
ከ 1 ሰአት በፊት
ከፊል ራስ ገዝ የሆነችው የሶማሊያዋ ግዛት ፑንትላንድ ሞቃዲሾ ለሚገኘው ለሶማሊያ ፌደራል መንግሥት የሰጠችውን ዕውቅና ማንሳቷን ይፋ አደረገች።
የፑንትላንድ መንግሥት ካቢኔ ቅዳሜ መጋቢት 21/2016 ዓ.ም. ያካሄደውን አስቸኳይ ስብሰባን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ፑንትላንድ ለፌደራል መንግሥቱ ተቋማት ላይ የነበራትን መተማመን በማጣቷ ትሰጥ የነበረውን ዕውቅና ለማንሳት ወስኗል።
ይህ የፑንትላንድ አስተዳደር ውሳኔ የተሰማው የሶማሊያ መንግሥት ፓርላማ ብዙ ባወዛገበ ሂደት በአገሪቱ ሕገ መንግሥቱ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ቅዳሜ ዕለት ይሁንታ መስጠቱን ተከትሎ ነው።
ቅዳሜ መጋቢት 21 የሶማሊያ የላይኛው እና የታችኛው ምክር ቤቶች ፕሬዝዳንቱ የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር የማሰናበትን ሥልጣን የሚሰጠውን ጨምሮ ሌሎችም ማሻሻያዎች በሕገ መንግሥቱ ላይ እንዲደረግ ውሳኔ አሳልፈዋል።
ይህ ለበርካታ ሳምንታት ብዙ ሲያነታርክ የቆየው የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ጊዜ ተወስዶ ሰፊ ውይይት እንዲደረግበት የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች እና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ጥሪ ሲያቀርቡ ነበር።
የከፊል ራስ ገዟ ፑንትላንድ መንግሥት የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ውሳኔን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ የማሻሻሉ ሂደት የተከናወነው የአገሪቱን “የፌደራል ሥርዓት እና ብሔራዊ አንድነትን አደጋ ላይ በጣለ መልኩ” በመሆኑ ውሳኔውን አጥብቆ እንደሚቃወመው አሳውቋል።
- ሶማሊያ ዜጎቿን በሞት የምትቀጣበት የባሕር ዳርቻው የእግር ኳስ ሜዳከ 7 ሰአት በፊት
- “ሕዝብን በድሮን መትተን አናውቅም” ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ10 መጋቢት 2024
- ቱርክ እና ሶማሊያ የተፈራረሙት ወታደራዊ ስምምነት ዋነኛ ትኩረቱ ምንድን ነው?21 የካቲት 2024
“አጠቃላይ የሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እስኪመሠረት ድረስ የፑንትላንድ መንግሥት ለሶማሊያ ፌደራል መንግሥት የሚሰጠውን ዕውቅና ሽሯል፤ በፌደራል መንግሥት ተቋማት ላይም መተማመኑን አንስቷል” ብሏል በመግለጫው።
በከፊል ራስ ገዝ የሆነችው ፑንትላንድ ከአሁን በኋላ ፍላጎቷን ለማስጠቅ ከማዕከላዊወቅ የሶማሊያ መንግሥት እውቅና ውጪ በራሷ አማካይነት የውጭ ግንኙነቶችን እንደምታደርግም ጨምራ ገልጻለች።

ይህ የፑንትላንድ ውሳኔ ከሶማሊያ ተነጥሎ ነጻ አገርነትን ከማወጅ ጋር ሊስተካከል እንደሚችል በመጥቀስ ከሶማሊላንድ ቀጥሎ ለፌደራል መንግሥቱ ሌላ ራስ ምታት እንደሚሆን ተንታኞች እየገለጹ ነው።
የፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ መንግሥት በአሁኑ ወቅት ከሶማሊያ ተገንጥላ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ምክንያት እሰጣ ገባ ውስጥ እንደሚገኝ ይታወቃል።
ፑንትላንድ ከምሥረታዋ ጀምሮ ከሶማሊላንድ በተለየ መልኩ መገንጠልን ሳትመርጥ ከፊል ራስ ገዝ ሆና የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት አካል ሆና ቆይታለች።
ፑንትላን በፈረመችው በሶማሊያ ሪፐብሊክ የፌደራል ቻርተር ላይ ፑንትላንድ የፌደራል ሶማሊያ አባል መሆኗን እና የሶማሊያን አንድነት በመጠቅ ለፌደራል መንግሥቱ ሥርዓት ተገዢ መሆን አለበት ይላል።
በይፋዊ መጠሪያ ስሟ ‘ፑንትላንድ ስቴት ኦፍ ሶማሊያ’ ተብላ የምትታወቅ በከፊል ራስ ገዝ የሆነችው ፑንትላንድ፣ ከአውሮፓውያኑ 1998 ከፊል ራስገዝ አስተዳደር ከሆነችበት ጊዜ አንስቶ የሶማሊያ መንግሥት ፌደራል መንግሥት አካል ሆና ቆይታለች።
ዋና ከተማዋን ጋሮዌ ያደረገችው ፑንትላንድ በሰሜን ምሥራቅ ሶማሊያ የምትገኘው ሲሆን፣ በምዕራብ በኩል ከሶማሊላንድ፣ በሰሜን ምሥራቅ ከሕንድ ውቅያኖስ፣ በምዕራብ በኤደን ባሕረ ሰላጤ እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ ከኢትዮጵያ ጋር ትዋሰናለች።