syria

ከ 5 ሰአት በፊት

በሰሜናዊ ሶሪያ የሰዎች እንቅስቃሴ በሚበዛበት ገበያ መሃል መኪና ላይ የተጠመደ ቦምብ ፈንድቶ ቢያንስ ሰባት ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ።

ከቱርክ ድንበር በቅርብ ርቀት በምትገኘው አዛዝ ከተማ ገበያ መሃል የደረሰው ፍንዳታ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎችን አቁስሏል።

ከቦምቡ ፍንዳታ በኋላ የሰዎች አስክሬን መሬት ላይ ወድቆ፣ ሕንጻዎች ፈራርሰው እና በርካታ ተሸርካሪዎች በእሳት ተያይዘው ታይተዋል።

በቱርክ መንግሥት ደጋፊ በሆኑ የሚሊሻ አባላት በምትመራው ከተማ የተፈጸመውን ጥቃት ማን እንደፈጸውም እስካሁን አልታወቀም።

ለጥቃቱም ኃላፊነቱን የወሰደ ቡድንም የለም።

ቦምቡ የፈነዳው በርካታ ሰዎች ለበዓል ለልጆቻቸው ልብስ እና ጫማ እየገዙ ሳለ ነበር።

በዚህ ጥቃት የቆሰሉ ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር እስካሁን አልተገለጸም። ከደረሰው ጉዳት አንጻር ሕይወታቸው ሊያልፍ የሚችሉ ሰዎች ቁጥርም ሊጨምር ይችላል ተብሏል።

በሶሪያ ተጎጂዎችን በማንሳት እና በመንከባከብ የሚታወቀው የበጎ ፍቃደኛ ቡድን ‘ዘ ዋይት ሄልሜት’ ከሟቾቹ መካከል ሁለቱ ሕጻናት ናቸው ብሏል።

በአሌፖ ግዛት የምትገኘው አዛዝ ከተማ የሶሪያ ፕሬዝዳንት በሽር አል-አሳድን በሚዋጉ የሚሊሻ አባላት ነው የምትዳደረው።

ከዚህ በተጨማሪም ትክከለኛው የሶሪያ መንግሥት አስተዳደር ነኝ የሚለው የተቃዋሚ ቡድን መቀመጫ ነች።

ቱርክ ከሶሪያ የምትዋሰንበት አካባቢ ጨምሮ በርካታ አካባቢዎችን ተቆጣጥራ ትገኛለች።

ተንታኞች ይህች ከተማ ለቱርክ ካላት ቅርበት እና የንግድ እንቅስቃሴ መተላለፊያ ኮሪዶር መሆኗን በመጥቀስ በቀጠናው ከፍተኛ የሆነ ጠቀሜታ አላት ይላሉ።

በአዛዝ ጨምሮ በሶሪያ ሰሜን-ምዕራብ ግዛት ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ ያደረጉ የቦምብ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

እአአ 2017 ላይ ከአዛዝ ከተማ ፍርድ ቤት አቅራቢያ መኪና ላይ የተጠመደ ቦምብ ፈንድቶ 40 ሰዎች ተገድለው ነበር።

ለዚህ ጥቃት እአአ 2013 ከተማዋ ለአጭር ጊዜ ተቆጣጥሮ የነበረው እስላሚክ ስቴት ኃላፊነቱን ወስዶ ነበር።