
ከ 28 ደቂቃዎች በፊት
በሽብር፣ በቦምብ ጥቃት የምትታወቀው ሶማሊያ ነጭ አሸዋ የተንጣለሉባቸው ውብ የሆኑ የባሕር ዳርቻዎች መገኛ ናት።
ሰማያዊ የሆነውን የሕንድ ውቅያኖስ ተንተርሶ የሚገኘው የሞቃዲሾ የባሕር ዳርቻም አንደኛው ነው። በባሕር ዳርቻው አሸዋ ላይ በቆሙት ምሰሶዎች ታዳጊዎች እግር ኳስ ይጫወቱበታል።
ይህ ስፍራ ከውብነቱ እና ከመዝናኛነቱ ባሻገር ሶማሊያ አጥፍተዋል ያለቻቸውን ሰዎች በሞት የምትቀጣበት ስፍራም ነው።
ማስጠንቀቂያ፦ ይህ ጽሑፍ አንዳንድ ሰዎችን ሊረብሹ የሚችሉ ይዘቶች አሉት።
አብዛኛውን ጊዜ የፀጥታ ኃይሎች ወንዶችን በዚህ ስፍራ ይዘው ይመጣሉ። ከምሰሶዎቹ ጋር በፕላስቲክ ገመድ ጠፍረው ያስሩዋቸው እና ጥቁር ልብስ ጭንቅላታቸው ላይ አጥልቀው ጥይት ይተኩሱባቸዋል።
እነዚህን ወንዶች የሚገድለው ተኳሹ ቡድን አባላትም ፊታቸው የተሸፈነ ነው።
እነዚህ የተገደሉ ሰዎች ጭንቅላታቸው ዘንበል ቢልም ሰውነታቸው በገመድ ከምሰሶዎቹ ጋር ተጠፍሮ ቀጥ እንዳለ ይታያል። ልብሶቻቸውን ንፋሱ እያውለበለበው አካላቸው ሲጋለጥም በዚያ አካባቢ ማየት የተለመደ ነው።
አንዳንዶቹ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ያህል ሽብርን በማስፋት እና ሰፊውን የአገሪቱን ክፍል የተቆጣጠረው አልሻባብ አባል ናችሁ በሚል በወታደራዊው ፍርድ ቤት የሞት ቅጣት የተፈረደባቸው ናቸው።
በዚህ የእግር ኳስ ሜዳ በግድያ የሚቀጡት ሌሎቹ ደግሞ ሰላማዊ ዜጎችን ወይም ባልደረቦቻቸውን በመግደል ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ ወታደሮች ናቸው።
አልፎ አልፎም ይህ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ወንጀላቸው ከበድ ያለ ሲቪሎች ላይም ብያኔ ያስተላልፋል።
ባለፈው ዓመት ቢያንስ 25 የሚሆኑ ሰዎች በባሕር ዳርቻው ላይ ተገድለዋል።
በቅርቡ የሞት ፍርድ ተፈጻሚ የሆነበት ሰኢድ አሊ ሞአሊም ዳውድ ይሰኛል። ግለሰቡ ሉል አብዲአዚዝ የተሰኘችውን ባለቤቱን በአንድ ክፍል ውስጥ ቆልፎ በሕይወት እያለች አቃጥሎ በመግደሉ በሞት እንዲቀጣ ተፈርዶበታል። ሚኒስቱን እንዲህ ባለ ጭካኔ የገደላትም ፍቺ ስለጠየቀችው እንደሆነ ተናግሯል።
ግድያዎች ከሚፈጸሙበት ስፍራ በስተጀርባም ጊዜያዊ መጠለያዎች እና የፈራረሱ መኖሪያ ቤቶች ያሉበት መደበኛ ያልሆነ ሰፈር አለ። የቀድሞ የፖሊስ አካዳሚ በነበረበት በዚህ ስፍራ ከ50 በላይ አባወራዎች ይኖራሉ።
የእነዚህ ነዋሪዎች ልጆችም መዋያቸው ይህ የሞት መቀጫው የእግር ኳስ ሜዳ ነው።
