ማርቪን ጌይ መድረክ ላይ

ከ 28 ደቂቃዎች በፊት

ማርቪን ጌይ ከሞተ ከ40 ዓመታት በኋላም የሙዚቃ ሥራዎቹ አሁን ድረስ ተወዳጅነታቸው እና ተደማጭነታቸው አልቀነስም። ከእሱ ጋር እንዲህ ያለውን ዘመን ተሻጋሪ ዝናን የሚጋሩት ኤልቪስ ወይም ዘ ቢትልስ ናቸው።

የማርቪን ጌይ ሥራዎች በሸክላ ቴፖች ላይ ከመቀረጽ ጀምረው፣ የቴፕ ካሴቶች እና የሲዲ ዘመንን ተሻገረው በበይነ መረብ የሙዚቃ ማዳመጫ የቴክኖሎጂ ወቅት ላይ ደርሰዋል።

ማርቪን ጌይ ከ40 ዓመታት በፊት ሕይወቱ ያለፈው ቤት ውስጥ በተፈጠረ ከባድ የቤተሰብ አለመግባባት ምክንያት በአባቱ በጥይት ተመትቶ ነበር።

ነገር ግን ሙዚቃዎቹ አሁንም ድረስ በወር ወደ 20 ሚሊዮን ጊዜ ያህል በኢንተርኔት ላይ ይደመጣሉ፣ ይወርዳል። ከታሚ ቴሬል ጋር የተጫወተው ‘አይን ኖ ማውንቴን’ የተጫወተው ሙዚቃ ደግሞ ከአንድ ቢሊዮን ጊዜ በላይ በበይነ መረብ ላይ ተደምጧል።

ስለዚህ አሁንም በማርቪን ጌይ የተቀዳ አዲስ ሙዚቃ የያዙ የድምጽ ካሴቶች መገኘት ሊኖረው የሚችለው ተጽእኖ የጎላ ነው።

አሁን ከአርባ ዓመታት በላይ ቤልጂየም ውስጥ ተደብቆ የተገኘው ሥራው ከሙዚቃው ኮከቡ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ቅርሶች ክምችት አካል ነው። ይህም አሁን ይፋ ሆኖ የዓለም ሙዚቃ ርዕሰ ጉዳይ ሊሆን ነው።

ማርቪን ከቤልጂየም ጋር ያለው ግንኙነት ከዚህ በፊት ሲነገር ቢቆይም አሁን ይፋ የሆነው ዜና ሳይታወቅ ቆይቷል።

በአንድ የምሽት ክበብ ውስጥ ከአንድ የቤልጂየም የኮንሰርት ፕሮሞተር ጋር በተገናኘበት ጊዜ ለንደን ነዋሪ የነበረው ማርቪን፣ የኮኬይን ዕጽ ሱሰኛ ነበረ። የፕሮሞተሩን አድራሻ ከተቀበለ ከሳምንት በኋላ ደውሎለት ወደ ቤልጂየም የባሕር ዳርቻ ከተማዋ ኦስቴንድ ለመሄድ ዝግጅት አደረገ።

ይህ ጉዞው የሙዚቀኛውን ሕይወት ከዕጽ ጉዳት ታድጎታል ቢባል ማጋነን አይሆንም።

ማርቪን ጌይ በአውሮፓውያኑ 1984 የሞተው በአባቱ በተተኮሰበት ጥይትተመትቶ ነበር
የምስሉ መግለጫ,ማርቪን ጌይ በአውሮፓውያኑ 1984 የሞተው በአባቱ በተተኮሰበት ጥይትተመትቶ ነበር

በሜዳማው የሰሜን ባሕር ዳርቻ ላይ በመሮጥ እና ብስክሌት እየጋለበ እንደገና ወደ ጤናማ ሕይወት ተመልሶ ከታላላቅ ምርጥ ሥራዎቹ አንዱ የሆነውን ‘ሴክሽዋል ሂሊንግ’ የተሰኘውን ሙዚቃን ሠራ።

ማርቪን ለተወሰነ ጊዜ በኖረበት በቤልጂየማዊው ሙዚቀኛ ቻርለስ ዱሞሊን ቤት ውስጥ የተዋቸው የመድረክ አልባሳት፣ የማስታወሻ ደብተሮች እና የቴፕ ካሴቶች ስብስብ በአሁኑ ጊዜ በቻርልስ ቤተሰብ እጅ ይገኛል።

