
ከ 4 ሰአት በፊት
የፔሩ ፖሊስ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ዲና ቦሉዋርቴን መኖሪያ ቤት በረበረ።
ባለሥልጣናት እንዳሉት የፕሬዝደንቷን ቤት የበረበሩት በርካታ ሮሌክስ የእጅ ሰዓቶች እንዳላቸው ይፋ ሳያደርጉ ቤታቸው አስቀምጠዋል በሚል ነው።
ምርመራው የተጀመረው ፕሬዝደንቷ አደባባይ ሲወጡ የሚያደርጓቸው የእጅ ሰዓቶች እጀግ ውድ ናቸወ የሚሉ ዘገባዎች መውጣት ከጀመሩ በኋላ ነው።
የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን እንደሚሉት በተለይ ከአውሮፓውያኑ ኅዳር 2022 ጀምሮ የእጅ ሰዓታቸው ውድ እየሆነ መጥቷል።
የፔሩ መንገሥት ቅዳሜ ዕለት የተደረገው ብርበራ “ተገቢ ያልሆነ እንዲሁም ሕገ-መንገሥታዊነት የሚጎድለው ነው’ ብሏል።
“እየተነዛ ያለው ፖለቲካዊ ድምፅ ኢንቨስትመንት እና መላ ሀገሪቱን እየበጠበጣት ነው” ብለዋል የፔሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ጉሰታቮ አድሪያንዜን በኤክስ [የቀድሞው ትዊተር] ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት።
የመንግሥት ንብረት የሚቆጣጠረው ባለሥልጣን ፕሬዝደንት ዲና ባለፉት ሁለት ዓመታት ያስመዘገቧቸውን ንብረቶች መልሼ መረምራለሁ ብሏል።
- እነ አቶ ክርስቲያን ታደለ “እንደ መደበኛ ታሳሪ እንዲታዩ” ፍርድ ቤት ትዕዛዝ አስተላለፈ29 መጋቢት 2024
- ትራምፕ፤ ፕሬዝደንት ባይደን እጅና እግራቸው ተጠፍሮ የሚታዩበት ፎቶ መለጠፋቸውን ተከትሎ ወቀሳ ደረሰባቸውከ 6 ሰአት በፊት
- በደቡብ ሊባኖስ በተፈጸመ ጥቃት ሦስት የተባበሩት መንግሥታት ባልደረቦች ጉዳት ደረሰባቸውከ 6 ሰአት በፊት
ባለፈው ሳምንት ንግግር ያሰሙት ፕሬዘደንቷ ወደ መንግሥት መንበር የመጣሁት “ባዶ እጄን ነው፤ የምመለሰውም ባዶ እጄን ነው” ብለዋል።
ዲና አክለው ያደረጉት ሮሌከስ የእጅ ሰዓት ከ18 ዓመታቸው ጀምሮ ጥረው ግረው ባገኙት ገንዘብ የተገዛ መሆኑን ተናግረዋል።
ቅዳሜ ጥዋት ፖሊስ እና አቃቤ ሕግ ያደረጉት ብርበራ ላቲና በተሰኘ የሀገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ በቀጥታ ተላልፏል።
ፖሊስ የፕሬዝደንቷን መኖሪያ ቤት በር ሰብሮ የገባው ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ጥሪ ቢያደርጉም የሚሰማ ስላልነበር ነው ተብሏል።
ከቤተ-መንግሥት ትንሽ ኪሎ ሜትሮች ርቆ የሚገኘው የፕሬዝደንቷ መኖሪያ ቤት በዋና ከተማዋ ሊማ ነው የሚገኘው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ብርበራውን በተመለከተ እስካሁን ምንም ዓይነት አስተያየት ያልሰጡት ፕሬዝደንቷ መኖሪያቸው ሲበረበር ውስጥ ነበሩ።
አድሪያንዘን አክለው ፕሬዝደንቷ ሥልጣን የመልቀቅ ምንም ዓይነት ሐሳብ የላቸውም ብለዋል።
አቃቤ ሕግ ፕሬዝደንት ዲና ሰዓቱን የገዘቡትን ደረሰኝ እንዲያመጡ የሰጠው ቀን ገደብ በመጠናቀቁ ነው ቤታቸው የተበረበረው።
ጠበቃ የነበሩት ፕሬዝደንቷ የሀገሪቱ መሪ የሆኑት የቀድሞው ፕሬዝደንት ፔድሮ ካስቲዮ ኮንግረሱን ለማፍረስ ባደረጉት መኩራ ከሥልጣናቸው እንዲወርዱ ከተደረጉ በኋላ ነው።
ካስቲዮ ከወረዱ በኋላ ፕሬዝደንት ዲና ቦሉዋርቴም ወርደው አዲስ ምርጫ ይካሄድ ያሉ ሰዎች በመዲናዋ ሊማ ከፍተኛ አመፅ አስነስተው ነበር። በአመፁ ምክንያት ከ10 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።