣ ከብዙኃን መገናኛ ዘዴዎች የሚሠራጩትን ሰፊ የዜና ሽፋኖች እያሳዩን/እያስነበቡን ይገኛሉ፡፡ ለመሆኑ ይህንን አጋጣሚ መሠረት በማድረግ የባንክ ኢንዱስትሪው ያለበት አሳሳቢ ሁኔታና አካሄድ በሚመለከታቸው በቅርብ የመንግሥት አካላት፣ በባንኮቹ ባለአክሲዮኖች፣ በተባባሪ አካላትና በምሁራን በአግባቡ ታይተው ይሆን? ሁኔታዎቹ ተመልካች አጥተው መፍትሔ ሳያገኙ ሲንከባለሉ ከርመው በመጨረሻ ልክ እሳት የማጥፋት ዓይነት ዕርምጃ ለመውስድ ከመሯሯጥ፣ ለፋይናንስ ዘርፉ ጥንቃቄ የተሞላበት እንቅስቃሴ የሚረዱ ተቋማዊ ሕግታት፣ በተለይም የበላይ ተቆጣጣሪው የብሔራዊ ባንክ ኢንስፔክሽንና ሱፐርቪዥን፣ እንዲሁም በቼክ ሊስትና ፎርማቶች የተደገፈ ውጤት ተኮር ክትትል፣ ግምገማና በእጅጉ ቅስቀሳ ያስፈልገዋል ለማለት አያስደፍርም፡፡

በቅርቡ በጥቂት ባንኮች ላይ እየተወሰዱ ያሉት ዕርምጃዎች የሚያበረታቱ ቢሆኑም፣ እየተከሰቱ ያሉት ችግሮች የጥቂቶች ገመና ብቻ ሳይሆኑ በሁሉም ረገድ ጫን ያለ ፍተሻ ቢደረግ የሁሉንም ባይባልም የበርካታዎችን በር ማንኳኳታቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የሁሉም ባንኮች የጤናማነት ደረጃ በጥልቅ ተመርምሮ መፍትሔ ካልተደረገለት ችግሮች የሚቀጥሉና ላለመባባሳቸው ማረጋገጫ የሚኖር ስለማይመስል አደገኛ ሁነቶች ሳይከሰቱ በአግባቡ ቢጤኑ ለባንኮቹም ለአገርም የሚበጅ ይሆናል፡፡ እንደሚታወቀው አብዛኞቹ ባንኮች ዓመታዊ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ሲያደርጉ ዓመታዊ የኦፕሬሽንና የፋይናንስ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ይፋ ያደረጉ ሲሆን፣ ከእነዚህ ሪፖርቶችና ከስብሰባ ሒደቶቹ በመነሳት በርካታ ግድፈቶችና ማብራሪያ የሚሹ ነጥቦች በግልጽ የሚታዩ እንደ መሆናቸው ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ከጥብቅ የዕዝ ኢኮኖሚ ሥርዓት ወደ ገበያ መር ኢኮኖሚ ባደረገችው ሽግግር ከተወሰዱት ባለብዙ ፈርጅ የማሻሻያ ፕሮግራሞች ውስጥ፣ የሊበራላይዜሽንና የፕራይቬታሽን መርሆን በመከተል በመንግሥት ብቻ ተይዞ የነበረውን የባንክ ዘርፍ ለግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ክፍት የማድረግ ሪፎርም መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ይህንንም በመከተል በቅድሚያ በርካታ የግል ባንኮች በአገር ውስጥ ባለሀብቶች የሚቋቋሙበት አሠራር የተፈጠረ ሲሆን፣ በሒደትም የባንኩን ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት የማድረግ ቀጣይ ዕርምጃ ሲጠበቅ ቆይቷል፡፡ በተለይም በበለፀጉ ለጋሽ አገሮችና በኃያላኑ ዓለም አቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች በኩል ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት የማድረጉ ሒደት እንዲፋጠን፣ በመንግሥት ላይ የተለያዩ ተፅዕኖዎችም ይባል ጫናዎች ሲደረጉ ነበር፡፡ በመንግሥት በኩልም ይቀርቡ ከነበሩት የማዘግያ ሥልቶች መካከል የአገሪቱ ተቆጣጣሪ አካል ለጊዜው የውጭ ባንኮችን አሠራር በብቃት ለመደገፍም ለመቆጣጠርም አደረጃጀቱና አቅሙ በተጠናከረ ሁኔታ መገንባት እንዳለበት በሚቀርቡ ፕሮፖዛሎች፣ እንዲሁም ገና በምሥረታና በለጋ ዕድሜያቸው ላይ ያሉ የግል ባንኮችም ለዳዴነትና ለፉክክርም የጉልምስና ዘመን ሊቸራቸው ይገባል በሚሉ ሐሳቦች እንደነበረ አይዘነጋም፡፡