ማርቪን ቤልጂየም ውስጥ በቆየበት ጊዜ የተቀዳ ተሰምቶ የማያውቅ እና ከአርባ ዓመታት በላይ ተደብቆ የቆየ አዲስ ሙዚቃ እንዳለ ቢቢሲ ይፋ የማድረግ ዕድልን አግኝቷል።

በንብረቶቹ ላይ የይገባኛል ጥያቄ ያቀረበው የቤተሰብ የንግድ ሸሪክ የሆነው የቤልጂማዊው ጠበቃ አሌክስ ትራፕፔኒየርስ፣ እጅግ በጣም ውድ በሆኑት የማርቪን ጌይ የመድረክ አልባሳት፣ የማስታወሻ ደብተሮች እና ያልተሰማ ሙዚቃው ዕጣ ፈንታን የሚወስን ሰው ነው።

ይህንን ለቢቢሲ በተለይ ያሳወቀው ጠበቃ፣ በጉዳዩ ላይ የሕግ አቋም ምን እንደሆነ አስርድቷል።

እቃዎቹ “ከ42 ዓመታት በፊት ቤልጅየም ውስጥ ስለቀሩ የቤተሰቡ ንብረት ናቸው” ይላል። “ማርቪን ‘ማድረግ የምትፈልጉትን አድርጉ’ ብሏቸው ተመልሶ አልመጣም። ስለዚህ ይህ ወሳኝ ነገር ነው።”

ከሁሉ ከሁሉ የዚህ ታሪክ ዋነኛው ነገር የሚሆነው ግን ከዚህ በፊት ተሰምቶ የማያውቀው አዲሱ ሙዚቃው ነው።

ጠበቃው አሌክስ፤ የማርቪን ሙዚቃውን ሲለማመድ የሚደመጥበትን አጭር እና ገላጭ የሆነውን ናሙና ለቢቢሲ አሰምቷል። ይህም የሙዚቃው ልዑሉ ማርቪን ጌይ እንደገና በሙዚቃው መድረክ ላይ መነጋገሪያ ሊያደርገው የሚችል አዲስ ሥራ ነው።

የሙዚቃ ቅጂዎቹን በአንድ ዓይነት ቅደም ተከተል መልክ የማስያዙ ሥራ ቀላል አልነበረም። ነገር ግን ይህ አዲስ የተገኘው ሙዚቃ ምን ያህል ትልቅ እና ምን ያህል አስፈላጊ ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ፍንጭን የሚሰጥ ነው።

ሙዚቃዎቹን በሚሰማበት ጊዜ “ማርቪን መዝፈን ሲጀምር አዲስ የሙዚቃ መሳሪያ ስለሚጀምር ቁጥር እሰጥ ነበር” ሲል አሌክስ ይናገራል።

“ሁሉንም 30 ካሴቶች ሳዳምጥ መጨረሻ ላይ የ66 አዳዲስ ዘፈኖችን ማሳያን አገኘሁ። አንዳንዶቹ የተሟሉ እና ሌሎቹ ደግሞ ከ‘ሴክሽዋል ሂሊንግ’ ጋር በተመሳሳይ ጊዜ የተሠሩ ስለነሆኑ ድንቅ ናቸው።”

ከሁሉ በላቀ በአንዱ አዲስ የሙዚቃ ትራክ አማካኝነት የማርቪን ጌይ ሌላ ዓለም አቀፋዊ ስኬት ሊያንሰራራ ይችላል ብሎ አሌክስ ያምናል። ይህም በአንጻራዊነት ቀደምት የቢትልስ ቅጂዎች ታድሰው ለመደመጥ የበቁበት ሁኔታ ለማርቪን ጌይ ሥራም ሊውል እንሚችል ይታሰባል።

አሌክስ ትራፕፔኒየርስ የማርቪን ጌይ ሙዚቃ የተቀዳበትን ካሴት ይዞ
የምስሉ መግለጫ,አሌክስ ትራፕፔኒየርስ የማርቪን ጌይ ሙዚቃ የተቀዳበትን ካሴት ይዞ

አሌክስ ዘፈኑን ለማንም አላሰማም ለሚስቱም ጭምር፤ ነገር ግን በቀላሉ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል “አንድ ዘፈን አለ ለአስር ሰከንድ ያህል ብቻ አዳምጬው ሙዚቃው ቀኑን ሙሉ በጭንቅላቴ ውስጥ ሆኖ አገኘሁት። ቃላቶቹ ቀኑን ሙሉ በጭንቅላቴ ውስጥ ሲያቃጭሉ ውለዋል” ይላል።