“አምስቱ ትንንሽ ልጆቼ ከትምህርት ቤት ወዲያውኑ ተመልሰው ወደ ባሕር ዳርቻው እግር ኳስ ሜዳ ለመጫወት ይሮጣሉ” ትላለች በስፍራው ነዋሪ የሆነችው ፋርቱን መሐመድ እስማኤል።
ህጻናቱ ግድያዎቹ የሚፈጸሙባቸውንም ምሰሶዎች እንደ ጎል እንደሚጠቀሙባቸውም ይህቺው እናት ትናገራለች።
“ሰዎች ተተኩሶባቸው በሚገደሉበት እና ደም በሚረጭበት ስፍራ ስለሚጫወቱ የልጆቼ የጤንነት ሁኔታ ያስጨንቀኛል” ስትልም ለቢቢሲ ገልጻለች።
“ግድያዎች ከተፈጸሙም በኋላ አካባቢው አይጸዳም።”
ተተኩሶባቸው የተገደሉ የእነዚህ ግለሰቦች መቃብሮች በባሕር ዳርቻው አካባቢዎች ይገኛሉ።
- ሶማሊያዊቷን ታዳጊ ደፍረው የገደሉት በሞት ተቀጡ5 ህዳር 2020
- በሶማሊያ የአይኤስ አባላት የሆኑ 6 ሞሮኳውያን ሞት፣ አንድ ኢትዮጵያዊ ደግሞ እስር ተፈረደባቸው2 መጋቢት 2024
- ድብቁ የወሲብ ንግድ በሶማሊያ25 መጋቢት 2023

ለአስርት ዓመታት በግጭት በምትናጠው ሞቃዲሾ ውስጥ የተወለዱት ልጆቿ አመጽ እና ሁከትን መላመዳቸውን ይህችው እናት ትናገራለች።
ሆኖም እሷም ሆነች ሌሎች ወላጆች የግድያ ቅጣቶች በሚፈጸምበት ሜዳ ውስጥ ልጆቹ መጫወታቸው የሚረብሽ እንደሆነ ያምናሉ።
ነገር ግን ልጆቹ ከጓደኞቻቸው ጋር በባሕር ዳርቻው ሜዳ ላይ እንዳይገኙ መከልከል ኑሮን ለማሸነፍ ለሚሯሯጡት ወላጆች ፈታኝ ተግባር ሆኖባቸዋል። የሞት ቅጣቶቹ አብዛኛውን ጊዜ የሚፈጸሙት ማለዳ ከ12 እስከ 1 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ነው።
እነዚህን የሞት ቅጣቶች እንዲያዩ የሚጋበዙት ጋዜጠኞችም ቢሆኑ ህጻናትን ጨምሮ የአካባቢው ነዋሪዎች መሰብሰብ እና መመልከትን የሚከለክላቸው የለም።
ይህ የባሕር ዳርቻው ሜዳ ለግድያ ስፍራነት የተመረጠው በአውሮፓውያኑ 1975 በሲያድ ባሬ አገዛዝ ዘመን ነበር።
ይህ ስፍራ እንዲመረጥ ዋነኛ ምክንያት የነበረው በአቅራቢያው ያሉ ነዋሪዎች እንዲመለከቱ በሚል ነው።
የወቅቱ ወታደራዊ አገዛዝ ለሴቶች እና ወንድ ልጆች በውርስ ላይ እኩል መብት እንዲኖራቸው የሚደነግገውን የቤተሰብ ሕግ የተቃወሙ የእስልምና የሃይማኖት አባቶችን ለመግደል ነበር ምሶሶዎቹን ያቆማቸው።
በአሁኑ ወቅት ያሉት እነዚያው ምሶሶዎች ሲሆኑ ሕዝብ ግድያዎቹን እንዲመለከት አይበረታታም።

ወላጆች በአሁኑ ወቅት እያስጨነቃቸው ያለው ግድያዎቸን መመልከታቸው የልጆቻቸውን መንፈስ ይረብሻል የሚል ብቻ ሳይሆን፣ ድንገተኛ ተባራሪ ጥይት ሊያገኛቸው ይችላል የሚለው ስጋት ጭምር ነው።