 ለዚህም ይመስላል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እ.ኤ.አ. በፌብሯሪ 2009 ያሳተመው “NBE’s Monetary Policy Framework” ገና በመጀመሪያው ገጽ 1 ላይ “It is self-evident that monetary policy plays an important role in the performance of an economy. However, the effectiveness of the policy in achieving the intended goal largely depends on the institutional factors that constrain or facilitate the implementation process of the policy.” በማለት ያስቀመጠው፡፡ ለመሆኑ በዚህ ሁሉ የጊዜ ሒደት ያለንበት ሁኔታ ምን ይመስላል የተባለውስ ከምን ደረሰ?

ይኸው አንቀጽ ለአገር ኢኮኖሚ አፈጻጸም የሞኒተሪ ፖሊሲው የሚጫወተውን ሚና በማጉላትም ጭምር  እንደ መሆኑ መግቢያው ቢበታተን ባለብዙ ፈርጅ አንድምታ ሊኖረው አንደሚችል ቢገመትም፣ ለሞኒተሪ ፖሊሲው ጠንቃቃነትና ውጤታማ የትራንስፎርሜሽን ትኩረት አቅጣጫ የፋይናንስ ተቋማት ጥራትና የፋይናንስ ገበያ ልማት ወሳኝነት እንዳላቸው ነው፡፡

ከፋይናንስ ተቋማት ልማትና ጥራት አኳያ የዋነኛው ተቆጣጣሪ አካል ተቋማዊና የሰው ኃይል ብቃት በተለይ ጥንቃቄ ለተሞላበት የፋይናንስ ተቋማት የበላይ ተመልካችነት፣ ቁጥጥር አስፈላጊነቱና የሚገባም መሆኑ እንዳለ ሆኖ እንደ ብቸኛ ግብ ተደርጎ መወሰድ ያለበት ሳይሆን፣ በፋይናንስ ገበያው የዕለት በዕለት እንቅስቃሴ እንደ አንቀሳቃሽ ሞተር ሆነው የሚያገለግሉትን በርካታ ባንኮችን ጨምሮ በገበያ ልማት ድርሻ ከተቋዳሽነትም አልፈው የማይናቅ ተሳትፎ እያሳዩ ያሉትን የተለያዩ የማይክሮ ፋይናስ ተቋማትን ማካተት እንደሚገባው ችላ መባል እንደሌለበት ነው፡፡ በተጨማሪም የኅብረት ሥራ ማኅበራት በመንግሥት ደጋፊ ፖሊሲና በተባባሪ አካላት የሚንቆረቆርላቸው ልዩ ልዩ የፈንድ፣ የሥልጠናና የአቅም ግንባታ ዕገዛዎች በተለይ የብድርና የቁጠባ ኅብረት ሥራ ማኅበራትንም የማይናቅ አስተዋጽኦ አበርካችነት የሚጠበቅባቸው ያደርጋል፡፡

በመሠረቱ ይህ አጭርና ውስን ጽሑፍ ጥቂት እልህ አጫሪ የሆኑ ነጥቦችን በማጤን እንደ አንድ ተቆርቋሪ ዜጋ ከምንም ዓይነት የፖለቲካና የሻጥር ቁርኝት በሌለው የኅሊና ተነሳሽነት ችላ የተባሉ የሚመስሉ፣ በዕውን ግን እንደ ማንቂያ ደወል ሊቆጠሩ የሚችሉ አስተያየቶችን ለመነሻ ያህል ለግንዛቤና ለውይይት ታስቦ እንደ መሆኑ የየትኛውንም የፋይናንስ ተቋምም ሆነ የግለሰብ ቁመና እንደሚነካ ተደርጎ እንዳይወሰድ በትህትና ከአደራ ጭምር ሊሰመርበት ይገባል፡፡