ሥራዎቹ የማርቪን ጌይ ስለመሆናቸው ምንም የሚያጠራጥር ነገር የለም።

ቢቢሲ ቤልጂየም ኦስቴንድ ውስጥ በሚገኝ አንድ የሰነዶች ማስቀመጫ ውስጥ ያሉ የማርቪን ጌይን አጠቃላይ ሕይወትን የሚመለከቱ ሰነዶችን ገጽ በገጽ ተመልክቷል።

በዚህም በኮንሰርት ዝግጀት ወቅት የሚቀርቡ ሙዚቃዎች ቅደም ተከትልን የሚገልጹ በታይፕ የተጻፉ ወረቀቶች፣ ሙዚቃውን ለሚቀርጽለት ኩባንያ የጻፋቸው ቁጣን ያዘሉ ደብዳቤዎች፣ የአዳዲስ ሙዚቃዎች ረቂቅ ግጥሞች እንዲሁም የግል ሃሳቡን ያሰፈረባቸው ማስታወሻ ደብተሮች አሉ።

ቢቢሲ ሙዚቃ ለማቅረብ ከአገር አገር በሚዘዋወርበት ጊዜ ይለብሰው የነበረውን መለያው የሆነውን ቀይ ኮትን ጨምሮ ልብሶቹን እና የመድረክ አልባሳቱን የያዘ መደርደሪያን ለመመልከትም ችሏል። ይህም ከአጠቃላዩ የተወሰነው ማሳያ ብቻ መሆኑ ተገልጿል።

ነገር ግን ከሁሉ በላይ የሚሆነው ያልተሰማው አዲሱ ሙዚቃው ነው።

ይህም ከሚፈጥረው ጥልቅ ስሜት አንጻር የሚኖረውን ከፍ ያለ ዋጋ አሌክስ ትራፕፔኒየር አይጠራጠርም።

“የጊዜ ቁልፍን እዚህ ከፍተን የማርቪንን ሙዚቃ ለዓለም ማካፈል እንችላለን” በማለት “በጣም ግልጽ ነው፤ ማርቪን አሁንም አለ” ይላል።

ነገር ግን ስለአእምሯዊ ንብረት እና ስለ ሙዚቃ ህትመት መብቶች ያሉት ሁኔታዎች ግልጽ አለመሆናቸው ጥያቄን ማስነሳታቸው አልቀረም።

የማርቪን ግልጽ ውሳኔ በአውሮፓውያኑ 2019 ለሞተው ቻርልስ ይህንን ቅርስ ለመስጠት መወሰኑ ንብረትነቱ ሙሉ ለሙሉ የዱሞሊን ቤተሰብ ነው ማለት ቢያስችልም ተጨማሪ የባለቤትንት ጥያቄም ይኖራል።

ቤልጂየም ያላት ለየት ያለሕግ አንድ ሰው የተሰረቀም ይሁን በሌላ መንገድ እጁ ያስገባውን ንብረት ይዞ 30 ዓመታት የቆየ እንደሆነ የባለቤት መብትን ያገኛል።

ስለዚህ በቤልጂየም ከ40 ዓመታት በላይ የቆዩት የማርቪን ጌይ ንብረቶች የባለቤትንት ጉዳይ ብዙም የሚያጠያይቅ አይሆንም።

ሙዚቃው የተቀዳበት ካሴት እና ካሴቱ ላይ ያለው ሙዚቃ ንብረትነታቸው በተለያዩ ሰዎች እጅ ነው
የምስሉ መግለጫ,ሙዚቃው የተቀዳበት ካሴት እና ካሴቱ ላይ ያለው ሙዚቃ ንብረትነታቸው በተለያዩ ሰዎች እጅ ነው

ነገር ግን ይህ ሕግ ሙዚቃን በመሳሰሉ በአእምሯዊ ንብረትነት በሚካተቱት ላይ የሚሠራ አይደለም።

ስለዚህም አሌክስ ትራፕኒየርስ እና አጋሮቹ የማርቪን ጌይ ዘፈኖችን የማተም መብት ሳይኖራቸው፣ ሙዚቃው የተቀዳባቸው ካሴቶች ብቻ ባለቤቶች ሊሆኑ ይችላሉ።