ልጆቹ በሚያዩዋቸው ግድያዎች ምክንያት ፖሊስ እና ወታደሮችን በከፍተኛ ሁኔታ ይፈራሉ ይላሉ።
“ማታ ላይ ለመተኛት ትግል ነው፤ ሁልጊዜም በጭንቅ ላይ ነኝ” ትላለች ግድያዎቹ ከሚፈጸሙበት ስፍራ በጥቂት ሜትሮች ርቃ የምትኖረው ፋዱማ አብዱላሂ ቃሲም።
“ጠዋት ላይ የተኩስ ድምጽ ስሰማ ሰው መገደሉን አውቃለሁ” ትላለች።
“ልጆቼ ከቤት እንዳይወጡ ለማድረግ እሞክራለሁ። ወደ ውጭ ስንወጣ በአሸዋው ላይ የምናየው ደም የሚዘገንን ነው” በማለትም ታስረዳለች።
ምንም እንኳን ግድያዎቹ በሚፈጸሙበት ስፍራ የሚኖሩት አብዛኞቹ በዚህ ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ ቢሸበሩም፤ በርካታ ሶማሊያውያን የሞት ቅጣትን በተለይም በአልሻባብ አባላት ላይ መፈጸሙትን ይደግፋሉ።
አንዳንዶች ግን የሞት ቅጣትን ይጸየፉታል። በተለይም የጽዳት ሠራተኛ የነበረው የ17 ዓመት ልጇ ከሁለት ዓመት በፊት በሞቃዲሾ በተፈጸመ የመኪና የቦምብ ጥቃት የተገደለባት ፋዱማ ይህንን መቃወሟ የሚገርም ነው።
በዚህ ጥቃት ልጇን ጨምሮ ከ120 በላይ ሰዎች ሲገደሉ፣ 300 ሰዎች ቆስለዋል። ለዚህም ጥቃት አልሻባብ ተጠያቂ ነው ተብሏል።
“እየተገደሉ ያሉ ሰዎችን በግሌ አላውቃቸውም ነገር ግን ድርጊቱ ኢ-ሰብዓዊ ነው ብዬ አምናለሁ” በማለትም ታስረዳለች።
በዚህ የባሕር ዳርቻ የግድያ ስፍራ አሸዋማው ሜዳ ላይ የሚጫወቱት የዚያ ሰፈር ልጆች ብቻ አይደሉም። በተለይም የሶማሊያ የእረፍት ቀን በሆነው አርብን ጨምሮ በበዓላት ቀናት ከተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች የሚመጡ ታዳጊዎችም መሰባሰቢያ ነው።
ከመካከላቸው አንዱ የ16 ዓመቱ አብዲራህማን አደም ነው።
“እኔ እና ወንድሜ በየሳምንቱ አርብ የምንመጣው ለመዋኘት እና በባሕር ዳርቻው ላይ እግር ኳስ ለመጫወት ነው” ይላል።
“እህቴም ዝንጥ ብላ ከእኛ ጋር ትመጣለች። ፎቶ ለመነሳት እና ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ለመለጠፍ ነው አምሮባት የምትመጣው” በማለት ይገልጻል።
ከሌሎች ሰፈሮች የሚመጡት ታዳጊዎች በባሕር ዳርቻው የሚፈጸሙ ግድያዎችን ቢያውቁም ወደዚያ መምጣታቸውን አያቆሙም።
የቦታው ማማር እና ማዕከላዊ ቦታ ላይ መገኘቱ የበለጠ ይማርካቸዋል።
“የክፍል ጓደኞቻችን ፎቶዎቹን ሲያዩ ይቀናሉ። ነገር ግን ያላወቁት ጉዳይ ይህ የግድያ ስፍራ መሆኑን ነው” ሲልም ያስረዳል።
*ይህንን ጹሁፍ የጻፈችው በሶማሊያ የሴቶች ብቻ የሆነው ቢላን ሚዲያ የተሰኘው ጋዜጠኛ ናኢማ ሰኢድ ናት።