ከዚህ በመነሳት ማንም እኔም ያገባኛል የሚልና ጉዳዩ የሚመለከተው ምላሽም ሆነ ማብራሪያ በመስጠት ወይም ምሁራዊና ሙያዊ ትንተና በማበርከት ጠቃሚ ተሳትፎ ቢደረግ የሚደገፍና የሚበረታታም ጭምር እንደሆነ ብዙም ቅስቀሳ አያስፈልገውም፡፡ በተለይም የዩኒቨርሲቲ ድኅረ ምረቃ ፕሮግራሞችን በመከታተል ላይ ያሉ ዝም ብሎ ለመመረቅ ሲባል ብቻ ከሚደረጉ የለብለብና የኩረጃ ጽሑፎች ለበሳል ምርምርና ለመመረቂያ ጽሑፋቸው የባንኮቹን አፈጻጸምና ዓመታዊ ሪፖርታቸውን በጥልቀት በመፈተሽ በጠንካራና በደካማ ጎናቸው ላይ ምሁራዊ ትንተና በማድረግ፣ ከሌሎች የፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ተቋዳሽ ለመሆን ሲተጉ በነበሩ አገሮች ልምድ አኳያ የፋይናንስ ዘርፉ ሚና እንዴት እንደነበረና የአገራችን አካሄድስ ምን ይመስላል፣ ምንስ ተጨባጭ ውጤቶች አስገኘ፣ ምንስ ክፍተቶችና ጉድለቶች ይታዩበታል የሚሉት በአግባቡ ቢጤኑና ጠቃሚ ልምዶችና ተሞክሮዎች ተሰንደው ቢቀርቡ፣ ጠቃሚ ዕውቀትና ልምድ ከመጋራት በተጨማሪም ለፖሊሲ ግብዓቶችም ምቹ መድረኮች የሚሆኑበት አጋጣሚዎችና ዕድሎች ያሉ ይመስላልና ከአገር አኳያ ቢሰመርበት ለማለት ነው፡፡

ከልምድ እንደሚታየው በድህነት ቅነሳና ፈጣን ኢኮኖሚ ዕድገት ባስመዘገቡ አገሮች አንፃር የከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማት ከንድፈ ሐሳብ ባለፈ ሥራቸው አድርገው ለተጨባጭ ውጤቶች መሬት ከሚነኩ አበርክቷቸው መካከል የፋይናንስና የሞኒተሪ ፖሊሲ ሞጋች ውጤቶች፣ የኤክስቴንሽን ሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ ግኝቶችና ግብዓቶች እንደሚጠቀሱ ነው፡፡   

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ባንኮቻችንን እየተገዳደረ ያለው የወለድ ምጣኔ ተለዋዋጭነትና የዋጋ ግሽበት ግዝፈት የመከተል አዝማሚያ የሚጠቀስ ሲሆን፣ ይህም በባንኮቹ የጨዋታ ሜዳ ተፅዕኖ በተለይ የብድር ወጪዎችን በማናር ሳይወሰን በቀላሉ የሚናወጥ ኢኮኖሚና ብሎም የአምራችና የንግድ ድርጅቶችን የመዋዕለ ንዋይ ፍሰትን በማቀዝቀዝ የሥራ ዕድሎችን በመጫን የኢኮኖሚ ዕድገትን ሊገዳደር እንደሚችል ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት ደግሞ ኢትዮጵያ እየተንደረደረች ካለችባቸው ፋይናንስ ገበያ ልማት ዕቅዶችና የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ባንኮች ተሳትፎ ክፍት የማድረግ የአዲስ ምዕራፍ ዝግጅት ረገድ፣ የንግድ ባንኮቻችንም ሆነ የብሔራዊ ባንክ በዕውን ያሉበትን የጥንካሬና የድክመት ደረጃ ቆም ብለው በዕውቀት ላይ በተመሠረተ ግልጽነትና ኃላፊነት በተሞላው አኳኋን የግራና የቀኝ ብቻ ሳይሆን የፊትና የኋላ ፍተሻ ቢያደርጉ፣ ታረክና ሁኔታ እጃቸው ላይ ያስገቡትን አጋጣሚ ሳያባክኑት ሚናቸውን በብቃትና በጥራት ለመወጣት ያስችላቸዋል፡፡ እየመጣ ላለው ሥጋትም ሆነ የምቹ አጋጣሚ ዕድል ተገቢ ቅድመ ዝግጅቶች እንዲያደርጉ እንደሚያግዝ በአፅንኦት መግለጽ ይገባል፡፡