እናም በአሜሪካ የሚገኙት የማርቪን ጌይ ወራሾች ከሙዚቃው ጥቅም የማግኘት ንድፈ ሃሳባዊ መብት አላቸው። ነገር ግን ሙዚቃው የተቀዳበት ካሴት ባለቤትነት መብት የሌላ ሰው ስለሆነ አንዳች ስምምነት እስካልተደረሰ ድረስ የሚጠቀሙበት ዕድል የለም።

ነገር ግን በአሌክስ ዕይታ ይህ ሁኔታ ንብረቱ በእጃቸው ላይ ባለው እና በወራሾቹ መካከል አንድ ዓይነት ሰጥቶ የመቀበል የስምምነት በር መኖሩን ያሳያል።

“የማርቪን ቤተሰብ እና ሙዚቃው እጃቸው ላይ ያለው (ዱሞሊን ወራሾች) ሁለታችንም ጥቅም የምናገኝበት ይመስለኛል፤ ከተባበርን እና በዓለም ላይ ትክክለኛ ሰዎችን ካገኘን….አድምጠን የሚቀጥለውን አልበም እንሥራ” በማለት አሌክስ ሃሳብ አቅርቧል።

የማርቪን ጌይ ንብረቶች ቤልጂየም ውስጥ በምሥጢር የተጠበቁበት እና ይፋ የሚደረግበት ሁኔታ ስብስቦቹ ምን ዓይነት ዓለም አቀፋዊ ተጽእኖ ሊኖራቸው እንደሚችል ለመገመት አስቸጋሪ ያደርገዋል።

አሁንም በጣም ወሳኝ የሚሆነው የማርቪን ጌይ ልጆች የሆኑት ማርቪን፣ ኖና እና ፍራንኪ እንዲሁም የንብረቱ አስተዳዳሪዎች ይህንን ሁኔታ እንዴት ይቀበሉታል የሚለው ጥያቄ ነው።

ቢቢሲ የማርቪን ጌይ ቤተሰቦች ምላሽ እንዲሰጡ ጠይቆ ነበር። ከሦስቱ ልጆቹ የሁለቱ ጠበቆች ቤልጂየም ውስጥ ስላሉት ንበረቶች ያውቃሉ። ምናልባት ድርድሮች ሊኖሩ የሚችሉ ሲሆን፣ እስካሁን ግን ምንም የተጀመረ ነገር የለም።

በዚህም የማርቪን ጌይ ሙዚቃ የተቀዳበት ካሴት ባለቤት በሆኑት እና የሙዚቃው ባለመብት በሆኑት ወገኖች መካከል በሚደረግ ድርድር መስማማት ላይ ሊደረስ ይችላል።

ከሞራል አኳያ አንዳንዶች ሰነዶቹ፣ አልባሳቱ እና የሙዚቃ ቅጂዎቹ ስብስብ የጌይ ቤተሰብ ንብረቶች እንደሆኑ በማሰብ በቀላሉ ለእነሱ መሰጠት አለባቸው ይላሉ።

አሌክስ ግን የሕግ ጉዳይ ያን ያህል ግልጽ እንዳልሆነ እና እሱ እና አጋሮቹ ሙሉውን ንብረት በቀላሉ የመሸጥ መብት እንዳላቸው ይከራከራል።

የማርቪን ጌይ ንብረቶችን በተመለከተ በርካታ ያልተቋጩ አወዛጋቢ ጉዳዮች አሉ። እነዚህም ልጆቹን እና ንብረቱን በውርስ ያገኘውን ቤተሰብ በማቀራረብ በሚያስማማ መልኩ ሊቋጩ እና ሙዚቃው ለአድማጭ መድረሱ የመጨረሻው ግብ ነው።

ይህ ደግሞ በአርባዎቹ ዕድሜው መጀመሪያ ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ በአባቱ የተገደለውን ማርቪን ጌይን ከአርባ ዓመታት በኋላ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በሙዚቃው ዓለም የዜና መድረክ ላይ ትልቁ መነጋገሪያ ያደርገዋል።

የማርቪን ጌይ የሙዚቃ ሥራዎች ብቻ ሳይሆኑ አልባሳቱም ቤልጂየም ውስጥ ይገኛሉ
የምስሉ መግለጫ,የማርቪን ጌይ የሙዚቃ ሥራዎች ብቻ ሳይሆኑ አልባሳቱም ቤልጂየም ውስጥ ይገኛሉ