ከታሪክ ለመገንዘብ እንደሚቻለው በአገሮች አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት ረገድ የፋይናንስ ዘርፉ ስለሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ጀምሮ ግንዛቤ እየተቸረው እንደመጣ በርካታ የመረጃ ምንጮችን መጥቀስ የሚቻል ሲሆን፣ በኢትዮጵያም ቢሆን በተለይ በመንግሥት ደረጃ ይህንኑ ሒደት የመጋራት አካሄዶች መንፀባረቅ እንደጀመሩ ነው፡፡ በሒደት እንደታየውም የፋይናንስ ዘርፉ ሚና ምን እንደሆነ እንዳለበት የተለያዩ ዕሳቤዎች የመኖራቸውን ያህል፣ ተጠቃሽነት ያላቸው እንደ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ቀደም ብሎ ሹምተር የተባለ ጀርመናዊ ኢኮኖሚስት እ.ኤ.አ. በ1911 ያበረከተው “Theorie der Wirtschaftlichen Entewicklung” ጽሑፍ የፋይናንስ ዘርፍን የጎላ ሚና ለማሳየት ሞክሮ ነበር፡፡ ይህም ቢሆን በሰሜን አሜሪካና ምዕራብ አውሮፓ ከ1930ዎቹ መግቢያ ጀምሮ ታላቁ የኢኮኖሚ ድባቴ በመባል ተከስቶ ከነበረው አጠቃላይ የኢኮኖሚ ቀሰስተኝነት ረገድ እንኳን ብዙም ትኩረት ሳያገኝ ቆይቶ፣ በ1950ዎቹ የታደሰ ፍላጎትን እንዳነሳሳ ነው፡፡ በኅትመት ደረጃም ቢሆን ለዓለም አቀፍ ተቀባይነት የእንግሊዝኛ ትርጉም ሽፋንም የተቸረው ወደ ሁለት አሠርት ዓመታት ዘግይቶ እንደነበረም ጭምር ነው፡፡

እስካሁን ድረስም ለእድገትም ሆነ ልማት በኢኮኖሚው ግንባር ቀደም አንቀሳቃሽ ሴክተሮች (ከኢንዱስትሪ፣ ግብርናና አገልግሎቶች) ረገድ የፋይናንስ ዘርፉ እንቅስቃሴ ምን መሆን አለበት በሚለው በተለይ ቀዳሚ ይሁን፡፡ ጎን ለጎን አጃቢ ወይም ተከታይ ይሁን የሚሉ ምሁራዊ ክርክሮች ቢኖሩም፣ ጎላ ብለው ተቀባይነት ካላቸው አመለካከቶች ውስጥ ተጠቃሽነት ያለው ለየትኛውም አገር ቀጣይነትና ትርጉም ያለው የኢኮኖሚ ዕድገትም ሆነ ልማት ጤናማ የፋይናንስ አገልግሎት ኢንዱሰትሪ የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ነው፡፡ ለዚህም መሻት ዕውን መሆን ደግሞ በቅድሚያ ሊታሰቡባቸው ከሚገቡት ውስጥ አግባብ ያለው የመንግሥት ፖሊሲ መኖር፣ የተቆጣጣሪው አካል  ተፈጻሚነት ያላቸው ምቹ ሕግጋትና ደንቦች ማመንጨትና ሥራ ላይ የማዋል ብቃት፣ የፋይናንስ ሙያዊ ድጋፍ የመለገስ፣ የየባንኮቹንና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትን የሥራ አመራሮችና የዳይሬክቶሮች ቦርድ በተገቢው መሥፈርቶችና መመዘኛዎች መመልመላቸውና መመደባቸውን በማጣራት ውጤታማነታቸውንም በግልጽ መሥፈርቶች መገምገምና የማያቋርጥ ክትትል የማድረግ፣ የቁጠባ አስቀማጩን ሰፊ ኅብረተሰብ ገንዘብ ያላግባብ ከመመዝበርና ከብልሽት የመከላከል፣ ውስን የሆነውን የብድር አቅርቦት ለተገቢ የልማት የምርታማነት ዕገዛ፣ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ግኝትና አዋጭ ፍላጎቶች የሚመደቡበትን አሠራርና ትግበራ መቆጣጠርና ብልሹ ብድሮችን መከላከል፣ የፋይናንስ ማጭበርበርንና መጥፎ ምግባር ቅሬታዎችን መከታተልና ጥፋተኞችን በሕግ ፊት በማቅረብ፣ በአጠቃላይ በአገሪቱ የፋይናንስ ገበያና ሲስተም መተማመን እንዲኖር የማስቻል ሥራዎች የመሳሰሉት ሊተኮርባቸው እንደሚገቡ ነው፡፡  

በመሆኑም የፋይናንድ ዘርፉ ለዋጋ መረጋጋት፣ ከውጭ ንግድ ሚዛን አጠባበቅና የውጭ ምንዛሪ ግኝት፣ እንዲሁም ከኢኮኖሚው ቀልጣፋ የፋይናንስ ኢንተርሚዲየሽን (እንደ የመዋዕለ ንዋይ/ኢንቨስትመንት ፍሰትን ማመቻቸት፣ የቁጠባ ባህልን ማበረታታት፣ ለልዩ ልዩ ብድር ፍላጎቶች ምላሽ መስጠት፣ የገንዘብ ዝውውርን በማቀላጠፍ በተለይም በሌሎች አገሮች ቀደም ብሎ የተጀመረው በሞባይል የዲጂታል ፋይናንሲንግ፣ የመድን ሽፋን አቅርቦትን ከማሟላት) ጋር በተያያዘ ለኢኮኖሚ ዕድገትም ሆነ ለልማት በግልጽ የሚታይ የወሳኝነት ሚና እንዳለው በመረዳት፣ በዓለም ዙሪያ ከምሁራን የምርምርና የውይይት መድረክ በኢኖቬሽንና በአዳዲስ የፈጠራ ንድፈ ሐሳብም እየታጀበ የፖሊሲ አውጭዎችን ያላሰለሰ የትኩረት አቅጣጫ ሳቢ ዘርፍ ለመሆን በቅቷል፡፡

ለአብነት ያህልም ፕሮፌሰር መሐመድ ዩኑስ የተባሉ በሰሜን አሜሪካ የዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ በትውልድ አገራቸው ባንግላዴሽ ያለውን ሥር የሰደደ ድህነት ለመቅረፍ የፋይናንስ ዘርፉ ተቋማዊ ድጋፍ እንዲያደርግ፣ የማይክሮ ፋይናንስ ንድፈ ሐሳብን ይዘው ወዲያውኑ በግራሚን ባንክ አሠራር ወደ ሙከራ ትግበራ ተሸጋግሮ አገሪቱን በአጭር ጊዜ በድንቅ ተደራሽነትና ውጤታማነት ስሟን አስጠርቶ በዓለም ዙሪያ ለአነስተኛ ብድር አቅራቢነትና የቁጠባ ተቋምነት እንደ ድንቅ ተምሳሌትነት ሆኖ፣ ከአፍሪካም ኢትዮጵያን ከእነ ችግሩም ቢሆን ስመ ጥር ተጠቃሽ እያደረጋት እንዳለ ያለማጋነን መናገር የሚቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ምሳሌ መጥቀስ ቢያስፈልግ በጥቂት የወረዳ ቅርንጫፎች ኦፕሬሽን የጀመሩት አንደ የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋምና የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም የመሳሰሉት የክልሎቻቸውን ወረዳዎች ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል ደረጃ ሽፋን በመስጠት፣ የንግድ ባንኮች ሊደርሱባቸው ያልቻሉትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደንበኞችን የባንክ ተጠቃሚ በማድረግ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም ለመሆን ሲበቁ፣ በተለይም በደንበኞች ብዛትና በአንዳንድ የግምገማ መሥፈርቶች የዓለም አቀፍ ተሸላሚዎች ለመሆን አስችሏቸዋል፡፡ እነሆ ዛሬ ፀደይ ባንክና ሲንቄ ባንክ በመባልም ወደ መደበኛ የንግድ ባንክነት “ግራጁኤት” አድርገው አንቱ በሚባሉበት ደረጃ ግዙፍ የፋይናንስ ተቋማት ለመሆን እየሠሩ ያሉበትን ሁኔታ፣ ከብዙዎቹም ዕድሜ ካስቆጠሩ የንግድ ባንኮች በላቀ ካፒታል የሚንቀሳቀሱበትንም ማንሳት ይቻላል፡፡

እንደሚታወቀው ለየትኛውም ኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት የፋይናንስ ገበያው ትኩረት “Real Sector” በሚባሉት ክፍላተ ኢኮኖሚዎች እንደ መሆኑ፣ በኢትዮጵያም ከኤክስፖርት ዕምቅ አቅም፣ ከአብዛኛው ኅብረተሰብ ቀለብም ሆነ መተዳደሪያነትና ከጠቅላላው የአገር ውስጥ ምርት ግኝት አኳያ ግብርና እስካሁን ድረስ የኢኮኖሚው ጀርባ አጥንት ሆኖ የዘለቀ ቢሆንም፣ የትኞቹም የግል ንግድ ባንኮቻችን ለግብርናው ሴክተር የአንበሳውን ድርሻ የብድር አቅርቦት ሲያቀርቡ አይታይም፡፡ ልክ እንደ ንግድ ባንኮቻችን ግብርናው አዋጭ አይሆንም የሚለውን አንዳንድ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትም የመጋራት ዝንባሌ ቢኖራቸውም፣ በአንፃሩ ትልልቆቹና የገበያ ተፅዕኖ ያላቸው የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የብድር አቅርቦታቸው በአብዛኛው የግብርና ምርትንና ምርታማነትን ለማሳደግ ለሚውሉ ግብዓቶች ለመሳሰሉት የሚያውሉት እንደሆነ ነው፡፡

የዚህ ዓይነቱ ከአፍ የዘለለ ተጨባጭ ውጤት ዝም ብሎ ገበያው በመደገፉ ብቻ የተገኘ ሳይሆን፣ ገና ከመነሻው ጀምሮ ለዘርፉ በመንግሥት የተሰጠው ቁርጠኝነትና ደጋፊ የፖሊሲ ማዕቀፍ ከሥር ከሥሩም እንዳስፈላጊነቱ አመቺ የማሻሻያ ደንቦችና ድንጋጌዎች እንዲተገበሩ መደረጋቸው፣ የሕዝባዊና የመንግሥታዊ ባለአክሲዮን የዳይሬክተሮች ቦርድ አመራሮች ከውስጥ የመነጨ ሕዝባዊ የባለቤትነት ስሜት፣ የቅርብ የኦፕሬሽን ክትትልና አቅጣጫ ሰጪነት፣ መሬት በነካ የየተቋማቱ የሥራ አመራሮቻቸውና ቡድኖቻቸው ከግል ጥቅመኝነት ባለፈ ኃላፊነት የተሰማው ለለውጥና ውጤታማነት፣ እንዲሁም የተረጋጋ ቀጣይነት ያለው የሥራ አመራር፣ የተባባሪ አካላት የፈንድ፣ የሥልጠናና የአቅም ግንባታ ድጋፍና ዕገዛ የመሳሰሉት ጎላ ያለ ተጠቃሽነት እንዳላቸው ነው፡፡

በተጨማሪም የደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ፋና ወጊነትና የኢትዮጵያ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ማኅበር ትስስርና ብርቱ ተጋድሎ፣ በተለይም አፈር ይቅለላቸውና ከመሥራችነት ጀምሮ ለረጅም ጊዚያት ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት ወልዳይ አምሐ (ዶ/ር) አመራር የጎላ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው ከአንዳንድ የመረጃ ምንጮች መረዳት ይቻላል፡፡ ማኅበሩ ከትስስር አመቻችነቱና ከወትዋችነት በተጨማሪ ለአባላቱና ለተባባሪ አካላት የሚሳተፉበት ቋሚ ፕሮግራሞች እንደሚያካሂድ፣ እንደ አስፈላጊነቱም የተለያዩና ወቅታዊ የውይይት አጀንዳዎችን በመቅረፅ በክልል ከተሞች ጭምር ሰፊ አሳታፊ መንግሥትን ጭምር በፖሊሲ ግብዓት የሚያነቃቁ ተግባራዊ መድረኮች በማካሄድ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ በአጭር ጊዜ ስም ለማግኘት በቅቷል፡፡ በመዲናችን ዕምብርትም ባለብዙ ወለል ሕንፃ፣ የሥልጠና ማዕከልና ላይብረሪ ጭምር በመገንባት ጥቅም ላይ ለማዋል የበቃ ተቋም ነው፡፡ 

ከምንም ነገር በላይ ለባንክ አገልግሎት በዕውን ያለው ሰፊ የገበያ ክፍተት ደጋፊነት ቢኖረውም በታችኛው ደረጃ የኢትዮጵያ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት እንደ ስኬትና ውጤታማ የሥራ ክንውን ሊያስቆጥርላቸው ከሚገቡት ውስጥ፣ የትራንስፖርትና የግንኙነት መሠረተ ልማቶች እንደ ልብ ባልተስፋፋበት በየገጠሩ በአጠቃላይ፣ በተለይም የምግብ ዋስትና ጉድለት ባለባቸው ወረዳዎች ከዕርዳታ እህልና ዘይት ዕደላ፣ አንዲሁም የሴፍቲኔት ድጋፍ የተንሰራፋው የጥገኝነት መንፈስ (Dependency Syndrome) ለልማትና በግል ጥረት ለሕይወት ለውጥ ተነሳሽነት አናሳ መሆንና ለድህነት ቅነሳ ትርጉም ያለው የራስን መቻል ዝግጁነት ያለማሳየት ተግዳሮት፣ የዕርዳታ ጥገኝነትና የተረጂነት ስሜት ሲፈጥረው የነበረውን ጫና ተቋቁመው በአባባልም በተለይ በፕሮሞሽን ደረጃ ሲያጋጥሟቸው የነበሩትን ለዕርዳታ ነው የመጣችሁት ወይስ ለብድር የሚለው ተግዳሮት በገበሬው ደረጃ ብቻ ሳይሆን፣ ከዕርዳታ አላግባብ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ከጥቅመኛ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ጭምር በቀላሉ የሚታይ እንዳልነበረ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ተግዳሮት እየተሠራ ተቋማቱ ገና ብዙ የሚቀራቸው የለም ለማለት ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ ለልምድም ሆነ ለተሞክሮ ቀሰማ ለማይክሮ ፋይናንስ ገበያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም ፉክክርና ውድድር አለባቸው ወደሚባሉት እንደ ባንግላዴሽ፣ ቦሊቪያ፣ ኡጋንዳና የመሳሰሉት አገሮች ለትንሹም ለትልቁም ልዑካን መላክ ብዙም በማያስፈልጋት ቁመና ላይ ለመድረስ እንዳስቻላትም ነው፡፡ 

በአንፃሩ አንዳንድ የትና የት ለመድረስና ለኢኖቬሽን ምቹ ሁኔታዎች ተመቻችተውላቸውና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እስከ አፍንጫቸው እንደሚባል ዓይነት ከሁለት አሠርት ዓመታት በላይ በማያቋርጥ አሳዳጊነት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር የብዙ ሚሊዮኖች ዶላር የብድር ፈንድ ድጋፍ፣ የሥልጠናና የተቋማዊ አቅም ግንባታ ዕገዛ ሲንቆረቆርላቸው የነበሩ በተግባር ግን ከሥም መቀያየር ውጪ ገና ከዝቅተኛ አሠራር ለመላቀቅ ሲፍጨረጨሩና እስከ “Ghost Loan” የከፋ የብድር ብልሽት ተግዳሮት ሲገዳደራቸው እንደሚታዩ ነው፡፡ ለመሆኑ ከላይ በመጠኑ ለማቅረብ እንደተሞከረው፣ እንደ የኢትዮጵያ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ማኅበርና ከዚያም ባለፈ የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ምን ሊኮራበትና ለታሪክ የሚያቀርበው መልካም ዜና ይኖር ይሆን?

በተግባር አንደሚታየው ከሆነ የበርካታ የተበላሹ ብድሮች ምንጫቸው በብልሹ የደንበኛ መረጣ፣ ጥልቅ የብድር አፕሬዛል ሥርዓት ያለመኖር ቢኖርም የአቅም ድክመት፣ የውጤት ተኮር ክትትልና ግምገማ ሥርዓት ያለመኖር፣ ደካማ የኢንስፔክሽንና ቁጥጥር ሥርዓት፣ የቦርድ ጣልቃ ገብነት፣ አናሳ ቁጥጥርና አቅም አልባ አመራር፣ በባንኮቹ የሥራ አመራሮች ይሁንታና ድክመት፣ እንዲሁም የብቃና አቅም ማነስ መሆናቸው እየታወቀ የማዕከላዊ ባንኩ ኃላፊነትና ሚናስ እንዴት ይታያል? ለወደፊቱስ ምን ዓይነት የሕግ ዕርምጃና የጥንቃቄ አካሄድስ ታስቧል? በተለይ አንዳንድ ዕድሜ ጠገብ ባንኮች በተከታታይ ሪፖርት እያደረጉት ያለው እጅግ የወረደ ዓመታዊ ትርፍና ከባንኮች የቁጠባ የወለድ ወለል ምጣኔም ያነሰ ዓመታዊ የዲቪደንድ ሥሌት ያለ ተጠያቂነት የሚታለፍበት፣ በተለይ ለተከታታይ ዓመታት የማዕከላዊ ባንክ ተወካዮች በአካል በሚገኙበት የጠቅላላ ስብሰባ እየተነሳ፣ አንዳንዴም በአክሲዮኖች ዕንባ ቀረሽ እሮሮ የሚያሰሙበት ተቆጣጣሪ አለ ወይ እስከሚባል ድረስ ጥያቄ የሚያጭር እስከመሆን ደርሷል፡፡

በተግባር እንደሚታየው አብዛኞቹ የቦርድ አባላት አንድም የጡረተኛ ስብስብ አሊያም በስመ ምሁራን ለፋይናንስ ዘርፉ በማይመጥን ሙያና ልምድ የተሞሉ የሚመስሉበት አካሄድ ይታያል፡፡ በተለይም ደግሞ በዕድሜ የገፉ የምህንድስና፣ የዶክትርነትና የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ይዘው በአባልነት በሚሳተፉባቸው ሁኔታዎችና ክንውኖች የሥጋት አካሄድ እያሳዩ ባሉበት ነገሮች “ቦርድ ፕላስ ጭጭ” ሲሆኑ ምን ማለት ይቻል ይሆን?

ከልምድ አንደሚታየው የቦርድ ተርም ግፋ ቢል በተከታታይ ሁለቴ ሆኖ ሳለ በባንኮች እስከ ሦስት ተርም እየደጋገሙ እንዲመረጡ የሚደረግበት፣ አንድ ተርም አርፈው ወዲያውኑ በድጋሚ የሚመረጡበት፣ ለዚያውም ለምርጫ የተሻለ ብቃትም፣ ልምድም ያላቸው ዕጩዎች ከበቂ በላይ ባልጠፉበት መሆኑ እንዴት ይታያል?   

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